የቀድሞዉ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ሞቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 15 2012ማስታወቂያ
የቀድሞዉ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ዣክ ሽራክ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የ86 ዓመቱ የረጅም ጊዜ ታዋቂ የፈረንሳይ ፖለቲከኛ ዣክ ሺራክ፤ ሁለት ጊዜ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ከጎርጎረሳዊዉ 1995 እስከ 2007 ዓም ድረስ ደግሞ ፈረንሳይን በፕሬዚደንትነት አገልግለዋል። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የፈረንሳይን ጦር በመምራት ሃገራቸዉን ነፃ ያወጡት የጀነራል ቻርልስ ደ ጎልን ፈልግ የተከሉት ወግ አጥባዊቅዉ ፖለቲከኛ ዣክ ሺራክ በስልጣን ዘመናቸዉ ለሃገራቸዉ በዉጭ ፖለቲካ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውና በተለይም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባለዉ ግንኙነት ፈረንሳይ ነጻና ሉዓላዊ መሆንዋን ያረጋገጡ መሪ ናቸዉ።በጎርጎሮሳዊው 2003 ዓም ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን ለመዉጋት አጋር ስታሰባስብ የያኔው ፕሬዚደንት ሺራክ፤ ፈረንሳይ በዉግያዉ አትሳተፍም ሲሉ በመወሰናቸዉ በዓለም ፖለቲካ ስማቸዉ በጥሩ የሚነሳ ፖለቲከኛ እንዲሆን አድርጎአቸዋል።ዣክ ሺራክ ዛሬ ቀትር ላይ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉን ቤተሰቦቻቸዉ ናቸው። ሺራክ ባለትዳር እና የሁለት ሴቶች አባት ነበሩ።አንደኛዋ ልጃቸው በህይወት የሉም።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ