ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት 80ኛ ዓመት በኋላ ያንሰራራው ቀኝ ጽንፈኝነት ዘረኝነትና ፀረ ሴማዊነት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2017በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለደረሱ ጭፍጨፋዎችና ጥፋቶች ተጠያቂው አዶልፍ ሂትለር ከሞተ 80 ዓመታት ቢቆጠሩም የዶቼቬለው ሀንስ ፋይፈር እንደዘገበው ሂትለር ቢያንስ በኢንተርኔት አልሞተም ። የቢሊዮነሩ ኢሎን ማስክ ንብረት በሆነው ኤክስ ወይም በቀድሞ መጠሪያው ትዊተር መፈለጊያ ላይ ሂትለር የሚለው ስም ሲሰጥ የጥቂት ሰኮንዶች እድሜ ያለው መረጃ ይገኛል።
በአሁኑ ጊዜ የኢንተርኔቱ ሜዳ በሂትለር ፎቶዎች፣ ማስታወሻዎች ፣ስዋስቲካ በመባል በሚጠራው አርማ እና «ሀይል ሂትለር» በተሰኘው መፈክር ተሞልቷል። የሂትለር ደጋፊዎች በጀርመን በአውሮጳ በዩናይትድ ስቴትስ በላቲን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ እና በህንድ ፀረ-ሴማዊ እና ፀረ-ዴሞክራሲ መረጃዎችንና የሴራ ጽንሰ ሀሳቦችን ጨምሮ መርዘኛ አስተሳሰቦቻቸውን በየቦታው እየረጩ ነው።
የሂትለር መፀሐፍ «Mein Kampf» «ትግሌ»
አምባገነኑ ሂትለር ከሞተ 80 ዓመታት ቢያልፍም፣በርካታ ሰዎችን ባስጨረሰው በዚህ ሰው ስም አሁን ብዙ ገንዘብ እየተገኘ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መጻህፍት መሸጫዎች የሂትለርን ማስታወሻዎችና ልዩ ልዩ መረጃዎችን ያካተተውን «Mein Kampf» የተሰኘውን መፀሐፍ በመሸጥ ተጨማሪ ገንዘብ እያገኙ ነው። መፀሐፉ በጀርመን ወደ 250 ዩሮ ገደማ ሲሸጥ ፣ በስፓኝ ቋንቋ የተተረጎመው ደግሞ 300 ዩሮ እየተቸበቸበ ነው። የእንግሊዘኛው ትርጉም ደግሞ በኢንተርኔት ወደ 600 ዶላር ያወጣል። መጸሐፉ በግብጽ ገበያዎች እና በህንድ ደግሞ ባነሰ ዋጋ ይገኛል። ይኽው የሂትለር መጸሐፍ ፣አክራሪ የዓለም እይታውን ፣ገዳይ ፀረ ሴማዊነቱን እና ለዴሞክራሲ እና ለማኅበራዊ ብዝሀነት ያለውን ንቀት ያብራራበት ማኒፌስቶ ተደርጎ ይወሰዳል።
ማስታወሻው የተዘጋጀው ሂትለር በጎርጎሮሳዊው1933 ስልጣን ከመያዙ ከ8 ዓመት በፊት ነበር። በዚህ መፀሐፍ ሂትለር ለጀርመናውያን ከሁሉም ዘሮች የበላይ የሆነ ደረጃ ይሰጣል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ምሥራቅ አውሮጳን የጀርመን የማድረግና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የማባረር ህልም ነበርው። "Mein Kampf" ወይም «ትግሌ» የተሰኘው የሂትለር መጸሀፍ ኦስትሪያዊው የታሪክ ምሁር ኦትማር ፕሎኪንግር ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት ርዕሱ ብቻ ብዙ ይናገራል። በውስጡም ያካተተው ሀሳብም ዘረኛ ነው ይላሉ።
"የጦርነቱ ጭብጥ በርዕሱ ውስጥ ቀድሞውኑ ይገኛል። እና በእውነቱ ሁሉም ዘረኝነት በውስጡ ታጨቋል። የበለጠ ጠንካራው ያሸንፋል, ጠንካራው ዘር ያሸንፋል ማለት ነው። በግለሰብ ትግል ውስጥ እንኳን, ለደረጃዎች፣ ለቢሮዎች፣ በሚደረገው ፉክክር የሚያሸንፈው በጣም ጠንካራ ፍላጎት ያለው በጣም ጨካኝ በሰፊው ደግሞ የተሻለው ዘር ወይም የተሻለ ችሎታ ያለው ነው ይላል። "
የመጸሐፉ ግምገማ
በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 1925 የታተመው መጸሀፉ የዶቼቬለው ሀንስ ፋይፈር እንደዘገበው በውስጡ ስሜታዊነት ብቻ ነበር የያዘው። ሂትለር በከባድ የሃገር ክህደት ወንጀል ከአንድ አመት በላይ በእስር ቤት ያሳለፈ ተገፍቶ የተጣለ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄደ ሰው ነበር። የብሔራዊ ሶሻሊስት ንቅናቄውም አነስተኛ ሲሆን በጀርመን እና ኦስትሪያም ጉልህ የፖለቲካ ተፅእኖ አልነበረውም።
በወቅቱም ሂትለር ከፖለቲካ የመጥፋት እጣም ተጋርጦበበት ነበር። ያኔ ሌሎች በርካታ ጠንካራ ትችት የሚቀርብባቸው የብሔረተኞች ጽሁፎችና የእስር ቤት ማስታወሻዎች በመፀሐፍ ገበያ ይቀርቡ ነበር። ፖሎኪንገር እንደሚሉት በወቅቱ በሂትለር መጸሀፍ ቅር የተሰኙ በርካታ ተከታዮቹ ነበሩ። ከመካከላቸው አንዱን ያስታውሳሉ።
«በዶቼ ሳይቱንግ ላይ የወጣ ሂትለርን በጣም ያስቆጣ አንድ ታዋቂ ምንባብ« እኛ በብሔረተኛ የመከላከያ ትግላችን ለ40 ዓመታት ቆይተናል። አሁን ወጣቱ መፈንቀለ መንግስት አድራጊ ሂትለር መጥቶ ለኛ የፖለቲካ አስ,ተሳሰብ ምን እንደሆነ ሊያብራራልን ይሞክራል። በርግጥ አዎንታዊ አስተያየቶችም አሉ። አምባገነን በመሆኑ ሰዎች ያከብሩታል። ሁሉንም ነገር በራሱ ነው የተማረው። ሆኖም በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ማንም ሂትለር ለውይይት የበቃ አዲስ ነገር ግን አምጥቷል የሚል ግን አልተገኘም።» ሆኖም መጸሐፉ በከፍተኛ ደረጃ ተሸጧል፤ ለሂትለርም ብዙ ገንዘብ አስገኝቶለታል።
ሂትለር ከሌሎች አምባገነኖች ይለያል
ሂተለርን ከሌሎች አምባገነኖች የሚለየው "Mein Kampf." በተባለው መጸሀፉ ሀሳቡን ፣የዓመፅ ሀሳቦቹንም በይፋ ማሳወቁ መሆኑም የመጸሀፉ አርታዒዎች በሰጡት ትንታኔ ገልጸዋል። ሂትለር «ጦርነትን በቆራጥነት ያስተዋውቃል ፤ የወደፊቱ ጦርነት የህልውና ትግል ይሆናል ፣ ለሰብዓዊነትና ለውበት የሚሰጠው ግምት በከንቱነት መውደቅ አለበት" ይል እንደነበርም ገልጸዋል። ስለዚህ በነርሱ ግምገማ የአዶልፍ ሂትለር ዘመን አምባገነን አገዛዝ ፣ በይፋ በማሳወቅ የሚመራ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1933 የጀርመን ምርጫ ከ117 ሚሊዮን 277 ሺህ 180 ጀርመናውያን ለሂትለርንና ለጀርመን ብሔራዊ ሶሻሊስት የሠራተኞች ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት ስልጣን እንዲይዝ መንገዱን ጠርገውለታል። ዶቼቬለ ስለሂትለር የጠየቃቸው በጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ፤ እንዲሁም የታሪክ ምሁር ልዑል ዶክተር አስፋ ወሰን አሥራተ ካሳ ሂትለር በወቅቱ ስልጣን የያዘው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን ያስታውሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት የተመረጠበትም ምክንያት የኮምኒዝም ፍራቻ ነበር ።
የሂትለር መመረጥ ያስከተለው እልቂት
የሂትለር መመረጥ በአውሮጳ ጦርነትና እልቂት አስከትሏል። በአውሮፓ አይሁዶች ላይም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የጅምላ ጭፍጨፋ ተካሂዷል።የናዚ አገዛዝ እና ደጋፊዎቹ የጀርመን ህዝብ ጠላቶች ባሏቸው ላይ በሙሉ አሰቃቂ የጭካኔ እርምጃዎች ወስደዋል። ሂትለር በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 30 ቀን 1945 ዓም ሕይወቱን በገዛ እጁ ካጠፋ ከ8 ቀናት በኋላ አገዛዙ ተንኮታኩቶ ወደቀ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ጀርመናውያን ዳግም ይህ ዓይነቱ ድርጊት አይፈጸምም ሲሉ ቃል ገቡ።
ይሁንና አሁን የሂትለር ፀረ ሴማዊነት ሃሳብ እንደገና በአሳፋሪ ሁኔታ አንሰራርቷል። ይህ ብቻ አይደለም የዴሞክራሲ ጥላቻና ዘረኝነትም እንደገና አብቧል። ቀኝ ጽንፈኝነት ፀረ ሴማዊነት ፣ እና የቀኝ ጽንፈኞች ርዕዮተ ዓለም እንደገና እየተመለሱ ነው። ወጣት ቀኝ ጽንፈኞችም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይበልጥ አመጸኛ እየሆኑ ነው። ከዛሬ 80 ዓመት በኋላ በነውርነት የሚታዩ አስተሳሰቦች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደባባይ እየወጡ ነው።
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ