ውሾችን ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች እያነሱ መጠለያ የሚሰጡት ወጣቶች
ዓርብ፣ ግንቦት 22 2017እንግዶቻችን አዲስ አበባ ላይ ካሉ ችግሮች አንዱን እና የበኩላችንን ድርሻ መወጣት እንችላለን ብለው ያመኑበትን ችግር ለማቃለል ቆርጠው ተነስተዋል። የቤት እንስሳትን በጣም እንደሚወዱ የሚናገሩት እነዚህ ወጣቶች ውሾችን ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየታደጉ መጠለያ ይሰጣሉ። ለዚህም ሶስት ዘመዳሞች እና ሁለት ጓደኞቻቸው በጋራ በመሆን የአዲስ መዳፎች የሚል ትርጓሜ ያለውን አዲስ ፓውስን (addis_paws) አቋቁመዋል። ከመስራቾቹ አንዷ የሆነችው ማራኪ ሰለሞን፤ ለምን አዲስ ፖውስ እንደተባለ ታብራራለች፤«አዲስ ፖውስ የተባለበት ምክንያት ከተማው አዲስ አበባ ውስጥ በመሆኑ ነው፤ ውሾች ደግሞ በእንግሊዘኛ እግራቸው ፖውስ ይባላል፤ »
ሌላዋ መስራች ልዩ ወርቁ ትባላለች። የ17 ዓመቷ ወጣት እስከ 10 ዓመቷ ድረስ አዲስ አበባ ነው ተወልዳ ያደገችው። ከዛ በኋላ ያሉትን አመታት ደግሞ ስፔን ሀገር ፤ባርሴሎና ነው የምትኖረው፤ ይህ ግን ውሾችን ከመታደግ ወደ ኃላ አላስባላትም። «ከልጅነቴ አንስቶ ከእንስሳት ጋር ነው ያደኩት። ውሻ ነበረኝ ፤ ድመቶች እና ጥንቸሎች። እና ከዝኖቼ እና ጓደኞቼ እንስሳ ስለሚወዱ እንዴት እንስሳቶችን መርዳት እንደምንችል አሰብንና ነው አዲስ ፓውስን ያቋቋምነው። እነሱ አዲስ አበባ ነው የሚኖሩት። የድሮ ቤታችንን ወደ መጠለያነት አስቀይረን እዛ የሚያግዘን ሰው አለ። ውሾችን ያበላሉ። ከዝኖቼ እዛ እየሄዱ ከእነሱ ጋር ይጫወታሉ፤ ያጥቧቸዋል ፤ይመግቧቸዋል። »
የሰዎች አስተያየት ምን ይመስላል?
ይህንንም ፕሮጀክት ከጀመሩ አንስቶ ልዩ ወደ ኢትዮጵያ እንደወትሮዋ በአመት ሁለቴ ሳይሆን በየሁለት ወሩ መሄድ መጀመሯን ገልጻልናለች። ማራኪ እና ልዩ የእህትማማች ልጆች ናቸው። 16 ዓመቷ ማራኪ ቦታው ላይ እንደመገኘቷ ውሾችን ከጎዳና ሲታደጉ ያለው የሰዎች አቀባበል እንዴት እንደሆነ ጠይቀናታል። «ሁሉም የተለያየ አስተሳሰብ ነው ያለው። አንዳንድ ሰዎች ጎበዞች የሚሉ ፤ በምግብ የሚረዱም አሉ። አንዳንዶች ደግሞ መንገድ ላይ ስናበላ። የሚሳደቡ፤ ሰው እያለ ውሻ ታበላላችሁ የሚሉ፤ ክፉ የሚናገሩም አሉ። እኛ ግን ጥሩውን ብቻ ነው የምንወስደው»
አዲስ አበባ ውስጥ በሚደረገው የኮሪዶር ልማት የተነሳ በርካታ ውሻ የነበራቸው ሰዎች ውሻቸውን ይዘው የሚገቡበት ቤት ስለሌላቸው ጎዳና ላይ የሚቀሩት ውሾች ቁጥር መበራከቱን ልዩ ትናገራለች፣«ሲፈርስ ብዙ ውሻ የነበራቸው ሰዎች ውሻ ይዘው ወደ ኮንዶሚኒየም መግባት ስላልቻሉ ብዙ ውሾች ጎዳና ላይ አሉ። በዚህ ችግር ምክንያት ነው ይህን ፕሮጀክት የተጀመረው። አሁን አምስት ወራችን ነው ከጀመርን። እስካሁን ከመቶ በላይ ውሾች ታድገናል። ከነዚህ ውስጥ 40 ያህሉ ናቸው የሚያሳድጋቸው አግኝተው የተሰጡት፤ ካለው ችግር ጋር ሲነፃጸር ብዙ አይደለም። ግን ምንም ካለማድረግ ይሻላል።»
በአሁኑ ሰዓት በመጠለያ ውስጥ አምስት ትላልቅ ውሾች እና 15 ቡችሎች እንዳሉዋቸው የምትናገረው ልዩ «ለውጥ ለማምጣት የማህበረሰቡ ትብብር ያስፈልጋል» ትላለች። ወጣቶቹ ወደ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና ህፃናት ሙዋያዎችም በመሄድ ስለ ውሾች እንክብካቤ ግንዛቤ ያስጨብጣሉ።
«ውሻ ከሰው ጋር መሆን ይፈልጋል። ምግብ ይፈልጋል። መታጠብ ይፈልጋል። ውሾች የሚያጫውታቸው ይፈልጋሉ። በቀን ቢያንስ አራት ሰዓት ያህል ከሰው ጋር መሆን አለባቸው። መከተብ አለባቸው። ጥሩ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። »
የውሻ ጉዲፈቻ
ጎዳና ላይ ያሉ ውሾች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ እና ወጣቶቹ ያቋቋሙት መጠለያ በቂ ባለመሆኑ የተነሳ ማራኪ እንደገለፀችልን ውሾቹ ያሉበት ጎዳና ላይ እየሄዱም የሚመግቧቸው አሉ። « ሰው ከደገፈን ወደፊት ተለቅ ያለ መጠለያ የመክፈት ሀሳብ አለን። ሰዎች ምግብ ፣ ማጫወቻ ፣ በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ። »
ወጣቶቹ እዛው ውሾቹ የተጠለሉበት ቤት ውስጥ የሚያዘጋጁት ሌላም ነገር አለ፤ « በወር እና በየሁለት ወሩ መጠለያውን ለ ስድስት ሰዓታት ያህል ከፍተን፤ ውሻ የሚፈልግ ሰው መጥቶ ውሻዎቹን አይቶ እንዲወስድ በራችንን ክፍት እናደርጋለን።» ማራኪም ውሻ ፈላጊዎች ውሻ ከሚገዙ ይልቅ በቅድሚያ እነሱ ጋር የተጠለሉትን ውሾች አይተው እንዲወስዱ ታበረታታለች፤ « ለምን ቢባል መንገድ ላይ የተጣሉ ብዙ ውሾች ስላሉ ብዙ ብር አውጥተው ከሚገዙ እነዚህን የታከሙ ውሾች መጥተው እንዲወስዱ ነው የምናበረታታው»
ውሾቹ እርስ በእርሳቸው ምን ያህል ይስማማሉ?
በርካታ ውሾችን በአንድ ቦታ ማስቀመጡስ ከባድ አይሆንም? ልዩ መልስ አላት፣« ውሾቹ ሰው እንደሚጠብቃቸው አይደሉም። ውሾቹ ሰው ይወዳሉ። ከሌሎች ውሾች ጋር አንዳንዴ ይጣላሉ። ግን አንድ ላይ ሲጫወቱ ደህና ናቸው። አዲስ ውሾች ሲመጡ ለአንድ ሶስት ቀን ቤት አላቸው። ከዛ ለሌሎች ውሾች ጋር አገናኝተን እናለማምዳቸዋለን። »
ስራው ጉልበት ብቻ ሳይሆን ገንዘብም ይጠይቃል። ምግብ ፣ ክትባት ወዘተ። ወጣቶቹ ወጪያቸውን እንዴት ይሸፍናሉ? «ብዙ ማገዝ የሚፈልጉ አሉ። ከእነሱ ብር እንሰበስባለን። ወይም በትምህርት ቤት ፈንድ ሬዚንግ እናደርጋለን። ወይ ምግብ እየሸጥን ቲኬት እየሸጥን ነው ብር የምናሰባስበው።»
በየዕለቱ ከውሾች ጋር ጊዜ ማሳለፉ የወጣቶቹን የትርፍ ጊዜ አይሻማባቸውም? በፍፁም ትላለች ማራኪ፤ « በጣም ውሻ ስለምንወድ ፣ ፍቅር ስላለን ባለን ሰዓት ነው የምንሄደው። ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት በኋላ መንገዳችንም ስለሆነ ውሾቹ ያሉበት ቦታ ሄደን ፤ተጫውተን እንዴት እንደዋሉ ጠይቀን ነው የምንሄደው። »