ዓመታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP 28 በዱባይ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 2016
የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ ጥንስስ
የዛሬ 21 ዓመት በርሊን ላይ በጀርመን መንግሥት ተነሳሽነት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ የተካሄደው እየጨመረ የመጣውን የዓለም የሙቀት መጠን ለመግታት የጋራ እርምጃዎችን ለመውሰድ በማለም ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላ ሃገራት ተሰባስበው የከባቢ አየርን ብክለት ለመቀነስ ያለመውን የኪዮቶ ስምምነትን ተፈራርመው እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2012 ዓ,ም ድረስ ውሉ ዘለቀ። የኪዮቶ ስምምነት ጊዜው ቢያበቃም የተፈለገው ውጤት ላይ ባለመደረሱ ለቀጣይ ስምንት ዓመታት ማለትም እስከ 2020 ድረስ ሁለተኛውን ቃል የተገባው ተግባራዊ የሚሆንበት የተባለ ስምምነት ተደረሰ። የኪዮቶ ውል ፈራሚዎች 192 ሃገራት ነበሩ፤ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከፍ ብሎ 197 ደርሰዋል። ባለፉት ዓመታት በየደረጃውና በዓመታዊ ጉባኤዎች በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በመምከር የዘለቀው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በተለይ ኮፐንሃገር ዴንማርክ፤ እንዲሁም ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ቁልፍ የተባሉ ስምምነቶችን ተፈራርሟል።
COP 28
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP 28 አስተናጋጅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ታሪክ ለማስመዝገብ መነሳቷን አመላክታለች። የጉባኤው ተሳታፊዎች ብዛት፣ እንዲሁም የሚካሄድበት ስፍራ ስፋት ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ጉባኤዎች በተለየ የእጅግ ግዙፍ መሆኑ እየተነገረ ነው። ከዚህ ቀደም በብዙዎቹ ጉባኤዎች ላይ የተሳተፉት በአፍሪቃ የምግብ ይዞታውን ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራት ስብስብ የሆነው የአላያንስ ፉድ ሶቨርኒቲ ኢን አፍሪካ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ሚሊየን በላይ በዱባይ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ድባብ ከወትሮ የተለየ መሆኑን ነው የገለጹልን።
የተመድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጉባኤው ለመሳተፍ ከ97 በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህ መካከል 52 ሺህዎቹ የመንግሥት ተወካጆች እና ታዛቢዎች ሲሆኑ፤ አራት ሺህዎቹ ደግሞ ጋዜጠኞች ናቸው። በዚህም የዘንድሮው ጉባኤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲተያይ የተሳታፊዎቹ ቁጥር እጥፍ ይጠጋል። አምና ግብፅ 50 ሺህ ገደማ ተሳታፊዎችን አስተናግዳለች።
የጉባኤው ዋና ትኩረት
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተጀመረው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሚነጋገር ቢሆንም ዋነኛ ትኩረቱ ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን መጠቀም ማቆም የሚለው መሆኑ እየተገለጸ ነው። ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የመንግሥታቱ ድርጅት እንዲሁም የጉባኤው አስተናጋጅ የሆነችው የአረብ ኤሜሬት ባለሥልጣናት የየበኩላቸውን ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው። በጉባኤው መክፈቻ ዕለት የዘንድሮውን የተመ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤን የፕሬዝደንትነት መንበር የያዙት የተባበሩት አረብ ኤሜሬት የነዳጅ ኩባይና ሥራ አስኪያጅ ሱልጣን አህመድ አል ጃቢር ባሰሙት ንግግር በካይ ጋዞችን ለመቀነስ ለጀመሩት ጥረት የነዳጅ ኩባንያዎች ትብብር እያሳዩዋቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
« ይህ የፕሬዝደንት ጊዜ ታሪክ ከነዳጅ እና ጋዝ ኩባንያዎችን የማሳተፉን ደፋር ምርጫ በመውሰድ የሚያስታውሰው ሀቅ ይሁን። ልንገራችሁ በርካታ ከባድ ውይይቶችን አድርገናል፤ ቀላል አልነበረም። ሆኖም እነዚህ ኩባንያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በ2030 የሜቴይን ጋዝ ብክለትን ለማስወገድ ቁርጠኛ ሆነዋል። በተጨማሪም በርካታ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በ2050 ተመሳሳይ የብክለት ማስወገድ ውሳኔዎችን ተቀብለዋል፤ ለዚህ ለውጥ ለሚያመጣ እርምጃቸውም አመሰግናለሁ። እርግጥ ነው ይኽ በቂ ነው አልልም፤ ከዚህ የበለጠ ማድረግ እንደሚችሉም አውቃለሁ።»
ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ እንዲቆም የሚለውን ሃሳብ ደጋፊ መሆናቸውን የተናገሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በበኩላቸው ፤ እርምጃው ቀስ በቀስም ቢሆን ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት መንገድ መፈለግ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት። በዘንድሮው COP 28 ጉባኤ ላይ ከመነሻው ለከባቢ አየር ብክለት መንስኤዎች ናቸው የተባሉትን ሙቀት አማቂ ጋዞች ለማስወገድ፣ መገኛ ምንቾች የሆኑት ነዳጅ ዘይት፤ ጋዞች እና የድንጋይ ከሰልን የመሳሰሉ የኃይል ምንጮች በታዳሽ የኃይል ምንጮች መተካትን በሚያበረታቱ ንግግሮች መታጀቡ አንድ ነገር ቢሆንም ተግባራዊነቱ በተመለከተ ግን ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ተጠቁሟል። ለበርካታ ዓመታት ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ሚሊየን ከቅሪት አጽም የሚገኘውን የኃይል ምንጭ አጠቃቀምን የማቆምን ተጨባጭነት በተመለከተ ሲናገሩ በተሳታፊ ሃገራት መካከል የተቀላቀለ ስሜት መኖሩን ነው የገለጹት።
ከአንድ ዓመት በፊት ግላስጎው ስኮትላንድ የተካሄደው COP 26 ጉባኤ የድንጋይ ከሰልን ለኃይል ምንጭነት መጠቀም እንዲቀንስ በሂደትም እንዲቆም ከሚል ስምምነት መድረሱ አይዘነጋም። እንዲያም ሆኖ የሩሲያ ዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ የሞስኮ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት መቋረጥ በርካታ የምዕራብ ሃገራትን የኃይል ምርጭ አማራጭ እንዲያማትሩ አስገድዷል።
ሌላው የዘንድሮው ጉባኤ ትኩረት ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማልማትን ይመለከታል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ አፍሪቃ ውስጥ ለዚህ ልማት የሚሆን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ መመደብ ከዚህ ጉባኤ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።
«በዚህም ምክንያት ለአፍሪቃ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገናል። ግራ የሚያጋባ ነገር አለ፤ አፍሪቃ 60 በመቶ የጸሐይ ኃይል የሚያመነጭ አቅም አላት፤ ሆኖም ግን አፍሪቃ የፀሐይ ኃይል ምንጭ ላይ የዋለው መዋዕለ ነዋይ ሁለት በመቶ ብቻ ነው። ስለዚህ ለአፍሪቃ የፀሐይ ኃይል ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር ይኖርብናል። ምክንያቱም ከፀሐይ ኃይል ለማመንጨት ከፍተኛ ወጪ የሚፈልገው መነሻው ላይ መሆኑ የታወቀ ነው፤ የአፍሪቃ ሃገራት ደግሞ የፋይናንስ ገበያን ወይም እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የወለድ መጠን የማግኘት ዕድሉ የላቸውም።»
ከጉባኤው ምን ይጠበቃል
ጉባኤው ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ሃገራት የተስማሙበት የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ታሪካዊ ተጠያቂነት ያለባቸው ሃገራት የወሰኑት የቅነሳ መጠን ተግባራዊነትንም እንደሚገመግምም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። በአየር ንብረት ለውጡ ተጽዕኖ ለተጎዱ ለተጽዕኖው ለተጋለጡ ሃገራት ለብክለቱ ተጠያቂ ሃገራት ይሰጣሉ በሚል የታሰበው ከፍተኛ ገንዘብ ሌላው የዚህ ጉባኤ መነጋገሪያ ሲሆን ከወዲሁም ጀርመን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን ጨምሮ አንዳንድ ሃገራት የየበኩላቸውን የገንዘብ አስተዋጽኦ አሳውቀዋል። ዶክተር ሚሊየን እንደሚሉትም አብዛኛውን ጊዜ በሚደረጉት ጉባኤዎች አለመስማማቱ የሚመጣው በጀትን በሚመለከት ነው። እናም COP 28 በሰፊው ከሚነጋገርበትና ውጤት ከሚጠበቅበት አጀንዳ አንዱ የገንዘብ አስተዋጽኦ ጉዳይ ነው። እንደቀደሙት ጉባኤዎች ሁሉ በዚህ በዱባዩ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ መድረክ ላይ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው ሃገራት መንግሥታት ተግባራዊ እርምጃቸውን እንዲያፋጥኑ የሚጠይቅ ሰልፍ እያካሄዱ ነው። በዛሬው ዕለትም ከቅሪት አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን መጠቀም እንዲቆም ጠይቀዋል። ለሰጡን ማብራሪያ ዶክተር ሚሊየን በላይን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ