ከተገደሉ 1 ዓመት ቢደፍንም ፍትሐቸው የዘገየው ፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2017ፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ በትውልድ ቀዬያቸው አምና ከተገደሉ ዛሬ አንድ ዓመት ደፍኗል ። በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ድርጅት ስር ከፍተኛ ዕውቅና ያተረፉትና ስመጥር የነበሩት ፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ ተገድለው የተገኙት አምና ሚያዝያ 2 ነበር ። ሚያዚያ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ለሚያዚያ 2 አጥቢያ በትውልድ መንደራቸው መቂ ከተማ ተገድለው ተጥለው የተገኙት ፖለቲከኛ ግድያ ዛሬም ድረስ ፍትሕ ሳይረጋገጥ ቆይቷል ። አጥፊው ላይም ፍርድ መተላለፉ አልተሰማም ።
ፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ አምና ልክ የዛሬ ዓመት እስከተገደሉበት እለት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ እስር ላይ የነበሩት ፖለቲከኛ በቴ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራርም ጋር በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት ለሕይወታቸው በሚያሰጋ ደረጃ በጠና ታመው ነበር ከእስር የተፈቱት፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ ሐሳባቸውን ሲያጋሩ የነበሩት ፖለቲከኛው ልክ የዛሬ ዓመት ሲገደሉ የእሳቸው ግድያ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የሚገገኙትን ሌሎችንም ያስደነገጠ ክስተት ነበር፡፡
ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተው ከተለቀቁ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፖለቲከኞች አንዱ የነበሩት ፖለቲከኛ ለሚ ቤኛ አቶ በቴን የፖለቲካ አጋር ብቻ ሳይሆን እንደ ጓደኛም በቅርበት ያውቋቸዋል፡፡ “አቶ በቴ በጣም ታዋቂ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ለኔ ደግሞ ጓደኛም አብሮአደግም ነበር፡፡ አብረን እንደመማራችን የአቶ በቴን ስብዕና በጣም ነው የማውቀው፡፡ ለእውነት፣ ፍትህ እና ነጻነት የሚቆም ፤የሰው ልጅ በማንነቱ እንዳይገፋ የሚታገል ሰው ነበር፡፡ ወደ ፖለቲካ ድርጅቱም ስመጣ ይህንን አቋም ይዞ ነበር” በማለት በቴ የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠው ያለፉ በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡
በቴ እንዴት ትግሉን ተቀላቀሉ
በ1996 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን መቀላቀላቸው የተነገረው ፖለቲከኛ በቴ ዑርጌሳ እስከ ጎርጎሳውያኑ 2018 ወይም 2010 ዓ.ም. ድረስ በሂቡ በመንቀሳቀስ የፖለቲካ አቋማቸውን ስያራምዱም ነበር፡፡ “ከጎርጎሳውያኑ 2004 ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት አምና ድረስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል ሆኖ በተለያየ መንገድ ስንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ድርጅቱ በሂቡ ስንቀሳቀስ ስለነበር እሱም 2018 ወፊት መጥቶ በድርጅቱ ውስት የመስራት እስከሚገኝበት ድረስ በህቡ በመንቀሳቀስ ትግሉን ስመራ ነበር” ነወ ያሉት፡፡
የፖቲከኛው የፍትህ ጥያቄ
የፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ ግድያንተከትሎ በወቅቱ ምርመራ መጀመሩን አስታውቆ የነበረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እስካሁን ያሳወቀው ይፋዊ የምርመራው ውጤት አላሳወቀም፡፡ ዶቼ ቬለ ዛሬ የኮሚሽኑን አመራሮች ስለህደቱ ብጠይቅም ማብራሪያ ግን አላገኘም፡፡ የትግል ጓዳቸውና ጓደኛቸው አቶ ለሚም ይህ የዘገየ ያሉት የእዉቁ ፖለቲከኛ ፍትህ የሚያስቆች ነው፡፡ “አቶ በቴ በሃሳብ በመሟገት የሚያምን ሰው ነበር፡፡ በሚዲያም ሆነ በሚገኝባቸው የተለያዩ መድረኮች መታዘብ እንደሚቻለው በእውቀት የሚሞግት ሰው ነበር፡፡ የተበላሹ ሃሳቦች ተስተካክሎ የህዝብ ጥያቄ ወደፊት እንዲሄድም ነበር ሀሳቡ፡፡ ጠመንጃ ያነገበና ጫካም የገባ አልነበረም፡፡ ግን እንደዚ የፍጥኝ ታስሮ ተገድሎ መጣሉ በትውልዳችን በመጥፎነቱ ከመጠቀሱም በላይ እስካሁንም ፍትህ አላገኘምና የሚስቆጭ ነው” ሲሉም የዘገየውን ፍትአቸውን በቁጭት ገልጸውታል፡፡
ልክ የዛሬ ዓመት ፖለቲከኛው መገደላቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጨምሮ የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ፍትህ እንዲረጋገጥ ጥሪ አሰምተው ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም በእለቱ በግድያው ዙሪያ ትክክለኛውና ሀቀኛ ምርመራ እንደሚያከናውን በማሳወቅ በዚያው ሰሞን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ ከ10 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ