ከስደት "ወደ ከፋ ሕይወት እንገባለን" የሚል ሥጋት የተጫናቸው የቅማንት ስደተኞች በሱዳን
ሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2015በጦርነት የምትታመሰው ሱዳን ከኢትዮጵያ በምትዋሰንበት የገዳሪፍ ግዛት በተቋቋመው የባቢክር መጠለያ የሚገኙ ስደተኞች የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) የሚሰጣቸውን እርዳታ እየተጠባበቁ ነው። ድርጅቱ ለወትሮው እርዳታውን በየወሩ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም ስደተኞቹ ግን አራተኛ ሣምንቱን ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት እንዳያስተጓጉልባቸው ሰግተዋል። ይኸ ሥጋት ከተጫናቸው መካከል በ2013 ከኢትዮጵያ ተሰደው ሱዳን የገቡት አቶ ሰለሞን ምትኩ አንዱ ናቸው።
"ለአንድ ሰው 14 ኪሎ ማሽላ ነው የሚሰጠው። እዚህ ላለው ስደተኛ ሁሉ እርዳታ የሚሰጠው የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) ነው" የሚሉት አቶ ሰለሞን "ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በየወሩ ሲረዱን ነበር። ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ግን እስካሁን አልመጡም። ይመጣሉ የሚል ወሬ ነው የምንሰማው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
አቶ ሰለሞን እንደሚሉት ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርኻን በሚመሩት የሱዳን ጦር እና በጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሚታዘዘው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ "ሁሉም የበጎ አድርጎት ድርጅቶች" በመጠለያው ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጡትን እገዛ አቁመዋል። የሁለቱ ኃይሎች ውጊያ እንደ ኻርቱም ባይከፋም በርካታ ኢትዮጵያውያንን እስካስጠጋው የገዳሪፍ ግዛት የዘለቀ ነው። በባቢክር መጠለያ የሚገኘው ሌላው ስደተኛ መሠረት ከፋለ ጦርነቱ "ከገዳሪፍ አካባቢ ወደ እኛ ይስፋፋል" የሚል ሥጋት ተጭኖታል።
"ማኅበረሰቡ በትልቅ ሥጋት ውስጥ ነው" የሚለው ወጣቱ መሠረት ኻርቱም እና ገዳሪፍን ጨምሮ "የተለያዩ አካባቢዎች ማኅበረሰቦች እየተሰደዱ በገላባት አድርገው እየገቡ ነው። የእነሱን ሁኔታ ስናይ ከገባንው ስደት ደግሞ ወደ ከፋ ሕይወት ውስጥ እንገባለን የሚል ትልቅ ሥጋት ውስጥ ነው ያለንው" በማለት እርሱ እና አብረውት ባቢክር መጠለያ የሚኖሩ ስደተኞች የሚያብሰለስላቸውን ጉዳይ ያስረዳል።
በገዳሪፍ የሚገኘው የባቢከር መጠለያ ከኢትዮጵያ ለሚጎርፉ ስደተኞች በሱዳን መንግሥት እና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ትብብር ኅዳር 2014 የተቋቋመ ነው። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ መሠረት በመጠለያው የሚገኙ አብዛኞቹ ስደተኞች የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት ናቸው። ድርጅቱ እስካለፈው ጥር ወር ድረስ 2,842 ስደተኞች ቢመዘግብም የመጠለያው አስተባባሪ አቶ ደጀን ክብረት ግን ቁጥሩ ከዚያም በላይ ነው ባይ ናቸው።
«ከሰባት ሺሕ በላይ ሰው ነው የሚሆነው፤ በጣም በርካታ ሕዝብ ነው ያለው። [በመጠለያው] ቄስ አለ፤ እናቶች አሉ። አረጋውያን አሉ" የሚሉት አቶ ደጀን የሕክምና እጥረት አንዱ የስደተኞች ችግር እንደሆነ ገልጸዋል። "አሁን የሚሰጠን የምግብ አገልግሎት በጣም አነስተኛ ነው። መሠረታዊ ፍላጎቶችን ያሟላም አይደለም። ከዚያ በተጨማሪ ምንም የሌላቸው፤ ከኢትዮጵያም ሲመጡ የሚለብሱት [ልብስ]፤ የሚጫሙት ጫማ የሌላቸው ብዙ ደሐ ማኅበረሰቦች አሉ" ሲሉ በባቢከር መጠለያ የሚገኙ ስደተኞች ያሉባቸውን ተደራራቢ ችግሮች ይዘረዝራሉ።
ዶይቼ ቬለ ካነጋገራቸው መካከል እናት እና አባታቸውን ጨምሮ ከስምንት ቤተሰቦቻቸው ጋር የተሰደዱት አቶ ሰለሞን ምትኩ መተዳደሪያቸው ግብርና ነበር። ወጣቱ መሠረት በአንጻሩ ትምህርቱን በትውልድ ቀዬው በነበረ ግጭት ከ10ኛ ክፍል ለማቋረጥ ቢገደድም በምዕራብ ጎንደር ዞን በምትገኘው ሽንፋ ከተማ ባለ ሱቅ ሆኖ የተሻለ ሕይወት ይመራ እንደነበር ይናገራል። የመጠለያው አስተባባሪ አቶ ክብረት መምህርነትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሠሩ ናቸው። በአካባቢው በቀበሌዎች አስተዳደር ጉዳይ የተቀሰቀሰ ግጭት ግን የሦስቱንም ሕይወት አተረማምሶታል።
የ24 ዓመቷ ብርቱካን ዮሐንስ ከእህት እና ወንድሞቿ ጋር ምዕራብ ጎንደር ዞን ከሚገኘው የትውልድ ቀዬዋ ወደ ሱዳን ከተሰደደች ሁለት ዓመታት ሊደፍን ነው። ብርቱካን እንደምትለው ግጭቱ እናት እና አባቷን ነጥቋታል። "እኔ ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ። እናት አባት የለንም። እህት ወንድሞቼ ናቸው። ከእኔ ጋር ስምንት ነን" የምትለው ወጣት "ሕጻናቶች እዚያም ያሳለፍንው ታሪክ ከሕሊናቸው አልወጣም። በዚያ ላይ ይኸ ሲደገምባቸው ከፍተኛ [ችግር] ነው" ስትል በተደራራቢ ቀውስ የገጠማቸውን ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ታስረዳለች። "በቂ የሆነ ሕክምና የለንም። እርዳታው በቂ አይደለም። የውኃ ችግርም አለን። አልባሳት በተለይ ለሕጻናት በጣም አስፈላጊ ነው። አልባሳት የለንም" በማለት የመጠለያው አስተባባሪ አቶ ደጀን ክብረት የጠቀሷቸው ችግሮች ብርቱ እንደሆኑ ትገልጻለች።
በባቢከር መጠለያ የሚገኙት ስደተኞች እስካሁን በቀጣይ እጣ ፈንታቸው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳላነጋገራቸው ገልጸዋል። ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለምን በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ከእርዳታ ድርጅቶች በሚሰጣት ማሽላ እና ዘይት ታናናሾቿን ለአንድ ወር የመቀለብ ፈታኝ ኃላፊነት ትከሻዋ ላይ የወደቀው ወጣት ብርቱካን ግን ወደ ኢትዮጵያ ከመመለስ ይልቅ ወደ ሦስተኛ አገር መሻገርን ታልማለች።
"የሰላሙ ጉዳይ ያሳስበኛል" የምትለው ብርቱካን "ሰላም ቢሆንም እናት እና አባት ስለሌለን ምን ተስፋ አደርጋለሁ?" ስትል መልሳ ትጠይቃለች። ወጣቱ መሠረትም እንደ ብርቱካን ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለስ ይልቅ ወደ ሦስተኛ አገር መሻገርን ይሻል።
ራሳቸው ስደተኛ ሆነው የባቢክር መጠለያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደጀን ክብረት ግን አብዛኞቹ ወደ ትውልድ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። "የሚመለከተው ፌድራል መንግሥት ከእኛ ጎን ሆኖ እኛ ሔደን የምንሰፍርበት ቀያችን አካባቢ እንድንገባ እና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የጸጥታ ጥበቃ እንዲደረግ ኃላፊነቱን ቢወጣልን እኛ የመመለስ ፍላጎቱ አለን" ሲሉ አቶ ደጀን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሱዳን የሚገኙ ስደተኞች ጉዳይ "በክልል ደረጃ ሳይሆን እንደ ሀገር በፌድራል ደረጃ የሚታይ" እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ በጽሁፍ በሰጡት መልስ ገልጸዋል። "ታጥቀው አካባቢው ላይ ችግር ሲያደርሱ የነበሩ ኃይሎችን ጨምሮ ለህግ የሚቀርበው በህግ ጥላ ስር እንዲውል እንደ ጥፋቱ ክብደት ደግሞ ምህረት የሚደረግለትም ምህረት ተደርጎላቸው ቀጠናው ሰላም ከሆነ ቆይቷል" ያሉት ኃላፊው በ2013 በነበረው ግጭት ከሶስት ወረዳዎች የተፈናቀሉ 3406 የቅማንት ማህበረሰብ አባላት "ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ በሆነ አግባብ እየኖሩ" መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። አቶ ግዛቸው ወደ ሱዳን የተሰደዱ "በሰላም ይቅርታ ጠይቀው እስከመጡ ድረስ ክልላችን ውስጥ ለነበሩት አካላት የተደረገውን ለማድረግ ክልሉ ሁሌም ዝግጁ ነው" የሚል መልስ ሰጥተዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ