ኦፌኮ እና ኦነግ “የሰላም መፍትሄ” ለምን አወዛገበ?
ሰኞ፣ የካቲት 24 2017ኦፌኮ እና ኦነግ “የሰላም መፍትሄ” ለምን አወዛገበ?
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከአንድ ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ከኦሮሞ ማህበረሰብ ጋር ከተወያዩ በኋላ ያቀረቡት “ለግጭቶች ዘላቂ እልባት“ ያሉት የመፍትሄ አቅጣጫ ማወዛገቡን ቀጥሏል። ሁለቱ አንጋፋ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ከተወያይ ማህበረሰብ አካላት ቀርቧል ያሉትን የመፍትሄ አቅጣጫ በማቅረብ ከመንግስት ጋር ለመወያየት መዘጋጀታቸውን ነበር በይፋ የገለጹት።
ይሁንና ፓርቲዎቹ የዘላቂ ሰላም የመፍትሄ አቅጣጫ ያሉት ሃሳብ በመንግስትም ሆነ በሌሎች ተቃዋሚ ቡድኖች ነቀፌታ ሲነሳበት ተስተውሏል፡፡ ፓርቲዎቹ በበኩላቸዉ መፍትሄ ሆናል ብለው ካቀረቡት ሃሳብ ዝንፍ እንደማይሉ እያሳወቁ ነው።
የፓርቲዎቹ የጋራ አቋም
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከተለያየ አቅጣጫ የኦሮሞን ማህበረሰብ እንወክላለን ከሚሉና ከሌሎችም ለቀረበባቸው ትችቶች ምላሽ መሰል የጋራ መግለጫቸውን ስያወጡ እንዳስረዱት፤ ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅርቡ የደረሱበት የጋራ አቋም ለህብረተሰቡ እንቅፋት የሆነውን በኦሮሚያ ያለውን የሰላም ችግር በትብብር ለመፍታት ያለመ ብቻ ነው ብለውታል።
ወደዚህ አቋም ለመምጣትም ከሁለት ወራት በላይ የዘለቀ ውይይት ተደርጎ የተለያዩ የማህበረሰብ አካላትን በመጨመር ከአንድ ሳምንት በፊት ለአራት ቀናት ወደ ምክክር መገባቱን የገለጸው ያሳለፍነው ሳምንት መጨረሻው የሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መግለጫ፤ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁሟል፡፡ በዚህም ከኦሮሞ እና ኦሮሚያ ክልል ጋር በተያያዙ በርካታ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ መደረስ እንደሚቻል በማመን ከመንግስት ጋር ለመወያየት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንመም ፓርቲዎቹ በጋራ አቋማቸው አስምረውበታል። የኦነግና ኦፌኮ «የሽግግር መንግሥት» ምስረታ ምክረሃሳብ
ፓርቲዎቹ ስላስቀመጡት የመፍትሄ አቅጣጫ ይህን ካሉም በኋላም የሚሰነዘርባቸው ትችት ነቀፋው ግን አላቧራም፡፡ በዚህ ላይ ሁለቱ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች አስቀመጥን ያሉት የመፍትሄ አቅጣጫ በበርካቶች ዘንድ የሃሳብ መከፋፈል የፈጠረው ለምን ይሆን በሚል የተጠየቁት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “ሁሉም ነገሮችን ከራሱ የፖለቲካ ፍላጎት አንጻር ስለሚያሰላ ይሆናል” በሚል መልሰዋል።
የውዝግቡ መንስኤ እና የፓርቲዎቹ የማይቀለበስ አቅጣጫ
ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች የውይይቱ መርህ ዓላማ በኦሮሚያ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት በጦርነት ላይ ያሉትን ተፋላሚ አካላት ግጭት በማቆም ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መስራት ነው፤ ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህም ሰላም የሁሉም ችግሮች መፍትሄ መሆኑን በማመን እንደሆነ ነው የተጠቆመው፡፡ በተለያዩ አቅጣጫ የተነሱትን ውዝግቦች ተከትሎ ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ያስቀመጡትን አቅጣጫ ይቀለብሱት ይሆን የተባሉት ፕሮፌሰር መረራ በፍጹም የሚል ምላሻቸውንም ። “እኛ ህጋዊ መድረክ ላይ የምንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት እንደመሆናችን ድርድሮች ውይይቶች ይጠቅማሉ፤ ለህዝባችን ፋይዳ አለው ብለን ስናምን እንገባባቸዋል” ነው ያሉት።
“ቀጣዩ ምዕራፍ ከመንግስት ጋር ወደ ውይይት መግባት ነው” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ “ነጻ ውይይት እና ውሳኔ” ባሉት የተደረሰውን የጋራ አቋም ወደ ስራ ከመተርጎም ውጪ ሌላ ምርጫ አለመኖሩንም ገልጸዋል።የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ጥሪ፣ ተስፋና ስጋቱ
በውይት ሃሳቡ የመንግስት ተሳትፎ አለን?
በኦሮሚያ ውስጥ ባለው ግጭት አንዱ መሪ ተዋናይ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ባለፈው ሳምንት በይፋ ባወጣው መግለጫ “ኦፌኮ እና ኦነግ በአዲስ አበባ ለምክክር ተቀምጠው ያወጡት የጋራ አቋም በመንግስት የተቀናበረ በመሆኑ እንደቁምነገር አይወሰድም” በማለት ጉዳዩን ነቅፎ አጣጥሎታል፡፡ መሰል ጉዳዮች በታቀደው ውይይት ላይ እንቅፋት አይሆንም ወይ ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ፤ “እነሱን ውጪ ትቶ ሰላምና መረጋጋት እንፈጥራለን ብሎ የተነጋገረ የተደራደረ አካል የለም፡፡ እና እያልን ያለነው ሁሉንም የሚወክል የጋራ መንግስት ኦሮሚያ ላይ ይቋቋም ነው የምንለው እንጂ የኦሮሞን ችግር በሙሉ ፈተናል ብሎ የተቀመጠ አቅጣጫ የለም” በማለት የታቀደው ውይይት የሁሉም ተሳትፎ የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶቹ “የማህበረሰብ ተወካዮች” ከተባሉት ጋር ተወያይተው አቅጣጫ ያስቀመጡበትን መድረክ መንግስት እንደሚጣውቀውም ፕሮፌሰር መረራ አልሸሸጉም፡፡ “ምንም መንግስት ሳያውቅ ከኦሮሚ በሙሉ ሰዎችን ሰብስበህ አዲስ አበባ በሆቴል ውስጥ በይፋ ስትወያይ መቆየትን መንግስት አያውቅም ያለም የለም” በማለት በፓርቲዎቹ እና መንግስት መሃል ከሁሉም ወገን የተውጣጣ አቀራራቢ መኖሩን ገልጸዋል።
ተጠባቂው ቀጣይ ምዕራፍ
በሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወቅታዊ አቋም ላይ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶች ያደረጉት ውይይት የሚነቀፍ ባይሆንም “የሽግግር መንግስት ማቋቋም” በሚል የቀረበው ሃሳብ ግን ተቀባይነት እንደማይኖረው በአስተያየታቸው አረጋግጠዋል።“እኛ በአመንበት መንገድ የህዝቡን ትግል በሰላማዊ መንገድ ማስተባበሩን እንቀጥላለን” ያሉት ፕሮፈሰር መረራ “መንግስት በራሱ በኩል ያለውን የቤት ስራ በመስራት በሰላም ውይይቱ ላይ ተሳታፊ ይሆናል” የሚለውን እምነታቸውን አስረደድተዋል።
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ