በፈረንሳይ በተሽከርካሪ ውስጥ 15 ኤርትራውያን የሰውነት ሙቀታቸው በአደገኛ ሁኔታ ቀንሶ ተገኙ
እሑድ፣ ነሐሴ 4 2017ኤርትራውያን ስደተኞች ከፈረንሳይ ወደ ብሪታኒያ የቀዘቀዙ አትክልቶች ጭኖ በመጓዝ ላይ በነበረ ተሽከርካሪ ውስጥ የሰውነት ሙቀታቸው በአደገኛ ሁኔታ ቀንሶ ተገኙ። ትላንት ቅዳሜ በሰሜናዊ ፈረንሳይ ፓስ ደ ካሊ ክፍለ ግዛት በሚገኝ የፍጥነት አውራ ጎዳና መኪናው ለእረፍት ሲቆም አሽከርካሪው ድምጽ በመስማቱ 15 ሰዎች ተደብቀው መገኘታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የፈረንሳይ የሕክምና ባለሙያዎች የስደተኞቹ የሰውነት የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የሕክምና እርዳታ አድርገዋል። ክርስቲያን ቬዴላጎ የተባሉ የአካባቢው አስተዳደር ባለሥልጣን የስደተኞቹ የሰውነት የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ በተሽከርካሪው ውስጥ ለሰዓታት መቆየታቸውን እንደሚጠቁም ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
ከስደተኞቹ መካከል አራቱ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ሌሎች አራት ደግሞ አዳጊ በመሆናቸው ክብካቤ ለሚያደርግ ማህበር ተላልፈው ተሰጥተዋል። ከስደተኞቹ መካከል ሁለት ሴቶች ይገኙበታል። አብዛኞቹ ከፈረንሳይ ለቀው እንዲወጡ ይፋዊ ትዕዛዝ የተሰጣቸው እንደሆኑ ዘገባው ይጠቁማል።
የቀዘቀዙ አትክልቶች በማጓጓዝ ላይ የነበረው ሞሮኳዊ አሽከርካሪ ምርመራ እየተደረገበት እንዳልሆነ ክርስቲያን ቬዴላጎ ገልጸዋል። በሰሜናዊ ፈረንሳይ ወደቦች ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ ቢሆንም ስደተኞች ወደ ብሪታኒያ የሚያመሩ ተሽከርካሪዎችን ለመሣፈር ይሞክራሉ። ይሁንና በስደተኞች ዘንድ ተመራጩ መንገድ በትናንሽ ጀልባዎች ባሕር አቋርጦ ከፈረንሳይ ወደ ብሪታኒያ መግባት ነው።
ካለፈው ጥር ወዲህ ከ25,000 በላይ ሰዎች ባህር አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል። በፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት “የእንግሊዝ ቻናል” ተብሎ የሚጠራውን ባሕር ለማቋረጥ ሲሞክሩ ባለፉት ስምንት ገደማ ወራት ብቻ 18 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እሸቴ በቀለ
አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር