የትራምፕ ታሪፍ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገትን እንዳቀዛቀዘ የአይኤምኤፍ ትንበያ አሳየ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 15 2017ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያውን ባለፈው ጥር ከነበረበት 3.3 በመቶ ወደ 2.8 በመቶ ዝቅ አድርጓል። መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው አበዳሪ ተቋም ትላንት ማክሰኞ ይፋ ያደረገው የ2025 ትንበያ በአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ የተጀመረው የኢኮኖሚ ጦርነት የዕድገት መቀዛቀዝ እንዳስከተለ አሳይቷል።
የድርጅቱ ዋና ኢኮኖሚስት ፒየር ኦሊቪየ ጉሪንቻስ በዋሽንግተን ዲሲ ትንበያው ይፋ ሲደረግ “ላለፉት 80 ዓመታት ሲተገበር የነበረው የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደ ገና መሠራት እየጀመረ በመሆኑ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገባን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በጎርጎሮሳዊው 2024 የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ 3.1 በመቶ የነበረ ሲሆን በተያዘው ዓመት ወደ 3.3 በመቶ ያንሠራራል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ይሁንና ከጥር ወር ጀምሮ አሜሪካ በንግድ ሸሪኮቿ ላይ የጣለቻቸው ታሪፎች እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት እና ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት የወሰዷቸው የአጸፋ እርምጃዎች ትንበያውን አዛብተውታል።
“የፖሊሲ እርግጠኝነት መጥፋት የኢኮኖሚ ትንበያው ዋንኛ ገፊ ምክንያት ነው” ያሉት ፒየር ኦሊቪየ ጉሪንቻስ “በዚሁ ከቀጠለ የንግድ ውጥረት መጨመር እና እርግጠኝነት ማጣት ዓለም አቀፍ ዕድገትን ሊያቀዛቅዝ ይችላል” በማለት አስጠንቅቀዋል። ትንበያው እስከ ሚያዝያ 4 ቀን 2025 ተግባራዊ የተደረጉ የታሪፍ ከፊል የፖሊሲ ርምጃዎችን ብቻ እንደሚያካትት የገለጹት የአይኤምኤፍ ዋና ኢኮኖሚስት “የዓለም ዕድገት በዚህ ዓመት 2.8 በመቶ በሚቀጥለው ዓመት 3 በመቶ ይደርሳል። ይህ በጥር 2025 ይፋ ካደረግንው የዓለም የኢኮኖሚ ትንበያ አኳያ በ0.8 በመቶ ዝቅ ያለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በጥር ወር የአሜሪካ ኢኮኖሚ በ2.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተነበየው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትላንት ወደ 1.8 በመቶ ዝቅ በማድረግ ከልሷል። ይህ በታሪፍ ሳቢያ ከዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት ቻይና እና የአውሮፓ ኅብረት ሊገጥማቸው ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ከፍ ያለ ነው። ድርጅቱ ለቻይና ሰጥቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ትንበያ ከ4.6 በመቶ ወደ 4 በመቶ፤ የአውሮፓ ቀጠናን ከአንድ በመቶ ወደ 0.8 በመቶ ዝቅ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ6.6 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል
ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ ሀገራት በ2025 የሚኖራቸው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዕድገት 3.8 በመቶ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከቀጠናው ሀገራት መካከል ሴኔጋል በ8.4 በመቶ ከፍ ያለ ዕድገት ሊኖራት እንደሚችል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰነድ ያሳያል። ዛምቢያ 6.2 በመቶ፣ ኮት ዲቯር 6.3 በመቶ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ 4.8 በመቶ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዕድገት ሊኖራቸው ይችላል።
“በተቀረው ዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች በቀጣው ላይም ጫና” እንደሚያሳድሩ ያብራሩት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኢኮኖሚስት ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ ሀገራት ዕድገት ከቀደመው ትንበያ በ0.4 በመቶ ዝቅ ማለቱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት 5.7 በመቶ አማካኝ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖራቸው እንደሚችል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። በተቋሙ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2025 ኢትዮጵያ 6.6 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይኖራታል ተብሎ ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ አበዳሪ ተቋም ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ያቀረበው ትንበያ ባለፈው ጥር የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ሲያጸድቅ ይፋ ካደረገው ጋር ተመሳሳይ ነው።
ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከሚጠብቀው የኢኮኖሚ ዕድገት በ1.8 በመቶ ዝቅ ያለ ነው። በ2017 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ8.4 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ መንግሥት አስታውቋል።
በ2017 ኢንዱስትሪ በ12.8 በመቶ፣ ግንባታ በ12.3 በመቶ፣ የማምረቻው ዘርፍ በ12 በመቶ እንዲሁም ትራንስፖርት እና ኮምዩንኬሽን 11.4 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ ከሣምንት ገደማ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ባካሔደበት ወቅት ያቀረቡት ሪፖርት ያሳያል።
ኢትዮጵያ በዶናልድ ትራምፕ 10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባታል
ኢትዮጵያን ጨምሮ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በበርካታ ሀገራት ላይ የጣሉት ታሪፍ ለ90 ቀናት እንዲገታ ወስነዋል። ፕሬዝደንቱ በውሳኔያቸው ከጸኑ ከኢትዮጵያ ገበያ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሸቀጦች 10 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል። ከሌሎች ሀገሮች አኳያ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ አነስተኛ ቢሆንም የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ከሦስት ወራት ገደማ በኋላ ተግባራዊ ከሆነ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።
በጎርጎሮሳዊው 2024 ኢትዮጵያ እና አሜሪካ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የንግድ ልውውጥ እንደነበራቸው የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ቢሮ መረጃ ያሳያል። በዓመቱ ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ከአሜሪካ ሸምታለች። በአሜሪካ ገበያ 465.8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ሸጣለች። ኢትዮጵያ ቡና፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ ወደ ልዕለ ኃያሊቱ ሀገር ገበያ የምትልክ ቢሆንም የንግድ ሚዛኑ ግን ወደ አሜሪካ ያደላ ነው።
በአሜሪካ እና የተቀረው ዓለም የታሪፍ ግብግብ የተፈጠረው የንግድ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ “ፈጣን የፖሊሲ እና ተግባራዊ ምላሽ” እንደሚፈልግ የተናገሩት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ ለሀገራቸው “ዕድል” ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ያምናሉ።
የዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ ለኢትዮጵያ ዕድል?
“የተጣለው ታሪፍ በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ላይ የሚፈጥረው መናጋት በኢትዮጵያ ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ መጤን አለበት” ያሉት ዶክተር ፍጹም “ይህ የተገኘ ዕድልም ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል። “ለምሳሌ ከተጣለው ታሪፍ ውስጥ ከእኛ እጅግ የበለጠ ግን የእኛ ዐይነት ሸቀጦችን የሚያቀርቡ ሀገራት የተጣለባቸው ተወዳዳሪነታቸው የተጎዳ በመሆኑ ያን ዕድል ለመጠቀም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።
በእርግጥ በተፈጠረው የንግድ ውጥረት ምክንያት በዓለም ገበያ የታየው ነዳጅን ጨምሮ የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ደሐ ሀገሮች ፋታ ሊሰጥ የሚችል ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ገበያ በምትልካቸው ሸቀጦች ላይ የተጣለባት ታሪፍ 10 በመቶ በመሆኑ ብቻ በገበያው ከፍተኛ ቀረጥ እንዲከፍሉ ሊገደዱ ከሚችሉ ሀገራት አኳያ የበለጠ የመወዳደር አቅም ይኖራታል ማለት አይደለም።
በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር 44 በመቶ ታሪፍ የተጣለባት ኮሎምቢያ ወይም 46 በመቶ ታሪፍ የተጫነባት ቪየትናምን የመሳሰሉ ሀገሮች በምርታማነት እና በገነቡት ኢንዱስትሪ ከኢትዮጵያ የበለጠ ጠንካሮች ናቸው። ሁለቱም ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ቡና አምራች ሀገሮች ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚጥለው ታሪፍ እና የአሜሪካ ሸሪኮች የአጸፋ እርምጃ በደሐ ሀገሮች ላይ “አስከፊ ተጽዕኖ” ሊኖራቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል። በድርጅቱ የዓለም አቀፍ ንግድ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ፓሜላ ኩክ ሐሚልተን “ታሪፍ የውጪ ዕርዳታ ከማቆም የበለጠ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል” ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ኢኮኖሚስት ፒየር ኦሊቪየ ጉሪንቻስ “በታሪፍ ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታ የሚገጥማቸው ተጋላጭ ሀገራት በተለይ ከሰሐራ በርሐ በታች” እንደሚኖሩ ተናግረዋል። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ባለፉት ዓመታት የሚያገኙት እርዳታ እና ብድር በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ያስታወሱት ኦሊቪየ “ከእነዚህ ሀገራት መካከል አንዳንዶቹ ያላቸው ውስን የወጪ አቅም በመሆኑ የሚገኙበት አጣብቂኝ የበለጠ ፈታኝ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ናቸው” ሲሉ አብራርተዋል።
በመጪዎቹ ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ለመንግሥት ወጪ ፋታ ሊሰጥ እንደሚችል የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ ተናግረዋል። ሽግሽጉ ዕዳ ስረዛን ባያካትትም ለመንግሥት የተሻለ የመክፈያ ጊዜ የሚሰጥ ነው።
የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ተባባሪ ሊቀ-መንበር ዊሊያም ሮስ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽጉን በወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደታቀደ ለሬውተርስ ተናግረዋል። ይህ ሒደት የዐቢይ መንግሥት እስከ ጎርጎሮሳዊው 2028 ለአበዳሪ መንግሥታት መክፈል የነበረበትን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያድን ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተፈራረመችው የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሥራ ላይ በሚቆይባቸው ዓመታት የዕዳ ክፍያዋን በ3.5 ቢሊዮን ዶላር መቀነስ ይጠበቅባታል።
አርታዒ ነጋሽ መሐመድ