ከዱባዩ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ምን ተገኘ?
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2016«ሁሉም ዓይኖች ከቅሪተ አጽም የኃይል ምንጮችን መጠቀም ማቆም ወይም መቀነስን በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ናቸው። አብዛኞቹ ሃገራት የCOP ፕሬዝደንቱ ትናንት ምሽት ይፋ ያደረጉትን ዓለም ይህን በማቆም ወይም በመቀነስ በኩል ትርጉም ያለው መንገድ መጀመሩን የሚያመላክቱ ዝርዝሮች እንዲኖሩት የጠበቁ ይመስለኛል። በተቃራኒው ጽሑፉ ለሃገራት ጠቃሚ የሆኑ በርካታ አማራጮችን ይዟል፤ ሆኖም ግን ብዙዎቹ ሃገራት እንደጠበቁት ጠንካራ አይደለም።» የሚሉት በተመድ የልማት መርሃግብር የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ካሲ ፍሊን ናቸው። ዛሬ ከቀትር በኋላ ነው፤ ማክሰኞ እንደሚጠናቀቅ የታሰበው ዱባይ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የደረሰበትን ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
13ተኛ ቀኑን የያዘው COP 28 ጉባኤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ቢነጋገርም ለከባቢ አየር ብክለት ዋነኛ መንስኤ የሆኑ ሙቀት አማቂ ጋዞች ምኝጭ የሆኑ ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም ላይ የጋራ መግባቢያ ላይ ለመድረስ መቸገሩ እየተነገረ ነው። እንዲያም ሆኖ ከጉባኤው የተገኙ አዎንታዊ ውጤቶች እንዳሉም የሚገልጹ አሉ።
በዱባይ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የመጨረሻ ቀናት
ከመቶ በላይ ሃገራትእስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓም ታዳሽ የኃይል ምንጭ አጠቃቀማቸውን ለማፋጠን መስማማታቸውን ከጉባኤው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። እጅግ አወዛጋቢ የሆነው ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን መጠቀምን ሙሉ ለሙሉ የማቆም ወይም የመቀነስ ሃሳብ ጉባኤው እንደታሰበው በአንድ ድምጽ የጋራ አቋም ላይ ለመድረስ እንቅፋት ሆኗል። በጉባኤው መነሻ ተግባራዊነቱ እንዴት እንደሆነ መነጋገሪያ እንደሚሆን የተገለጸው ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ በተካሄደው ተመሳሳይ ጉባኤ ሃገራት የተስማሙበት የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ይመለከታል። ቀዳሚዎቹም የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም የማስፋፋት ዕቅድ ናቸው። ለዚህም ነው ከባቢ አየርን ለበከሉት ሙቀት አማቂ ጋዞች መገኛ የሆኑት ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን አጠቃቀም ማስቆም ወይም በከፍተኛ መጠን መቀነስ የሚለው ሃሳብ በዚህ ጉባኤ ዋነኛ ትኩረት የሆነው። በጉባኤው መክፈቻ ዕለት የነዳጅ ኩባንያዎችን እና አምራች ሃገራትን ሲያግባቡ እንደከረሙ የተናገሩት የአስተናጋጇ ሀገር አረብ ኤሜሬት የነዳጅ ኩባንያ ኃላፊ እና የዘንድሮው ጉባኤ የCOP 28 ፕሬዝደንት ሱልጣን አል ጃቢር፤ ዱባይ ላይ ታሪካዊው ስምምነት እንዲፈጸም ግፊት ማድረግ መቀጠላቸው ተሰምቷል። ትናንት ምሽት የስምምነቱን ሃሳብ ረቂቅ ለተሳታፊ ሃገራት ከበተኑ በኋላ በአየር ንብረት ለውጡ ተጽዕኖ የተጎዱ ሃገራት በአንድ ወገን፤ ምዕራባውያን ሃገራት በሌላው በኩል ሆነው ለጋራ ስምምነቱ የጠበቁትን እንዳላገኙ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። የCOP 28 ዋና ዳይሬክተር ማጂድ አል ስዋይዲ ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቆዎች በሰጡት ማብራሪያ የቀረበው ባለ 21 ገጽ ረቂቅ ሰነድ የውይይት መነሻ እንጂ የመጨረሻው እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። የተፈጠረው የሃሳብ መለያየትም ከስምምነት ለመድረስ የሂደቱ አካል ነው ባይ ናቸው።
«ሰነዱን ይፋ ስናደርግ ሃሳቦች እንደሚለያዩ እናውቅ ነበር፤ ሆኖም ግን ለእያንዳንዱ ሀገር ቀይ መስመር የቱ ነው የሚለውን ግን አናውቅምም። የጽሑፉን የመጀመሪያ ረቂቅ በማውጣትችን የየራሳቸውን ቀይ መስመሮች የያዙ ወገኖች በፍጥነት ወደ እኛ መጡ። ዋናው ጉዳይ የጋራ መግባባት ነው፤ በሂደቱ ይህን የሚያደናቅፍ ቀመር አንፈልግም። ወገኖች ወደ አንድነት እንዲመጡ እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም ተጨባጭ ወደሆነው ነገር መመለስ እንፈልጋለን። ይኽ ደግሞ 1,5 ዲግሪን ማሳካት ነው።»
ሰነዱ የተመለከቱት የየሃገራት ወኪል ልዑካን፤ የአየር ንብረት ባለሙያዎች እንዲሁም ተሟጋቾች በውስጡ የተካተተው ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም እና ምርት መቀነስ ብቻ ነው በሚል አጥብቀው ተችተዋል። እንዲህ ያሉትን የኃይል ምጮች መጠቀም ማቆም የሚለው ሃሳብ በተለይ የነዳጅ አምራች ሃገራት እና ኩባንያዎች የሚቀበሉት እንዳልሆነ እየታየ ነው። በነዳጅ ሃብት አቅርቦት ከታወቁት ሃገራት አንዷ የጉባኤው አስተናጋጅ አረብ ኤሜሬት መሆኗና ጉዳዩም እልባት ያገኛል በሚል ከመነሻው የሰጠችው ተስፋ ለተሳታፊዎቹ እንቆቅልሽ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ከCOP 28 ምን ተገኘ?
ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ ሃገራት በተናጠል ከዓመታት በፊት ቃል የገቡትን ምን ያህል ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ በየጊዜው ጥያቄዎች ይቀርቡበታል። በጉባኤው የተሳተፉት በአፍሪቃ የምግብ ይዞታውን ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራት ስብስብ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ሚሊየን በላይ ይህን በተመለከተም በየደረጃው በተለያየ መልኩ ሲካሄዱ በነገሩ ውይይቶች አማካኝነት ዳብሮ የመጣ ሰነድ መኖሩን ያመለክታሉ። በዘንድሮው ጉባኤውም በጉዳዩ የጋራ መግባባት እንዲኖር ይጠበቃል ባይ ናቸው።
ምንም እንኳን የብዙዎች ትኩረት በዚህ ላይ ቢሆንም ጉባኤው ያሳካቸው እና በአዎንታዊነት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ስምምነቶች ከዱባዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤመገኘታቸውንም ዶክተር ሚሊየን አንስተዋል። የታዳሽ ኃይል ምንጮችን አጠቃቀም ማስፋፋት፤ እንዲሁም የምግብ ሥርአትን እና እርሻን የጉባኤው የትኩረት ማዕከል ለማድረግ በቀረበው ሃሳብ ላይ ከመቶ በላይ ሃገራት በመስማማት መፈረማቸውንም ነግረውናል። በአየር ንብረት ለውጡ መዘዝ ምሥራቅ አፍሪቃን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው የሚከሰተው ድርቅ እና ጎርፍ የበርካታ ማኅበረሰቦችን የምግብ ዋስትና ማሳጣቱ አነጋጋሪ ሆኗል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው የዓለም የምግብ መርሃግብር WFP ከዚህ አኳያ ትኩረት እንዲሰጠውና ሃገራት ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት የየበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ስለካርቦን ዳይኦክሳይድ ቢነገርም ከእርሻና ከብት እርባታ አካባቢ የሚወጣው ሚቴይን የተባለው አደገኛ ጋዝ እስከጎርጎሪዮሳዊው 2030 ለመቀነስ ከስምምነት ተደርሷል። ገንዘብ መዋጣቱን የገለጹን ዶክተር ሚሊየን የኤሜሬት የምግብ ሥርዓት ስምምነት መባሉንም ተናግረዋል።
ከጉባኤው ጀርባ ያሉ የመሰባሰቢያ ምክንያቶች
በሌላ በኩል በየዓመቱ ለቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ የፍላጎት ፉክክርና የተለያዩ ስልቶች የሚታይባቸው የተለዩ ፕሮጀክቶች መገለጫም ነው። ዶክተር ሚሊየን ዱባይ ላይ እንዳስተዋሉት መንግሥታት ጠንካራ ውሳኔ እንዳይወስኑ የሚያባብሉ ቡድኖች፤ እንዲሁም የካርቦን ሽያጭን በሚመለከት የሚደረጉ ቅስቀሳዎችና ስምምነቶች ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የቀጣዩ ጉባኤ አስተናጋጅ ሀገር ታውቋል። በነዳጅ ሃብት ከበለጸጉት ሃገራት አንዷ አዘርባጃን COP29 ጉባኤን ለማስተናገድ ይኹንታ አግኝታለች። በየዓመቱ ብዙ ተስፋ ተድርጎ ውጤቱ እጅግም እየሆነ ዓመታት የዘለቀው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ፤ ከ60 እና 70 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች፤ በሚጓጓዙበት ሂደት የሚፈጠረው የከባቢ አየር ብክለት ይጠናል በሚል ይተቻል። ዶክተር ሚሊየን ከዓለም አቀፉ መድረክ ብዙም ከማይጠብቁ ተሳታፊዎች አንዱ መሆናቸውን በመግለጽ የተሳታፊው ቁጥር የሚበዛበት ምክንያት ከተለያዩ ሃገራት በቀላሉ የማይገኙ ባለሥልጣናት እና ባለሙያዎች የሚገኙበት፤ ልዩ ልዩ ትስስሮች በመፈጠሩ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይኽ ማለት ግን ጉባኤው አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ፤ እንዲህ ያለው ዓለም አቀፍ መድረክ ባይኖር ኖሮ አሳሳቢው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የመንግሥታትን ትኩረት ማግኘት እንደማይችል የተፈጥሮ ደህነት ተሟጋቹ አጽንኦት ሰጥተዋል። ጉባኤው እስካሁን ያልተጠናቀቀ ሲሆን ከቅሪት አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን አጠቃቀምን የተመለከተው ሃሳብ ከነዳጅ አምራች የአረብ ሃገራት ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠመው የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ ነው። ች ስለጉባኤው ሃሳባቸውን ያካፈሉንን የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ ዶክተር ሚሊየን በላይን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ