በዋግኸምራ ዞን አስተዳደር ከ4,000 በላይ አርሶ አደሮች በተፈጥሮ አደጋ መጎዳታቸው
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ የሚከሰትበት በአማራ ክልል የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በ2017/18 የክረምት ወቅት በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለ ዝናብ በብሔረሰብ ዞኑ ፃግብዥ ወረዳ 4 ቀበሌዎች የመኸር እርሻ ሙሉ በሙሉ መውደሙን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቋል። በወረዳው 06 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ገብሬ ግዛው ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ 1198 አርሶ አደር እርሻ በጎርፍ መወሰዱን እና ለቤት እንስሳት የሚሆን መኖ እንዳልቀረ ይናገራሉ። «በረዶና ጎርፍ በቀላቀለ ዝናብ የተከልነውን ሰብል ወስዷል፤ በጭራሽ የሚባላ የለም የ30 አባወራ ማሳ ነው የተረፈው። ለከብት መኖ የለም፤ የአርሶ አደሩ ብዛት 1198 ነው።»
ምንም ዓይነት ምላሽ ያላገኘዉ የተፈጥሮ አደጋ
በጻግብዥ ወረዳ 08 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘይኑን ካሱ በመኸር እርሻ ወቅት የተተከለ ማሽላ በቆሎም ሆነ ልዩ ልዩ ሰብሎች በሙሉ በጎርፍ መጥፋታቸውን ይናገራሉ።
573 አባወራ አርሶ አደር የተጎዱበት በጻግብዥ ወረዳ የ010 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ይግዛው የዘራነው ዘር በሙሉ በበረዶ ወድሞብናል፤ ከመንግሥት ግን ምንም ዓይነት ድጋፍ ማግኘት አልቻልንም ይላሉ። «በእኛ ቀበሌ የደረሰው ችግር በረዶ ነው የወደቀብን 573 አባወራ ተጎድቷል። ያው ለመንግሥት ግብርና ባለሙያ ሪፖርት ተደርጎ ነበር ምላሽ አልተገኘም።»
ወረዳው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ተደጋጋሚ ጉዳት አስተናግዶል
በጻግብዥ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሥዩም አባተ በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛጉዳት ያስተናገደው እና በመልሶ ማቋቋሙ ምንም ዓይነት ትኩረት ያልተሰጠው ጻግብዥ ወረዳ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መደበኛ ባልሆነ ዝናብ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።
በአደጋው የአንድ ሰው ሕይወት ሲጠፋ 19 ቤቶች ሙሉበሙሉ ወድመዋል። 4585 የማኅበረሰብ ክፍልም ለችግር ተዳርጓል የሚሉት አቶ ሥዩም አባተ ለመንግሥት የደረሰውን አደጋ ብናሳውቅም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ይላሉ።
«ባድሊባኖስ፣ ሰላምጌ፣ እምሊ አልበሳ፣ ፀፀጥነው፣ ቂርቆስ የሚባሉ ቀበሌዎችን ነው በረዶ የመታው 19 ቤቶች ፈርሰዋል አንድ ሰው ሞቷል እንስሳትም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለእነኝህም ምንም ድጋፍ አልተደረገም።»
የዋግ ህምራ ብሔረሰብ ዞን የጉዳቱን መጠን አላሳወቀም
የዋግህምራ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ እና የግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲሱ ወልድዬ የተፈጠረውን አደጋ በተመለከተ ለማናገር ብንደውልም ስልካቸው አይሠራም። ይሁን እንጂ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ በዋግህምራ ብሔረሰብ ዞን ጉዳቱ ተለይቶ አልቀረበልንም ይላሉ፤ ተለይቶ ሲቀርብ ግን አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
ኢሳያስ ገላው
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ