«ወደብ የሚጠላ የለም»፦ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
ዓርብ፣ መጋቢት 12 2017ከአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ጀምሮ ከአምስት ዐሥርተ-ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ለረዥም ዘመናት በፖለቲካል ሣይንስ መምህርነት አገልግለዋል ። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) መሥራች እና ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ። የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ ከወደብ ጉዳይ እስከ የኦሮሚያ «የሽግግር መንግሥት» ጥያቄ ብሎም ሌሎች ዐበይት ነጥቦችን በዶይቸ ቬለ የአንድ ለአንድ ዝግጅት አንስተዋል ።
ባለፉት አምሳ ዓመታት በተቃዋሚ ፖለቲከኛነት በመዝለቁ፦ «ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች አልፎ አልፎ ቢገጥሙኝም የሕዝቡን ስሜት ዕያየሁ እኔም ተመልሼ ወደ ትግል እገባለሁ» ብለዋል ። አንዳንድ አጋራት «ከዚህ በላይ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ውስጥ ሁነው ታግለው ውጤት ያመጡ» መኖራቸው በረዥም ዘመን ትግሉ ተስፋ እንዳይቆርጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ ። ለአብነት ያህልም፦ ደቡብ አፍሪቃ ይጠቅሳሉ ። «እነ ማንዴላ 27 ዓመታት ጭምር በመታሰር ነው ያን ሁሉ ውጤት ያመጡት» ያሉት ፕሮፌሰር መረራ «ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን ትግሉ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል» ሲሉ አክለዋል ።
ፓርቲያቸው ኦፌኮ፤ ከአንድ ወር ግድም በፊት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር በመሆን ይፋ ባደረጉት መግለጫ፦ በኦሮሚያ ክልል «የጋራ ሽግግር መንግሥት» ያሉት እንዲመሰረት ከተለያዩ ማኅበረሰብ አካላት አደራ መቀበላቸውን ገልጠው ነበር ። ፕሮፌሰር መረራ፦ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ጋር ፓርቲያቸው ከ20 ዓመታት በላይ ትብብር ሲያደርግ እንደቆየ ተናግረዋል ። «ብዙ ጊዜ አንናገርም እንጂ፦ ለረዥም ጊዜ ከ20 ዓመታት በላይ፤ ቢያንስ ቢያንስ ከሩብ ምእተ ዓመታት አካባቢ በተለያየ መንገድ የመተባበር ሁኔታዎች ነበሩ» ብለዋል ከዶይቸ ቬለ የአንድ ለአንድ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ።
«ላለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ደግሞ መሠረታዊ የሆኑ የኦሮሚያ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ያለንን አቋም አስቀምጠን በዚያ ላይ በጋራ ለመታገል ወስነን፤ ከዐሥር በላይ በሚሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት ተስማምተን፣ ተፈራርመን ነበር ትግሉን የቀጠልነው» ሲሉም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት አብራርተዋል ። ስለ ሁለቱ ፓርቲዎች የጋራ ግባቸው ተጠይቀውም፦ «የጋራ ግባችን፤ የእኛ ያው ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ፤ ዴሞክራቲክ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እንዲፈጠር ነው፤ ሌላ የሕዝባችን መብት እና ክብር ፤ ነጻነት ለማስመለስ እንጂ ሌላ የተለየ እንትን የለንም» ሲሉ መልሰዋል ።
ሰሞኑን ዐቢይ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የባሕር በር ጉዳይ ይነሳል ። ፓርቲያቸው የወደብ ጉዳይን በተመለከተ አቋሙ ምን እንደሆነ ተጠይቀውም፦ «ጥያቄው የተያዘበት መንገድ እና የተገባበት መንገድ አንዳንድ ጊዜ እኛ በምንፈልገው መንገድ አይሄድም እንጂ ወደብ የሚጠላ የለም» ብለዋል ።
ከፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ-መጠይቅ ከድምፅ ማዕቀፉ ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ