የሐምሌ 14 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሐምሌ 14 2017ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በዓለም መድረክ ድል ሲቀናቸው፤ ኬኒያዊቷ የማራቶን ሯጭ የተከለከተለ ንጥረ ነገር በመጠቀም ከውድድር ታግዳለች ። በማራቶን ሩጫ ታሪክ የ114 ዓመቱ አዛውንት በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አልፏል ። ገጪው ወጣት ወንጀሉን ለመሸሸግ ሞክሮ ነበር ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በነፃ ተጨዋቾችን እያስመጣ በሚሊዮናት መሰብሰቡ ተሳክቶለታል ። ከሑጎ ኢኬቲኬ የሊቨርፑል ሽያጭ 93 ሚሊዮን ዶላር አጋብሷል ። የጀርመን ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የፈረንሳይ አቻውን በአስደማሚ ሁኔታ ድል አድርጎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል ። የዋንጫ ተፋላሚዎች ማንነት ነገ እና ከነገ በስትያ ይለያል ።
አትሌቲክስ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤት ቀንቷቸዋል ። ቅዳሜ ምሽት በስፔን ማድሪድ እና በቤልጅየም ሂዩስደን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለድል በቅተዋል ። በቤልጅየም ሂዩስደን በነበረው የሴቶች 800 ሜትር ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ንግሥት ጌታቸው አሸንፋለች ። ንግሥት ለድል የበቃችው ውድድሩን በ1 ደቂቃ ከ57.01 ሰከንድ አጠናቅቃ የራሷን ምርጥ ስዓት በማሻሻል ነው ። በስፔን ማድሪድ በነበረ ሌላ ፉክክር ደግሞ በወንዶች 1,500 ሜትር ርቀት ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ አሸንፏል ። አትሌት አብዲሳ አንደኛ የወጣው ርቀቱን በ3ደቂቃ ከ34.63 ሰከንድ በመሮጥ ነው ።
በለንደን የ5ሺህ ሜትር የሴቶች ውድድር እንደተጠበቀው ሁሉ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መዲና ኢሳ አሸንፋለች ። ሐምሌ 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በነበረው እና ብርቱ ፉክክር በታየበት ውድድር አትሌት መዲና ኢሳ ያሸነፈችው ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ30.57 ሰከንድ ሮጣ በመግባት ነው ። በዚሁ ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፋንታዬ በላይነህ በ14 ደቂቃ ከ30.90 ሰከንድ በመግባት እጅግ ለጥቂት ሁለተኛ ወጥታለች ። የራሷን ምርጥ ስዓትም አስመዝግባለች ። አትሌት ፎትየን ተስፋዬ ደግሞ በ14 ደቂቃ ከ32.55 ሰከንድ አራተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች ።
ኬኒያዊቷ የማራቶን ክብረ ወሰን ባለድል ከውድድር ታገደች
የማራቶን ክብረ ወሰን ባለድሏ ሩት ቼፕንጌቲች የተከለከለ ንጥረ ነገር በመጠቀም ከውድድር ታገደች ። ምናልባትም ኬኒያዊቷ ለረዥም ጊዜ ከስፖርት ውድድሮች ልትታገድም ትችል ይሆናል ። ኬኒያዊቷ ሯጭ ጥቅምት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በነበረው የቺካጎ ማራቶን 2 ሰአት ከ09 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ ሮጣ በማሸነፍ ነበር የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ። በወቅቱ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሴቱሜ ከበደ 2 ሰአት ከ17 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ በመግባት የሁለተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር ። የሐምሌ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ናይጄሪያ ውስጥ ሲካሄድ በቆየው የአፍሪቃ እድሜያቸው ከ18 እና 20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ፉክክር ተካፋይ የሆነው የኢትዮጵያ ቡድን ዐሥር ሜዳሊያዎችን አግኝቷል ። ሁለቱ ወርቆች የተገኙት በ5,000ሜ ሴቶች ርምጃ ከ18 ዓመት በታች በሕይወት አምባው፤ እንዲሁም በ800ሜ ሴቶች ከ18 ዓመት በታች ፉክክር በኤልሳቤጥ አማረ ነው ። ኢትዮጵያ በዚህ ፉክክ 28 አትሌቶች ማሳተፏ ተገልጧል ። 2 ወርቅ፣ 3 ብር እና 5 ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን አስመዝግባለች ።
የጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሩብ ፍጻሜ ድል
ለአውሮጳ ዋንጫከፈረንሳይ አቻው ጋር ቅዳሜ ዕለት የገጠመው የጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ ። ጀርመን ምንም እንኳን አንድ ተጨዋቿ በጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትባትም ግብ ጠባቂዋ አን-ካትሪን ቡድኑን ታድጋዋለች ። ካትሪን ሔንድሪክን በ13ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ያጣው የጀርመን ቡድን 100 ደቂቃ ያህል በዐሥር ተጨዋቾች ብቻ ተወስኖ ለመጫወት ተገድዷል ። 75 በመቶ የኳስ ይዞታ የነበረው የፈረንሳይ ቡድን በ25 ከመቶ የኳስ ይዞታ ተወስኖ በነበረው የጀርመን ቡድን መሸነፉ ለደጋፊዎቹ እጅግ የሚያስቆጭ፤ ለጀርመኖች የሚያስቦርቅ ነው ።
ግብ ጠባቂዋ አን-ካትሪን በጨዋታም ሆነ በመለያ ምት ወቅት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን በማጨናገፍ የጀርመን ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ እንዲያልፍ አስችላለች ። ጀርመን ፈረንሳይ በመለያ ምት 6 ለ5 ባሸነፈበት ግጥሚያ ግብ ጠባቂዋ ኳስ ካጨናገፈች በኋላ ተራዋ ደርሶ በመምታት ከመረብ አሳርፋለች፦ በዚያም የቡድኗ ባልደረባዎቿን እና ደጋፊዎቿን አስቦርቃለች ።
የጀርመን ቡድን በግማሽ ፍጻሜው ዙሪክ ከተማ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ከነገ በስተያ ከስፔን ቡድን ጋር ይጋጠማል ። በነገው ዕለት ደግሞ የእንግሊዝ ቡድን ከጣሊያን አቻው ጋር ሌላኛዋ የስዊትዘርላንድ ከተማ ጄኔቫ ውስጥ ይጫወታል ። ነገ እና ከነገ በስትያ ማታ በሚኖሩ ግጥሚያዎች አሸናፊዎች ለዋንጫ ይደርሳሉ ። የፍጻሜው ግጥሚያ የፊታችን እሁድ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ባዝል ስዊትዘርላንድ ውስጥ ይከናወናል ።
የዝውውር ዜና
ሊቨርፑል የጀርመኑ አይንትራኅት ፍራንክፉርት አጥቂ ሑጎ ኤኪቲኬን በ 93 ሚሊዮን ዶላር ለማስመጣት ተስማማ ። የ23 ዓመቱ ፈረንሣዊ ከሊቨርፑል ጋር የስድስት ዓመት ውል ለመፈረም መስማማቱም ተዘግቧል ። ከፕሬሚየር ሊጉ መጀመር ቀደም ብሎ በሚኖረው የዐሥር ቀን የሆንግ ኮንግ እና ጃፓን ጉዞ ኢኪቲኬ የአሰልጣኝ አርኔ ስሎት ቡድንን በዚህ ሳምንት ይቀላቀላል ተብሏል ። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ከሚላን ጋር ለሚኖረው የወዳጅነት ግጥሚያ ዛሬ ሆንግ ኮንግ ደርሷል ።
ሑጎ ኤኪቲኬ ባለፈው የጨዋታ ዘመን ለአይንትራኅት ፍራንክፉርት 22 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ 12 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቷል ። ሑጎ ኤኪቲኬ በሻምፒዮንስ ሊግ ወቅት ነበር የበርካቶች ዐይን ውስጥ የገባው ። ቀደም ሲል ኒውካስል ይህንኑ አጥቂ ለማስመጣት ፈልጎ በዋጋ ሳይስማማ ቀርቷል ። ሊቨርፑል በበኩሉ የኒውካስሉ አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳቅን ለማስመጣት ፈልጎ በገንዘብ ሳይስማማ ፍጎቱ መክኗል ። የሰኔ 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሑጎ ኢኪቲኬ በቡንደስሊጋው ያለፈው የጨዋታ ዘመን የለጋቸው ኳሶች፤ የፈጠራቸው ዕድሎች እና ያመቻቻቸው ሚለጉ ኳሶች ብዛት በቡንደስሊጋው የሚስተካከለው የለም ። ከዚህ አንጻር በአብዛኛው ከአሌክሳንደር ኢሳቅ ጋር ተመሳሳይነት አለው ። ለዚያም ይሆናል ሊቨርፑል ሑጎ ኤኪቲኬን ለማስመጣት የወሰነው ።
ሊቨርፑል ሑጎ ኤኪቲኬን ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት አስመጥቷል
የሑጎ ኤኪቲኬ ትንሽ አሳሳቢው ጉዳይ የሚለጋቸው ኳሶችን ወደ ግብ መቀየሩ ላይ ነው ። በቡንደስሊጋው ከማንም በተለየ 117 ኳሶችን ለግቶ ወደ ግብ የቆየረው 12,8 በመቶውን ያህል ነው ። አሌክሳንደር ኢሳቅን ብንመለከት የሑጎ ኤኪቲኬ ዕድሜ ላይ በነበረበት ወቅት በ32 ግጥሚያዎች ወደ ግብ የቀየራቸው ኳሶች ስድስት ብቻ ነበሩ ። በዚያም ከሑጎ ኤኪቲኬ ያነሰ ነበር ማለት ነው ። ሊቨርፑል ይህን የገመገመ ይመስላል ።
አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሑጎ ኤኪቲኬን ጨምሮ ዖማር ማርሞሽን እና ራንዳል ኮሎ ሙዋኒን በመሸጥ ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ ከ269 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ ችሏል ። ያወጣው ወጪ ግን 18 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ። በ2023 በጋ ወራት ዖማር ማርሙሽ ከቮልፍስቡርግ ወደ አይንትራኅት ፍራንክፉርት የተዛወረው በነጻ ነበር፥ ወደ ማንቸስተር ሲቲ የተዛወረው ደግሞ በ79 ሚሊዮን ዶላር ።
አይንትራኅት ፍራንክፉርት በኮሎ ሙዋኒም በሚገባ አትርፏል ። ከፈረንሳዩ ናንቴ በ2022 ያስመጣው እንደ ዖማር ማርሙሽ ሁሉ በነፃ ዝውውር ነበር ። ከአንድ የጨዋታ ዘመን የጀርመን ቆይታ በኋላ ግን በበጋ ወራት ለፓሪ ሳንጃርሞ ዖማር ማርሙሽን ያስረከበው በ102 ሚሊዮን ዶላር ነበር ። ሑጎ ኤኪቲኬም ቢሆን ባለፈው ዓመት ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው በውሰት ነበር ። ቡድኑ ውሰቱን ወደ ቋሚ ለመቀየርም 18 ሚሊዮን ዶላር ከፍሏል ። በዓመቱ እጅግ አትርፎ ለሊቨርፑል ከ93 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማግኘት ሸጦታል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት የተጨዋቾችን ብቃት ፈጥኖ በመለየት በአትራፊነት መዝለቁን መዘየዱ ተሳክቶለታል ። የሰኔ 9 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በማራቶን ታሪክ የዓለማችን የእድሜ ባለጸጋ
በሕንድ ፑንጃብ ግዛት ነዋሪ ነበሩ የ114 ዓመቱ አዛውንት ፋውጃ ሲንግ ። በእርግጥ የትውልድ ማስረጃ ሠነድ ማቅረብ ባለመቻላቸው በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ጊነስ ወርልድ ላይ አልተመዘገቡም ። እድሜያቸው ግን 114 እንደነበር ይናገሩ ነበር ሕንዳዊው አዛውንት ። በበርካታ የዓለም የማራቶን ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበሩት ፋውጃ ሲንግ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ከዚህ ዓለም የተለዩት በሚኖሩበት መንደር በተሽከርካሪ ተገጭተው ነው ።
ፋውጃ ሲንግ በተለይ በለንድን ማራቶን እንደጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ ለስድስት ጊዜያት ተሳትፈዋል ። ከአንዱ በቀር በሁሉም ውድድሮች የማራቶን ሩጫቸውን ለማጠናቀቅ የፈጀባቸው ጊዜ ከሰባት ሰአት በታች ነበር ። በ2000 እና በ2001 ስድስት ሰአት ከአምሳ አራት ደቂቃ ሮጠው ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል ። በ2003 ያስመዘገቡት ምርጥ ሰአታቸው ስድስት ሰአት ከሁለት ደቂቃ ነበር ። በኒው ዮርክ ሲቲ እና ቶሮንቶ ማራቶን፣ እንዲሁም በሆንግ ኮንግ እና ግላስጎው ግማሽ ማራቶን ውጤት ካስመዘገቡበት ውድድሮች መካከል ይጠቀሳሉ ።
ፋውጃ ሲንግ በ101 ዓመታቸው የማራቶን ሩጫ መወዳደር ያቆሙት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 በለንደን ማራቶን ከተሳተፉ በኋላ ነበር ። ከዚያ በኋላ ግን በ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል ። በ89 ዓመታቸው ማራቶን መወዳደር የጀመሩት ሕንዳዊ በሕጻንነታቸው እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ መራመድ የማይችሉ እንደነበሩ በአንድ ወቅት ገልጠዋል ።
ፋውጃ ሲንግ ባለፈው ሳምንት በ114 ዓመታቸው ሕንድ ፑንጃብ አውራጃ በሚገኘው የትውልድ መንደራቸው በተሽከርካሪ ተገጭተው ነው ሕይወታቸውን ያጡት ። ገጭቷቸው ያመለጠው የ26 ዓመት ወጣት ገዳይ አምሪት ሲንግ ዲሎን የገጨበት ተሽከርካሪውን ደብቆ ላለመያዝ ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር ። ሆኖም ፖሊስ ፈልጎ በቁጥጥር ስር አውሎታል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ