ዉይይት፤ኢትዮጵያ ዉስጥ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር፣እጥረትና እስከፊ ጫናዉ
እሑድ፣ ሰኔ 29 2017ኢትዮጵያ ዉስጥ በየጊዜዉ የሚንረዉ የነዳጅ ዘይት ዋጋና እጥረት ዘንድሮም እንደአምና ሐቻምናዉ የሕዝቡን እንቅስቃሴ እያወከ፣ ኑሮዉን እያስወደደ፣ ታዛቢዎችን እያነጋገረ ነዉ።የኢትዮጵያ ተከታታይ መንግሥታት ለነዳጅ ዘይት ያደርጉት የነበረዉ ድጎማ ከ2014 ጀምሮ እየቀነሰ መጥቶ ባለፈዉ ግንቦት ማብቂያ ጨርሶ ተነስቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ድጎማዉን ለማንሳቱ ከሰጣቸዉ ምክንያቶች ዋናዎቹ መንግሥት የሚከተለዉ የምጣኔ ሐብት ተሐድሶ እንዲሳካ-አንድ፣ ለድጎማ ይዉል የነበረዉን ገንዘብ ለሌላ ልማት ለማዉል የሚሉ ናቸዉ።
ይሁንና መንግሥት ለነዳጅ ዘይት፣ ለማደበሪያ ይሁን ለሌላ የሚያወጣዉን ገንዘብ እንዲቀንስ የተገደደዉ በአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት በተለይም በIMF ግፊት እንደሆነ ተቋማቱም፣ባለሙያዎችም ይስማማሉ።ድጎማዉ በመነሳቱ አምና ግንቦት አካባቢ 78 ብር ይሸጥ የነበረዉ አንድ ሊትር ቤንዚን ዘንድሮ 122 ከ53 ሳንቲም ደርሷል።
ነዳጅ ዘይት ከመወደዱ በተጨማሪ በየነዳጅማደያዉ አለመገኘቱ ወይም እጥረቱ ለብዙዎች ፈተና ሆኗል።የኢትዮጵያ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንዳሉት ከዉጪ የሚገባዉ የነዳጅ መጠን አልቀነሰም።ባለሥልጣናቱ ለእጥረቱ «ስግብግብ» እና «ኮንትሮባንድ» ነጋዴዎች ያሏቸዉን ወገኖች ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ለድጎማዉ መነሳት ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የነጃ ዋጋ አለቅጥ ተንቻርሯል።-ለእጥረቱ ተጠያቂዉ ማንም ሆነ ማን እጥረቱ አለ።የዋጋዉ ንረትና እጥረቱ ወትሮም በየአካባቢዉ በሚደረጉ ግጭቶች ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለ፣ መሥራት ያልቻለዉ ወይም ሰላማዊ ዝዉዉሩ የተገደደበበት ሕዝብ፣ በብር የመግዛት አቅም መዳከምና በዓለም ላይ በሚታየዉ ግሽበት ምክንያት ኑሮ የተወደደበት ሕዝብ ለከፋ ችግር መጋለጡን በየአጋጣሚዉ እየተናገረ ነዉ።
በዛሬዉ ዉይይታችን የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናርና እጥረቱ ያስከተለና የሚያስከትለዉን ችግር ባጫጭሩ አንስተን መፍትሔዉን ለመጠቆም እንሞክራለን።
አራት እንግዶች አሉን።
ዶክተር ደስታዉ መኳንንት----የኢትዮጵያ የነዳጅና ኢንርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር
ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ------የኤኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያና ተንታኝ
አቶ ሙሼ ሰሙ-----የቀድሞ ፖለቲከኛ፣ የባንክ ባለሙያ፣ የፋይናንስ ጉዳይ ተንታኝ
አቶ ቁምላቸዉ አበበ------የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ተሟጋች ድርጅት ኃላፊና ጋዜጠኛ
ናቸዉ።
ነጋሽ መሐመድ