የሀለው ጥቃት
ረቡዕ፣ መስከረም 28 2012በምሥራቅ ጀርመንዋ ከተማ በሃለ ዛሬ ከቀትር በኋላ በአንድ የአይሁዶች ሙክራብ እና አጠገቡ በሚገኝ የቱርክ ምግብ መሸጫ ሱቅ ላይ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተገደሉ።ወደ ሙክራቡ እና ሱቁ ፈንጂዎችም ተወርውረው ነበር።ፖሊስ በግድያ ከተጠረጠሩት መካከል አንዱን መያዙን ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ደግሞ በመኪና ማምለጣቸውን አስታውቋል።የተያዘው ተጠርጣሪውም ሆነ የሟቾቹ ማንነት ይፋ አልሆነም።በጥቃቱ ሁለት ሰዎችም ክፉኛ ቆስለዋል። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ወደ ሙኒክ በሚወስደው አውራ ጎዳና ማቅናታቸውን በአቅራቢያው የምትገኘው እና ተኩስ ይሰማባት ነበር የተባለው የላንድስበርግ ከተማ ከንቲባ ተናግረዋል።የሃለ ማዘጋጃ ቤት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ተኩስ የተከፈተው ሁምቦልት በተባለው ጎዳና ላይ በሚገኘው ሙክራብ ፊት ለፊት እና አጠገቡ ባለው የመቃብር ስፍራ ላይ ነው።በቱርክ ምግብ መሸጣ ሱቅ ላይ ያነጣጠረ ሌላ ተኩስም ነበር። ቢልድ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በአንድ የአይሁዶች የመቃብር ስፍራ ላይም የእጅ ቦምብ ተወርውሯል።የሀላ አይሁድ ማህበረሰብ ሊቀመንበር ማክስ ፕሪቮርስኪ እንዳሉት አንድ የልዩ ኃይል ልብስ እና የብረት ኮፍያ ያደረገ እና ከባድ መሣሪያ የታጠቀ ሰው ሙክራቡ በር ላይ በመተኮስ ሰብሮ ሊገባ ሲሞክር በደህንነት ካሜራ ላይ ማየታቸውን ተናግረዋል።በሩ በተለያዩ አለመሰበሩን የገለጹት ፕሪኮቭስኪ ሙክራቡ ውስጥ የነበሩት ሰዎች በሩን አጥብቀው በመከለል ፖሊስ እስኪመጣ ድረስ ሲጠባበቁ እንንደነበር ገልጸዋል።በወቅቱ በሙክራቡ ውስጥ«ዮም ኪፖር» የተባለውን የአይሁዶች የዓመቱ የተቀደሰ ቀን ነው በማክበር ላይ የነበሩ ቁጥራቸው ከ70 እስከ 80 የሚደርስ ሰዎች እንደነበሩም አስረድተዋል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በመፈለግ ላይ ሳለ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ አሳስቦ ነበር። ብሔራዊው የጀርመን የባቡር አገልግሎት ዶቼ ባን እንዳስታወቀው የሃለ ዋናው ባቡር ጣቢያ ተዘግቶ ነበር።የጀርመን ፌደራል አቃቤ ሕግ ምርመራውን ከአካባቢው ፖሊስ መረከቡን አስታውቋል።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ