ወርቃማ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመናትን ያደሱት የኢትዮጲክ ቅጅዎች
ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 2017የኢትዮጲክ ቅጅዎች እንዴት የኢትዮጵያን የወርቃማ የሙዚቃ ዘመናት ዳግም አደሱት?
ፈረንሳዊዉ የሙዚቃ ተመራማሪ እና አዘጋጅ ፍራንሲስ ፋልሴቶ በተረሱ የሸክላ ቅጂዎች ላይ የነበረው ልዩ ፍቅር ዓለም በአፍሪካ ሙዚቃ ላይ የነበረውን ዕይታ ቀይሮታል። ሆኖም ይህ ከውዝግብ ነፃ አልነበረም። ፍራንሲስ ፋልሴቶ ሁሉም ነገር የተቀየረበትን አጋጣሚ አሁንም ያስታውሳል። በጎርጎረሳዉያኑ መጋቢት 1984 ዓ.ም ነበር፣ ፈረንሳዊዉ የሙዚቃ አዘጋጅ እና ተመራማሪ የተዋሰውን ረጅም የሙዚቃ ሪከርድ (LP) ሲያዳምጥ የኢትዮጵያዊው ድምፃዊ የመሐሙድ አህመድ አስገራሚ ሙዚቃዎች ክፍሉን የሞሉ። "ተገረምኩ። 'ይህ ምንድን ነው?'" ሲል ራሱን የጠየቀዉ ፋልሴቶ በሰዓታት ውስጥ የካሴት ቅጂዎችን አዘጋጅቶ ለሙዚቃ ጋዜጠኛ ጓደኞቹ ላከ። "በማግስቱ ሁሉም ደውለው፣ 'ፍራንሲስ፣ ይሄ ምንድን ነው? ከየት አገኘኸው? ድንቅ ነው!'" ሲሉ አስተያየት እንደሰጡት ፋልሴቶ መግለጹ ተመልክቷል።
ያ ፋልሴቶ የተደመመበት የተውሶ ቅጂ ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀ የኪነ-ጥበብ ትንሳኤን አስነሳ። የፋልሴቶ ተከታታይ የኢትዮጲክ ቅጅዎች (Éthiopiques)፣ በአሁኑ ወቅት 30 ጥራዞች ደርሰዋል። የኢትዮጵያን የሙዚቃ ወርቃማ ዘመን አስደናቂ ሙዚቃዎችን ጠብቆ ወደ ሆሊውድ የፊልም ማጀቢያዎች፣ ወደ ሂፕ-ሆፕ የሙዚቃ ስልት ናሙናዎች፣ እና ወደ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ድግስ መድረኮችም ወስዷቸዋል።
ሊከስም ተቃርቦ የነበረው የሙዚቃ ወርቃማ ዘመን
በጎርጎረሳዉያኑ 1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኪነ-ጥበቡ ረገድ አዲስ አበባ "የጎመራች አዲስ አበባ" ሆና ነበር። ባህላዊ የኢትዮጵያ ዜማዎች ከጃዝ፣ ሶል እና ፈንክ የሙዚቃ ስልት ጋት ተዋህደው ፍጹም አዲስ ነገር የፈጠሩባት ዓለም አቀፋዊ መዲናም ነበረች። አዲስ አበባ ላይ በዚያን ወቅት በዋናነት በታላቅዋ ብሪታንያ በዌልስ የምህንድስና ትምህርቱን አቋርጦ፣ በለንደን ትሪኒቲ ኮሌጅ እና በቦስተን በበርክሌይ የሙዚቃ ኮሌጅ የጃዝ ትምህርቱን ያጠናቀቀዉ አንጋፋዉ የሙዚቃ ደራሲ ሙላቱ አስታጥቄ ተጠቃሽ ነዉ። ሙላቱ በጎርጎረሳዉያኑ 1969 ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ፣ ከምዕራባውያን የሙዚቃ መሳሪያዎች የራሱ ከሆነዉ ልዩ ቫይብራፎን ሙዚቃ መሳርያ እና ከባለአምስት-ኖታዉ የኢትዮጵያ ክራር ጋር በማጣመር ከፍተኛ የሙዚቃ ደረጃ አላቸዉ ከሚባሉት ጋር አዋህዶታል። ውጤቱም እጅግ አስደናቂ ነበር። ሙላቱ አስታጥቄ በ"ኢትዮ-ጃዝ" ባህላዊ ሙዚቃን ከዘመናዊ ስልት ጋር በማጣመር እንደ ጥላሁን ገሠሠ ያሉ እንቁ አርቲስቶችን ጭምር ሊያካትት የቻለም ነዉ። የጥላሁን ድምጽ እጅግ በመወደዱም ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሙዚቃ ድግስ አቅርቧል። እንደ አምሀ ሪከርድስ ያሉ የግል የቅጅ ድርጅቶችም ይህንን የለውጥ ዘመን ቀርፀው አስቀርተውታል። እነዚህ የሙዚቃ የቅጅ ድርጅቶች ከጎርጎረሳዉያኑ 1969 እስከ 1975 መካከል ባለው ጊዜም 103 የሚሆኑ ነጠላ ዜማዎችን አውጥተዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 1974 በሶቪየት ህብረት የሚደጋፈው የደርግ መንግሥት የኃይለሥላሴን መንግሥት ዙፋናዊ አስተዳደር ከገረሰሰ በኋላ፤ በሃገሪቱ የሰዓት እላፊ ገደቦች ተጣሉ፤ በቅድመ ምርመራ «ሳንሱር» ምክንያት የኢትዮጵያ አስደሳች የምሽት ህይወት በአንድ ጀምበር ድርግም ብሎ ጠፋ። በርካታ ሙዚቀኞችም ተሰደዱ። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ወርቃማው ዘመን ለዘላለሙ ያከተመ ይመስልም ነበር።
ፈረንሳዊው አዳኝ
ከጎርጎረሳዉያኑ 1984 ቱ የደርግ አብዮት በኋላ ፈረንሳዊዉ የሙዚቃ ተመራማሪ እና አዘጋጅ ፍራንሲስ ፋልሴቶ በጎርጎረሳዉያኑ 1985 አርቲስት መሐሙድ አህመድን ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ ነበር። ፋልሴቶ "ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሸክላዎችን መሰብሰብ ስጀምር፣ እኔ ብቻ ነበርኩ" ሲል ያስታውሳል። "ያኔ የካሴቶች ጊዜ ነበር፣ ህገ-ወጥ ቅጂም መላዉን የሙዚቃ ሥራ ማጥፋት የጀመረበት ጊዜ ነበር።" ሲል ፋልሴቶ ተናግሯል። እንደ አምሀ እሸቴ ካሉ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አዘጋጆች ጋር በመስራት ፋልሴቶ የወርቃማው ዘመን ቅጂ መብቶችን ማግኘት ጀመረ። በጎርጎረሳዉያኑ 1997 ከቡዳ ሙዚቃ ጋር በመሆን የኢትዮጲክ ቅኝቶችን ተከታታይ ቅጂ አስጀመረ። ፕሮጀክቱ መሐሙድ አህመድ፣ ሙላቱ አስታጥቄ እና ጥላሁን ገሠሠን የመሳሰሉ አርቲስቶችን ለአድማጮች በማስተዋወቅ ኢትዮጵያን በዓለም ሙዚቃ ካርታ ላይ አስቀምጧታል።
ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ መምጣት
ሁለት አጋጣሚዎች የኢትዮጲክ ቅኝቶችን ከጥቂት የሙዚቃ ሰዎች ጉዳይ በማውጣት ወደ ባህላዊ ክስተትነት ቀይረዋቸዋል። በመጀመሪያ፣ ፊልም ሰሪው ጂም ጃርሙሽ የሙላቱ አስታጥቄን ሙዚቃ ከሰማ በኋላ "Broken Flowers" የተሰኘ በጎርጎረሳዉያኑ 2005 የወጣ ፌልም ማጀቢያ በማድረግ ኢትዮ-ጃዝን በሚሊዮኖች ለሚቆጠር የዓለም ህዝብ አስተዋወቀ።
"የሙላቱ አስታጥቄን ሙዚቃ ምናልባት ከሰባት ዓመታት በፊት ነው የሰማሁት፣ እናም ተደመምኩ" ሲል ጃርሙሽ ገልጿል። "በጣም የሚያምር እና ለማጀቢያ የሚሆን ነው።" ሲልም ጃርሙሽ አክሏል። ሁለተኛው ትልቅ ለውጥ በሂፕ-ሆፕ የሙዚቃ ስልት በኩል የመጣ ነው። ከናስ እስከ ካንዬ ዌስት ያሉ የሙዚቃ አዘጋጆች የኢትዮጲክ እትሞችን መጠቀም ጀመሩ። የናስ እና ዳሚያን ማርሌይ በጎርጎረሳዉያኑ 2010 ያወጡት ዘፈን "As We Enter" የሙላቱን "የገሌ ትዘታ" የተሰኘዉን ሙዚቃ በግልፅ ያሳየ ነዉ። በዚህም እንደ ማድሊብ ያሉ አዘጋጆች በኢትዮጵያ ቅኝቶች ተመስጠው ነበር።
ዓለማቀፍ የአዝማሪ ጉባኤ ፣ በጀርመን ሂልደስ ሃይም
አዲሱ ወጀብ
በመላው ዓለም ያሉ ሙዚቀኞች ኢትዮጲክ ቅጂዎችን እንደ መሰረት አድርገው ይገልጻሉ። የቦስተኑ ደቦ ባንድ እና የኒው ዮርኩ አንበሳ ኦርኬስትራ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ክህሎቶችን እና ዜማዎችን የሚጫወቱ ሲሆን፣ ከለንደን እስከ ሜልበርን ያሉ ባንዶችም የኢትዮጵያ ድምጾችን መነሻ ያደረጉ ሙዚቃ ያሳትማሉ።
የወርቃማው ዘመን ሙዚቀኞችም አዲስ ህይወትን አግኝተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥራዎቹን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያቀርብ የነበረዉ መሐሙድ አህመድ አሁን በእድሜ ምክንያት ከመድረክ ወርዷል። የኪቦርድ ተጫዋቹ ኃይሉ መርጊያ ደግሞ ከጎርጎረሳዉያኑ 2013 ወዲህ ወደ ሙዚቃዉ መድረክ ተመልሷል።
"ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን የሚመጣው ምላሽ በአብዛኛው ጥሩ እና የሚያበረታቱ ናቸዉ" ሲል ፋልሴቶ ይናገራል። "በተለይ ትዝታዎቻቸውን ኢሜል የሚያደርጉልኝ ኢትዮጵያውያን ልቤን ይነኩኛል። በ50ዎቹ እና 60ዎቹ ዘመናት ውስጥ ታዳጊዎች የነበሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ብዙውን ጊዜ በውጭ አገር ያደጉ ልጆችም የወላጆቻቸውን ዘመን ሙዚቃ በመስማት ይደነቃሉ።" ሲል ፋልሴቶ ተናግሯል።
ባህላዊ ባለቤትነት
ስኬት ያለ ውዝግብ አይመጣም። አንዳንድ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ፋልሴቶን ያለ በቂ ካሳ ከሥራዎቻቸው ትርፍ እያገኘ ነው ሲሉ ከሰውታል። ታዋቂው የሳክስፎን ተጫዋች ጌታቸው መኩሪያ "ሙዚቃችንን በዓለም ዙሪያ እንዲታወቅ አስተዋፅዖ ቢያደርግም፣ በሌላ በኩል ደግሞ እኛን ተጠቅሞብናል።" ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፦
ፋልሴቶ እንደዚህ ያሉትን ክሶች የኢትዮጵያን የቅጂ መብት ችግሮች በመጥቀስ ይሞግታል። "በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የቅጂ መብት ጥበቃ እስከሌለ ድረስ ይህ ችግር መቀጠሉ አይቀሬ ነው" ባይ ነዉ። ፋልሴቶ የኢትዮጲክ የሲዲ ቅጅዎችን በኢትዮጵያ ውስጥ ጭምር የማከፋፈል ተደጋጋሚ ያልተሳኩ ሙከራዎችንም አስታዉሷል። እነዚህ፣ ባለመብቶች በሚፈጽሙት ክፍያዎች ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት ሳይተገበሩ የቀሩ ናቸው፤ ውጥረቱ ስለ ባህላዊ ባለቤትነት ሰፋ ያሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል ሲል ይገልፃል። አንድ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ፋልሴቶን በቀጥታ "እንዴት አንተ ፈረንጅ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ዙሪያ ታስተዋውቃለህ?" ሲል ጠይቆታል። የፋልሴቶ ምላሽ "እኔ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ዙሪያ እያስተዋወቅኩ እናንተ ኢትዮጵያውያን እንዴት እና ለምን እንደማታስተውቁ ማወቅ የለባችሁም?" ሲል በጥያቄ መልስ መስጠቱ ተዘግቧል።
ቋሚ ቅርስ
የተወሰኑ ውጥረቶች ቢኖሩም፣ የኢትዮጲክ ቅጅዎች በማያሻማ ሁኔታ ግባቸውን አሳክተዋል። ይህም ዓለምን በአፍሪካ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ተነጥሎ ከቀረው ክፍል ጋር ማስተዋወቅ ነው። የኢትዮጵያ ሙዚቃ አዳዲስ አድማጮችን ማግኘት እና አዳዲስ ሙዚቀኞችን ማነሳሳቱን ቀጥሏል። ይህ ታሪክ በማይገመቱ መሪዎች አማካኝነት እንዴት የባህል ማንሰራራት ሊከሰት እንደሚችል ያሳያል። አንድ ፈረንሳዊ የሙዚቃ አፍቃሪ እና ተመራማሪ የአጋጣሚ ክስተት ተቀብሮ ሊቀር ይችል የነበረን የሙዚቃ ቅርስ መልሶ ማስነሳቱም እዉን ነዉ። ይህ የባህል አድናቆት ነው ወይስ ወረራ የሚለው የሚወሰነው በየግለሰቡ አመለካከት ላይ ነው።
የማይካደው ሀቅ ግን ሙዚቃው ራሱ ነው። ከአራት አስርት ዓመታት በፊት ፋልሴቶን የሳቡት እነዚያ አስገራሚ ዜማዎች አዳዲስ አድማጮችን ማስደነቅ ቀጥለዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 1974 በድንገት ያበቃው ወርቃማ ዘመን እንደ ታሪካዊ ቅርሶች ብቻ ሳይሆን እንደ ቋሚ ቅርስ እንደገና እየኖረ ነው። የ 81 ዓመቱ አንጋፋዉ የሙዚቃ ደራሲ ሙላቱ አስታጥቄ እንዳለው፣ "እኔ ለገንዘብ ሰርቼ አላውቅም። ዋናው ሃሳብ፣ ይህን ጥበብ በዓለም ላይ እንዴት ማስተዋወቅ እችላለሁ የሚለው ነዉ።" በኢትዮጲክ ቅጅዎች በኩል፣ የጥበብ ዓለምን አዳርሶ መልኩ ተለውጦም ቢሆን ዳግም ወደ ቤቱ ተመልሷል፣ አሁንም ኢትዮጵያዊነቱ አያጠራጥርም።
ካሊድ አብዱኬ
አዜብ ታደሰ