ታዳጊዎች የየዕለት ውሏቸውን በሶሻል ሚዲያ መለጠፍ የሚደገፍ ወይስ የሚነቀፍ?
ዓርብ፣ ነሐሴ 16 2017የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሶሻል ሚዲያ በታዳጊዎች ላይ መልካም ወይንም መጥፎ ተጽዕኖ የማሳደር አቅሙ ትልቅ ነው ፡፡ በተለይም ያልተገደበ እና ወደ ሱስ ደረጃ የደረሰ የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም የጭንቀት ተጋላጭነትን ይጨምራል ፡፡ በርካታ ወጣቶች ሶሻል ሚዲያን በየቀኑ የሚያከናውኑትን የግል እንቅሰቃሴዎቻቸውን ጭምር ፖስት በማድረግ እንደሚጠቀሙ እና አጠቃቀሙን ለማስቆም እንደሚቸገሩም ጥናቶች ያረጋግጣሉ ፡፡
በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነች የ18 ዓመቷ ሰላም ሳሙኤል ኢንስታግራም ፣ ፌስ ቡክ እና ዩቲዩብን ጨምሮ አብዛኞቹን የሶሻል ሚዲያ አይነቶች እንደምትጠቀም ትናገራለች ፡፡ አሁን ላይ ብዙውን ጊዜ ተቀባይ በመሆን ሰዎች የለጠፉትን ከማየት በስተቀር የራሷን የግል ውሎዎች የመለጠፍ ልምድ እንደሌላት የጠቀሰችው ሰላም “ ነገር ግን ሰዎች የቀን ውሏቸውን ቢለጥፉና ለሌሎች ቢያጋሩ ችግር አለው ብዬ አላስብም ፡፡ ወደፊት የተሻለ ሥራ ሠርቼ ልምድና ተሞክሮ ሲኖረኛ እኔም ላደርገው የምችለው ነገር ነው “ ብላለች ፡፡
ሌላኛዋ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪና የ18 ዓመት ወጣት የሆነችው ኤሌሮይ ፍሰሃ የግል ውሎን መለጠፍ ችግር የለውም የሚለውን የወጣት ሰላምን ሀሳብ ትጋራለች ፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ጥንቃቄ ካልተደረገበት መጥፎ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል የጠቀሰችው ኤሌሮይ “ ለምሳሌ የየቀን እንቅስቃሴዎቻችንን ስንለጥፍ ጉዳት ሊያደርሱብን የሚያስቡ ሰዎች ቢኖሩ በስልካችን መረጃ እየሰጠናቸው መሆኑን ላንረዳ እንችላለን ፡፡ የትና ከነማን ጋር እንደምንውል ከታወቀ ሰዎች በቀላሉ ሊያጠቁን የሚችሉበትን ሁኔታ እንፈጥርላቸዋለን ማለት ነው “ ብላለች ፡፡
ወጣት ሰላምም ሆነች ወጣት ኤሌሮይ ሶሻል ሚዲያን በጥንቃቄ እና በተገደበ መልክ መጠቀም ይገባል ብለው ያምናሉ ፡፡ ታዳጊዎች በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሶሻል ሚዲያ ቢጠቀሙ ችግር አለው ብለው እንደማያምኑ የሚናገሩት ታዳጊዎቹ “ ነገር ግን ሲጠቀሙ በአስተውሎት መሆን አለበት ፡፡ ሁሉንም ነገር ወይንም ያገኙትን ነገር በሙሉ መለጠፍ የለባቸውም ፡፡ እንዲሁም ለቤተሰብና ለትምህርት የሚሰጡትን ጊዜ ሊሻማ አይገባም ፡፡ አጠቃቀማቸው በገደብ እስከሆነ ድረስ መጥፎ ጎን አይኖረውም “ ብለዋል፡፡