ኮሮና ተሐዋሲን የመዋጋት ተስፋ
ዓርብ፣ መጋቢት 11 2012ኮቪድ 19 ማለትም ኮሮና ተሐዋሲ መዛመቱን ባያቆምም በመላው ዓለም በበሽታው ከተያዙት መካከል 80,000 የሚሆኑት ከህመሙ ማገገማቸው ተገልጿል። የዳኑት ሰዎች በደማቸው ውስጥ ኮሮና ተሐዋሲን መዋጋት የሚችል በተፈጥሮ ለየት ያለ በሽታ መከላከያ እንዳላቸው ተደርሶበታል። በእነሱ ደም ውስጥ የተገኘው ተሐዋሲውን መቋቋም የቻለው የተፈጥሮ ቅመም በኮቪድ 19 ለተያዙ ታማሚዎች በክትባት መልክ ቢሰጥ በሽታውን መከላከል የሚያስችል መድኃኒት ተወጉ ማለት ነው። በመሠረቱ ይህ ክትባት አይደለም፤ የታማሚው ሰውነት በራሱ የበሽታ መከላከያ ስላላመረተ የተደረገ ድጋፍ ብቻ ነው። ፓሲቭ ቫክሲኔሽን ይሉታል፤ እንዲህ ያለው ህክምና ጥቅም እና ጉዳት፤ ጥቅሙ ግልፅ ነው እንዲህ ባለው ህመም በመጠቃት ጊዜ ሰውነት ወዲያው ያዘጋጀው የበሽታ መከላከያ አቅም ባለመኖሩ የገጠመውን ተሐዋሲ ለመዋጋት ከሌላ ሰው የሚሰጠው ሰውነት በሽታውን ለመከላከል እንዲችል ያግዛል።
ጉዳቱ ደግሞ ከሌላ ሰው ተወስዶ የሚሰጠው በሽታውን መዋጋት የሚያስችለው የተፈጥሮ ቅመም ግፋ ቢል በወራት ወይም በሳምንታት ውስጥ አገልግሎቱን ያቆማል። በዚህ መልኩ ሰውነት የሚያገኘው ርዳታ ረዥም ጊዜያትን የሚያዛልቅ አይደለም። የተፈጥሮ የበሽታ መከላከል አቅም በአግባቡ ባለመደራጀቱ እንደውም ሰውነት በቀጣይ ለሌላ ተሐዋሲ ይጋለጣል። ይህ የህክምና ዘዴ በሳይንሱ ዘርፍ ፓሲቭ ቫክሲኔሽን ይባላል። የህክምና ዘዴውን ጀርመናዊው የበሽታ መከላከያ ምርምር ባለሙያ ኤሚል ፎን ቤህሪንግ ነው፤ በጎርጎሪዮሳዊው 1890ዓ,ም ያስተዋወቀው። በወቅቱ ኤሚል ፎን ቤህሪንግ ይህን የተጠቀመው አደገኛ የሆነ የጉሮሮr በሽታን ለማከም ነበር።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይህ ጉሮሮን ከውስጥ አሳብጦ መተንፈሻ በማሳጣት የሚያሰቃየው በሽታ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ሕይወት መቀጠፍ ዋና ምክንያት ነበር። በዚሁ የዘመንቀመር በ1901 ላይ ፎን ቤህሪንግ ለዚህ ግኝቱ በህክምና የኖቤል ተሸላሚ ሆነ። ከሰዎች ደም ውስጥ በሽታን መከላከል የሚያስችሉትን ቅመሞች በመውሰድ በሠራው መድኃኒትም በወቅቱ ይህን ከባድ የጉሮሮ ህመምና ቴታነስን መፈወስ በማስቻሉ በዘመኑ የፕረስ ውጤቶች «የልጆች አዳኝ» የሚል ዝናን ሁሉ አተረፈ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም «የወታደሮች ታዳጊ» ተባለ።
ለወፍ ኢንፉልዌንዛ እና ለኢቦላ መከላከያነት ጥቅም ላይ የዋለው ይህን የህክምና ዘዴ የዛሬ 6 ዓመት በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የኢቦላ ወረርሽኝ በቀሰቀሰበት ጊዜ ሥራ ላይ ውሏል። ከሁለት ዓመታት በፊትም በተመሳሳይ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በኢቦላ ወረርሽኝ ስትቸገርም ከተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ የተቀመመው መድኃኒት የተዋሐሲው ብዙ እንዳይሰራጭ አግዟል። ይህም በበሽታው ሊሞት የሚችለውን ሰው ቁጥር 30 በመቶ መቀነስ አስችሏል። አሁንም ዓለም የገጠማትን ኮቪድ 19 ተሐዋሲ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ተመራማሪዎች ይህንን ዘዴ ለመጠቀም ፈልገዋል። ባለፈው የካቲት ወር ሻንጋይ ቻይና ውስጥ አንድ በልዩ ሁኔታ እንዲህ ያለውን ህክምና የሚሰጥ ክልኒክ አዘጋግቷል። የጃፓኑ ታኪዳ የተሰኘው የመድኃኒት ፋብሪካ በኮሮና ተሐዋሲ ተይዘው ከዳኑ ሰዎች ደም ውስጥ በተፈጥሮ በሽታ ተከላካይ ቅመሞችን በመውሰድ መድኃኒት ለመሥራት አቅዷል። የመድኃኒት ፋብሪካው ከዚህ ቀደምም በሽታ የመከላከል አቅማቸው ለተዳከመ ህሙማን የሚረዳ መድኃኒት አምርቷል። ውጤቱም ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ተመራማሪዎች የትኛው በሽታ ተከላካይ የተፈጥሮ ቅመም አዲሱን ኮሮና ተሐዋሲ የተሻለ ለመዋጋት ያስችላል የሚል ምርምር ማካሄድ አይጠበቅባቸውም። እናም ይህ ስልት ውጤታማ ይመስላል። ምክንያቱም የሚወስደው ጊዜ አጭር ከመሆኑ ሌላ፤ ሌላ ተሐዋሲ ባለመኖሩ አስተማማኝ ነው። ይህም ጊዜን ይቆጥባል። መድኃኒቱ በመዘጋጀቱም የሙከራ ጊዜ አስፈላጊ አይሆንም። እናም በቅርቡ በሽታውን መቋቋም የሚያስችል ህክምና ይገኝ ይሆናል። የካሊፎርኒያው መድኃኒት አምራች ፋብሪካ በዚህ ስልት ያመረተውን መድኃኒት በጎርጎሪዮሳዊው 2003 ዓ,ም የተቀሰቀሰውን ሳርስ የተሰኘ ተሐዋሲ ማከም አስችሏል። ለመሆኑ ይህ ከደም ውስጥ የሚገኝ ቅመም ክትባትን ይተካል ማለት ይቻላል?
ደግነቱ መድኃኒት እና ክትባት የማዘጋጀቱ ሂደት በተጓዳኝ ይሄዳሉ። አሁን ባፋጣኝ በተለይ ለጉዳት ለተጋለጡ ሰዎች ይህ ከደም የሚገኘው በሽታን መቋቋም የሚያስችለውን ቅምም ህክምና ቶሎ ማቅረብ ይቻላል። በብዛትም ይመረታል። በኢቦላ ምክንያት ሊሞት የሚችለው ሕዝብ ቁጥር የቀነሰውም በዚሁ ዘዴ ነው። የኮሮና ተሐዋሲን ተጋቦት በወጉ ለመቀነስ ግን ክትባት ማግኘት ግድ ነው። ይህም በከፍተኛ ትኩረት በመላው ዓለም እየተደረገ የሚገኝ ጥረት ነው።
ሸዋዬ ለገሰ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ