ከኪረሙ ሸሽተው አማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ግብር ክፈሉ ተባልን አሉ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 7 2017
ከ5 ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል በተከሰተ የፀጥታ ችግር አካባቢያቸውን ለቀው የተሰደዱ እና በአማራ ክልል የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተቃጥሎ ጥለነው ለመጣነው ቤትና ለአመታት ሳይታረስ ለቆየ የእርሻ መሬት ግብር ክፍሉ እየተባልን ነው ሲሉበጃራ፣ ጃሪ ቱርክ ካምፕ መካነ ኢየሱስ እና ሌሎች የመጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ተናገሩ፡፡በጃራ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚኖረው የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ በምስራቅ ወለጋ ሆሮ ጉድሩ ጃርቴ ወረዳ የሚገኝ መሬቴ ነገ ሰላም ቢመጣ አርሰዋለሁ ስል ከተሰጠኝ እርዳታ ላይ ቀንሼ ግብር ከፈልኩ ይላል፡፡ ‹‹መሬቱ ብቻ ነው ያለው፤ ቤቱ ሁሉ ተቃጥሏል ሀብት ንብረቱ ወድሟል መሬቱን እንኳን ለልጆቼ ይትረፍ ስል ከተሰጠኝ እርዳታ ከእለት ጉርሻየ ላይ ቀንሼ 4100 ብር ከፍያለሁ፡፡ ››
በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን ከ60,000 የሚልቁ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ የጸጥታ ስጋት የመኖሪያ ቀያቸውን ትተው የተሰደዱ ናቸው፡፡ ተፈናቃዮቹ እንደሚገልፁት አሁን ያለባችሁን ግብር የማትከፍሉ ከሆነ ለሌሎች መሬታችሁን እናስተላልፋለን እያሉ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ፣ ጃርቴጋ፣ጃርቴ ወረዳ ነው የምኖረው፡፡ እዚህ በብዛት የጃርቴ እና ያሙሩ ወረዳ ነው ያለው፤ ክፈሉ የቤት ጣራም ግብርም እያሉን ነው፡፡ መጥታችሁ ክፍሉ ለሌላ እንመራዋለን ብለውናል፡፡››
አሁንበመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እያለን ለምንበላውና ለምንጠጣው የመንግስት እጅን የምንጠብቅ ሁነን ሳለን ምንም ግብር የመክፈል አቅም የሌለን በመሆኑ መንግስት ችግራችንን ሊረዳ ይገባል ሲሉ ተፈናቃዮቹ ይገልፃሉ፡፡
‹‹እኛ እዛ ላለ መሬት ግብር መክፈል ሳይሆን የምንበላው አጥተናል፤ ከመጣን 5 ዓመት ሆኖናል በወር 15 ኪሎ እህል ታገኛላችሁ የተባለው ፓኬጁን ያሟላ አይደለም፡፡ እንደው መክፈሉ ህጋዊ ሆኖ ቢገኝ እንኳን የመክፈል አቅም የለንም፡፡ መንግስት እዚህ ላይ የሰራው እዚያ ያለው የመንግስት አካል ነው ማስታወቂያ የሚያወጣው፡፡››
አካባቢው ሰላም ቢሆን እና ለእኛም የመኖር ዋስትና ቢሰጠን አሁን በዚህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ መቆየት አንፈልግም የሚሉት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ ባለንበት ደረጃ ግን እንኳን ግብር ልንከፍል ቀርቶ ለልጆቻችን ምግብ መመገብ አቅቶናል ይላሉ፡፡
‹‹የለንም ምንም ሽሮ የምንገዛበት የለንም በቃሪያ ነው የምንበላው እንኳን ግብር ልንከፍል ለልጆቻችን እያለቀሱ በሽሮ ወጥ ስጡን እንጀራ እያሉ ምንም ለማቅረብ አልቻልንም ስንት ሀገር ሄደን ድንጋይ እየፈለጥን ነው የምንኖረው፡፡››
በምስራቅ ወለጋ ዞን ጃርቴ፣ኡሙሩ እና ኬረሙ ወረዳ ኗሪ እንደሆኑ እና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እነዚህ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ነገ መሬታችንን ላለማጣት ስንል አቅም ያለው ብር እየላከ፣ ግብር እየከፈለ ቢሆንም አብዛኛው ተፈናቃይ ግን ለተቃጠለ ቤትና የእርሻ መሬት ብር መክፈል አንችልም ብሏል፡፡
‹‹ክፈሉ ካልከፈላችሁ ለወጣቶች እንመረዋለን ይላሉ፡፡ የመሬት ከተማ ቤት ያላችሁ ደግሞ የቤት ግብር እኛ ደግሞ የመክፈል አቅሙ የለንም፤ ጭንቅላታችን ተበጠበጠብን፡፡››
በዚህ የሀገር ውስጥተፈናቃዮች ቅሬታዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የምስራቅ ወለጋ ዞን ኬረሙ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ፈቃዱ ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም መንገድ ላይ ነኝ በማለት ምላሽ አልሰጡንም፡፡
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ