ውዝግብ ያጠላበት የህወሃት ምሥረታ 50ኛ ዓመት በዓል
ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2017የህወሓትን ክፍፍል ተከትሎ የተለያዩ የአከባበር ስነስርዓቶች በመቐለ ሲስተዋል የሰነበተ ሲሆን፥ በስተመጨረሻ ትናንት ማታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ለበዓሉ አከባበር በመቐለ ተይዞ የነበረ መርኀግብር መሰረዙን አስታውቋል። ዛሬ ጠዋት በመቐለ በሚገኘው ትግራይ ስታድየም በነበረ ስነስርዓት በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሠራዊት አዛዦች፣ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በተለያዩ ፕሮግራሞች በዓሉ ተከብሯል።
በታሪኩ የከፋ በተባለ ቀውስ ላይ የሚገኘው ህወሓት ዛሬ የ50ኛ ዓመት ምስረታው የካቲት 11ን እያከበረ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ትናንት ማታ የካቲት 11ን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት፥ የትግራይ ሕዝብ በመላው ሀገሪቱ ተዘርግቶ የነበረውን የጭቆና ስርዓት ለማስወገድ የካቲት 11 የትጥቅ ትግል መጀመሩን የገለፁ ሲሆን፥ ከትግሉ ድል በኋላ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መትከል፣ የፖለቲካ ልዩነትን በንግግር እና በሕግ አግባብ መቋጫ የሚያገኝበት ሁኔታ መፍጠር ያለመ ትግን መሆኑ ደግሞ ከሌሎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች የተለየ እንደሚያደርገው ገልፀዋል። ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ምክንያት ወደ ግጭት መግባታችን ከየካቲት 11 ዓላማዎች ያፈነገጠ ነው ያለው የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የጽሑፍ መልእክት፥ ከባድ ዋጋ ተከፍሎ ወደ ሰላማዊ ንግግር መመለሱን ግን የሚደነቅ እርምጃ ብለውታል። ይሁን እንጂ አሁንም ፖለቲካዊ ልዩነቶች በትጥቅ የመፍታት ፍላጎት መንፀባረቁ አልቀረም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ጠቁመዋል። የትግራይ ሕዝብና ልሂቃን ወደ መደበኛ ሕገመንግሥታዊ አሰራር የሚመለሱበት፣ በሀገረ መንግሥቱም ተሳትፏቸውን የሚያደርጉበት ጊዜ አጭር እንደሚሆን እያረጋገጥኩኝ መልካም የየካቲት 11 በዓል እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉም መልእክታቸው አጠናቀዋል።
ዛሬ በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሚመራው የህወሓት ክንፍ አዘጋጅነት በመቐለ ስታድዮም የበዓሉ አከባበር ይፋዊ ስነስርዓት ተከናውኗል። በዚሁ መርኀግብር የህወሓት አንዱ ክንፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ የትግራይ ሐይሎች ወታደራዊ አዛዦች፣ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች እና ሌሎች የታደሙ ሲሆን በዚሁ መድረክ ንግግር ያደረጉት የህወሓት መሪ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ 50ኛ ዓመት በዓሉን እየተከበረ ያለው ከጦርነት መልስ ፤ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶርያ ውል ሳይፈፀም ነው ብለዋል።
ደብረፅዮን «ወራሪዎች ከሕገመንግሥታዊ ሉአላዊ የትግራይ ግዛት አልወጡም። በሕዝባችን ላይ ለተፈፀመው «ጀኖሳይድ» ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ሂደት አልተጀመረም። በህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ፖለቲካዊ ንግግርም ቢሆን ገና አልተጀመረም። የዳግም ግንባታ ሥራዎችም በአግባቡ አልተጀመሩም። ከዚህ አልፎ ደግሞ የፕሪቶርያ ውል ፈራሚ እና ተደራዳሪ የሆነው ህወሓት የተሰረዘ ሕጋዊ ሰውነቱን መመለስ ያልቻለ ሲሆን ወደማያስፈልግ ውዝግብ የሚያስገቡ ውሳኔዎች እየተላለፉ የፕሪቶርያው ስምምነትን ወደ አደጋ የሚያስገባ ተግባር እየታየ ነው» ብለዋል።
በተለይም በየአምስት ዓመቱ በተለየ ድምቀት ይከበር የነበረው የካቲት 11 ዘንድሮ እንደቀድሞው አልደመቀም ሲሉ ታዛቢዎች ይገልፃሉ። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የህወሓት ክፍፍል ተደርጎ ተወስዷል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በዓሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ደግሞ «ብሔራዊ በዓል የሆነውን የካቲት 11ን በጋራ ለማክበር» በሃይማኖት መሪዎች እና ሌሎች አሸማጋዮች የተደረገ ጥረት እንደነበረ ያነሳ ሲሆን፥ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል ተቀባይነት ቢያገኝም በሌላኛው የህወሓት ክንፍ በኩል ግን «የሕዝብ በዓሉን የብቻው አድርጎ በመውሰድ» በበዓሉን በእያንዳንዱ ስነስርዓት ተደራቢ ሌላ መርኀግብር በማውጣት ችግር መፍጠሩን በማንሳት፥ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራውን የህወሓት ቡድንን ወቅሷል። ይህንኑ ምክንያት በማድረግም ያልተፈለገ ሁኔታ ላለመፍጠር በጊዜያዊ አስተዳደሩ መቐለ ላይ ለማድረግ ታቅደው የነበሩ የበዓል መርኀግብሮች መሰረዙን ትናንት ሌሊት አስታውቋል።
በዛሬ የትግራይ ስታድዮም መድረክ ላይ የተናገሩት ዶክተር ደብረፅዮን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን ይተግብር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ዶክተር ደብረፅዮን «የፕሪቶርያ ውል መፈፀም ለኢትዮጵያ ሕዝብም የሚጠቅም በመሆኑ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የፈረመው ውል ተግባራዊ እንዲያደርግ ሁሉም ሚናው እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን። የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን የትግራይ ጉዳይ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ብቻ እንደሚፈታ አምኖ ለፖለቲካዊ ንግግር ዝግጁ ሆኖ የፈረመውን ስምምነት በታማኝነት እንዲፈፅም ጥሪ እናቀርባለን» ሲሉ አክለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዛሬው የበዓል ስነስርዓት የትግራይን ታሪክና ባህል የሚያሳዩ ትእይንቶች እንዲሁም ወታደራዊ ሰልፎች በስታድዬሙ ቀርበዋል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ