የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 7 2017
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ስምምነት ማዕቀፍ
በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያ እና የጂኦ-ፖለቲካ ትንተና የሚሰጡት ዶ/ር ዳርስከዳር ታዬ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብመጠናቀቅን ተከትሎ በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙ ያሏቸው አስተያየቶች ከአሁን በኋላ በግድቡ ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ወይም የሚቀለብሱት ውሳኔ አይኖርም፡፡ “ግድቡ ላይ የሚመጣው ቀጥተኛ ተጽእኖም አይኖርም፤ ግን ወደፊት የናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ የጋራ ስምምነት እንዲኖር ግፊት ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም የናይል ውሃ ተጋሪ አገራትን በሚሳትፍ እንጂ በግብጽ እና ኢትዮጵያ መካከል ብቻ በሚኖር ስምምነት የሚከወን አይሆንም ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “በአባይ ውሃ ላይ እጅጉን ጥገኛ የሆነች ግብጽ የተጎዳሁ ጩኸት በምታሰማበት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቁን ግድብ ኢትዮጵያ እንዴት ልታጠናቅቅ ቻለች የሚሉ የአድናቆትም ድምጾች ይሰማሉ” የሚሉት ዶ/ር ዳርስከዳር ጫናው ሁሉ በዘላቂነት ግድቡን የማስተዳደር እና ቀጣይ የናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ ስምምነት ፈጽሙ የሚል ግፊት መኖሩ አይቀሬ ነው ሲሉ አስረድተዋልም፡፡
አሜሪካ ለግብጽ ታደላለችን?
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የግድቡ መጠናቀቅ ይፋ መሆንን ተከትሎ በግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ስምምነት ላይ እንድትደርስ እንደሚሹና ግድቡንም አገራቸው በገንዘብ መደገፏን መግለጻቸው እጅጉን አወዛጋቢ አስተያየት ነበር፡፡ ለመሆኑ ትራምፕ አብዛኛውን ጊዜ ለግብጽ የሚያደሉ አስተያየቶች ለመስጠት የሚመርጡት ለምን ይሆን የተባሉት ዶ/ር ዳርስከዳር፤ “የእኛም ፋይናንስ አለበት ማለት እኛም በአባይ ላይ የመወሰን መብት አለን የሚል መልእክት አለው” ብለዋል፡፡
ይህን እውነትነቱን መጠየቅ ግን እጅጉን አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸው ትራምፕ የህዳሴ ግድብን ከመካከለኛው ምስራቅ ፖሊሲያቸው ጋር ለማገናኘት መጣራቸውን፤ ለዚህም ግብጽን የሚስደስት መንገድ በመከተል ግብጽ በፊናዋ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ለምታስፈጽመው ፖሊሲዋ አጋር እንድትሆን ማድረግ ዋናው ፍላጎታቸው እንደሚመስል ገልጸዋል፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ትራምፕ በመካከለኛ ምስራቅ ለማስፈጸም የሚጥሩት “የአብራሃም አኮርድ” እያለፈበት በመምጣቱ ሊሆን የሚችለው በቀጣይ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ጫና ማሳደር ነው ብለዋልም፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ግብጽ ሁሉ በቀጣናው እጅግ ተፈላጊ አገር ሆና እንደምትታይም ገልጸው፤ በዓለም የሰጥቶ መቀበል መርህ መስራት ለሁሉም ወገን እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡
የግድቡ አስተዳደር ስምምነት አስፈላጊነት
በጉዳዩ ላይ ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ፤ “ካሁን በኋላ ሊኖር የሚችለው ድርድር እና ስምምነት ስለግድቡ አስተዳደር ነው” ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ግድቡን የተመለከቱ የመዋቅርና ሌሎች ጉዳይ ለመወያየት ጊዜው አልፏል በማለትም “ካሁን በኋላግድቡ ላይ ጉዳት ቢደርስ በታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም ግብጽ እና ሱዳን እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ስለሚደርስ ግድቡን እንዴት እናስተዳድር የሚለው ጉዳይ ቀጣዩ የውይይት ትኩረት ሊሆን ይችላል” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ የግድቡን መጠናቀቅ ባበሰሩበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ግብጽን ጨምሮ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ለሁሉም የሚጠቅም ያሉትን ግድብ ለመመረቅ እንዲታደሙ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ ያንን ተከትሎ ይፋዊ ምላሽ የሰጠችው ግብጽ ግን ጥሪውን አለመቀበሏንና ያለተጨባጭ ስምምነት የግድቡ ተገንብቶ መጠናቀቅ ላይ ተቃውሞዋን ማሰማቷም ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ