ዝምታ ያጠላበት ወሲባዊ ጥቃት በኢትዮጵያ
እሑድ፣ ነሐሴ 11 2017ማስታወቂያ
ከሳምንት በፊት ሁለት ዓለም አቀፍ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ ሴቶች ላይ የተፈጸመው አስገድዶ መድፈርና ዘርፈ ብዙ ወሲባዊ ጥቃት ፍትህ አለማግኘቱ ድርጊቱ የተለመደ ነገር እንዳይሆን እንደሚያሰጋ ጠቁመዋል።ይህ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የተፈጸመ የመብት ጥሰትና ወንጀል በዝምታ መዳፈኑ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ድርጊቱን ሊያስፋፋ እንደሚችልም አሳስበዋል። አብዛኞቹ ሰለባዎች አስፈላጊውን የአካልም ሆነ የስነልቦና ህክምና የማግኘት እድሉ የሌላቸው፣ በዚያም ላይ ማኅበራዊ መገለልን በመፍራት ጥቃቱ እንደተፈፀመባቸው እንኳ ለመግለፅ ሳይችሉ ከነስቃያቸው የሚኖሩ ዓይነት ናቸው። የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች በአካልም ሆነ በስነልቡና በሚደርስባቸው ላይፍትህ አለማግኘታቸው ተጨማሪ ጉዳት መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የመብት ተቆርቋሪዎች በየጊዜው ያመለክታሉ። ጥፋተኞች በሕግ ተጠያቂነታቸው ተረጋግጦ መፍትሄም አለመወሰዱ ውሎ አድሮ ማኅበረሰቡ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝም ሊታሰብበት እንደሚገባም ያሳስባሉ። ፍትህ የሚሻው ዝምታ ያጠላበት ወሲባዊ ጥቃት በኢትዮጵያ የዚህ ሳምንት የዶቼ ቬለ የእንወያይ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ሙሉውን ውይይት ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኔ።
ሸዋዬ ለገሠ