ዉይይት፤ የገዥዉ ብልፅግና ፓርቲ የ 5 ዓመት ጉዞ - ስኬት እና ድክመት ሲገመገም
እሑድ፣ ኅዳር 29 2017
ዉይይት፤ የገዥዉ ብልፅግና ፓርቲ የ 5 ዓመት ጉዞ ስኬት እና ዉድቀት ሲገመገም
የኢትዮጵያዉ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ የተመሰረተበት አምስተኛ ዓመት ማጠቃለያ ዝግጅት ባለፈዉ ሳምንት ማብቅያ በይፋ ተከብሯል። በዚሁ ክብረ በዓል ላይ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ፤ ባለፉት 5 ዓመታት በፖለቲካዉ፤ በኤኮነሚዉ እና በማኅበራዊ ዘርፎች አከናዉኛለሁ ያላቸዉን ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል። ከአምስት ዓመታት በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፤ ህወሓትን ጥሎ የተዋሐደው የብልጽግና ፓርቲ አባላት ቁጥር፤ ከ15 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ ዐቢይ ተናግረዋል።
ሀገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብር እና ነፃነት የብልፅግና ፓርቲ እሴቶች መሆናቸዉን ዐቢይ ገልፀዋል። በመድረኩ ላይ አብዝተው ፓርቲያቸውን ያወደሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የተሻለ እሳቤ እና ሀሳብ ከማፍለቅ ይልቅ፤ የተሻለ ሴራ መጎንጎን እንደ ብቃት የወሰዱ ሲሉ የደርጉን ገዢ ፓርቲ ኢሰፓን፣ የወቅቱን ተቃዋሚ ፓርቲ ኢሕአፓን፣ ህወሓትን እና ኦነግን በኮሙኒስትነት ፈርጀዋቸዋል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከመንግሥታቸው ጋር የሚዋጉ ታጣቂዎች ”አንድ ሺህ ዓመት ቢታገሉ“ እንደማያሸንፉ የተናገሩት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የፋኖ ታጣቂዎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ወደ ሰላም እንዲመጡ” ጥሪም አቅርበዋል። ሆኖም፤ ይህ ጥሪያቸዉ ብዙዎችን ሲያነጋግር እና ትችት ሲያሰናዝር ሰንብቷል።
ኢትዮጵያን የሚመራዉ ብልጽግና ፓርቲ ፤ የፖለቲካ ምህዳርን ከማስፋት ፤ የአገሪቱን ኤኮኖሚ ከማሳደግ ዲሞክራስያዉ እና ሰብዓዊ መብቶችን ከማስጠበቅ አንጻር ድጋፍም ተቃዉሞም እየተሰማበት ዛሬ ደርሷል። ባለፉት ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ አሳካለሁ ብሎ ያላሳካዉ፤ ነገር አለመኖሩን ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የፓርቲዉ ባለስልጣናት እና አብዛኞች ደጋፊዎቹ ይናገራሉ። የብልፅግና የአምስት ዓመት ጉዞ ስኬት እና ድክመት እንዴት ይመዘናል? ዛሬ የምንወያይበት ርዕሳችን ነዉ።
በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን ሊያካፍሉን፤
1, አቶ ሬድዋን ምትኩ ፤ የብልፅግና ፓርቲ የሚዲያ ዘርፍ አቀንቃኝ ከአዲስ አበባ - አቶ ሬድዋን በአብዛኛዉ ሚዲያ ላይ የሚታወቁት ቡኖ በደሌ በሚል ስማቸዉ ነዉ።
2, አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ምክትል ሊቀመንበር ከአዲስ አበባ
3, ዶ/ር ደመላሽ መንግሥቱ ፤ በጅማ ዩንቨርስቲ የኮሚኒኬሽን እና የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ የብልፅግና ፓርቲ ደጋፊ
4, አቶ መስፍን አማን የፖለቲካ ተንታኝ ናቸዉ።
ሙሉዉን ዉይይት የድምፅ ማድመቻ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ