እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል የክሰሰው ዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምሁራን ማህበር
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው ወንጀል የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን የዓለም የዘር ማጥፋት ወንጀል ምሁራን ማኅበር ባስታወቀ ማግስት፤ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ፔድሮ ሳንቼዝ ዛሬ ለጋርዲያንን በሰጡት ቃለ መጠይቅ እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ላይ እየፈጸመችው ባለው ወንጀል አንጻር ኅብረቱ ጠንካራ አቋም አለማራመዱ ተአማኒነት ያሳጣው መሆኑን አሳውቀዋል። የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች ሩሲያ በዩክሬን ላይ ላይ እየፈጸመች ባለው ጦርነት ከዩክሬን ጎን በመቆምና በሩሲያ ላይ ጠንካራ ርምጃዎችን በማራመድ የሚጠቀሱ ቢሆንም፤ በእስራኤል ላይ ግን ጠንካራ ውሳኔ ሲያሳልፉ ዐይታዩም በማለት ይህ ሊቀጥል እንደማይገባው አሳስበዋል።
አምስት መቶ አባላት ያሉት የዓለም የዘር ማጥፋት ወንጀል ምሁራን ማኅበር ግን እስራኤል፤ በአሸባሪነት የተፈረጀው፤ ሐማስ እ እ ኦ ኦክቶበር 7/ 2023 በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ከፈጸመ ወዲህ፤ እራሷ በሰላማዊ ሰዎችና መሰረተ ልማቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመፈጸሟ፣ የጦር፣ የሰብአዊነት እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ላይ በመሳተፏና ከሁሉም በላይ ደግሞ ርዳታ እንዳይደርስ በማድረግ ረሐብን የማጥቂያ መሣሪያ በማድረጓ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
የእስራኤል ተቃውሞ
እስራኤል ግን ይህን በዓለም ዙሪያ ያሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምሁራንን ግኝት እና ውሳኔ አጥብቃ አውግዛለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ባወጣው መግለጫ የዓለም የዘር ማጥፋት ወንጀል ምሁራን ማኅበር ለመጀመሪያ ጊዜ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ የሆነችውን እስራኤልን በዘር ማጥፋት ከስሷል በማለት የእስራኤል ርምጃ የራስ መከላከል ርምጃ መሆኑን አሳውቋል።
የእስራኤል የመከራከሪያ ሀሳብ ህጋዊ መሰረት የለውም መባሉ
የማኅበሩ ፕሬዝደንት ፕሮፈሰር ሜላኒ ኦብሬይን ግን ይህንን የእስራኤል የመከራከሪያ ሀሳብ «ራስን የመከላከል መብት በሌሎች ላይ ወንጀል የመፈጸምን መብት አይሰጥም» በማለት ውድቅ አድርገውታል። «እንደ ሕግ ባለሞያነቴ የጦር ወንጀል፤ የሰብአዊነት እና የዘር ማፍጥፋት ወንጀሎች፤ ምንም አይነት የራስ መከላከል መብት ምክንያት ሊቀርብባቸው የማይችል መሆኑን መናገር እችላለሁ። መከራከሪያው ሐማስ ጥቃት በፈጸመ ማግስት እንኳ ቢሆን ትንሽ ትርጉም ሊሰጥ ይችል ነበር። ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀ ግድያና ጥቃት ግን ምንም አይነት የራስ መከላከል ምክንያት ሊቀርብበት አይችልም» በማለት የማኅበሩ አባሎች ወንጀሉን በዘር ማጥፋት ወንጀል የፈረጁበትን ምክንያት ግልጽ አድርገዋል።
የውሳኔው አንደምታ
የእስራኤል እስካሁን በጋዛ እየፈጸመች ያለውን ወንጀል በርካታ አለማቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት ያወገዙት ቢሆንም ወንጀሉን ግን በሰብአዊነት የተቃጣ ወይም የጦር ወንጀል ከማለት በዘለለ በዘር ማጥፋት ወንጀል ደፍረው አልፈረጁትም። ሆኖም ግን ይህ የዘርፉ ባለሞያዎች ብየና መንግስታትም ተመሳሳይ ርምጃ እንዲወስዱ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሎ ተገምቷል። በቤይሩት የአሜሪካ ዩንቨርስቲ ፕሮፌር የሆኑት ዶክተር ራሚ ኩሃውሪ እንደሚሉት ውሳኔው የጥቂት ጋዜጠኞች ወይንም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ሳይሆን፤ የታወቁ የዘርፉ ባለሞያዎች በመሆኑ ተሰሚነት ይኖረዋል፤ «እነዚህ በዓለም ትኩረት በሚሰጠው የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ የተሰማሩ ምሁራን ናቸው። በእነዚህ ምሁራን እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸመች መሆኑ መገለጹ ትኩረት መሳቡ አይቀርም» በማለት ውሳኔው እስራኤል ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ብቻ ሳይሆን የ1948ቱን የሰብአዊ መብት ድንጋጌን የፈረሙ አገሮች ሁሉ በእስራኤል ላይ ጫና በማድርግ ወንጀሉን ማስቆም ያለባቸው መሆኑንም የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸዋል።
ገበያው ንጉሴ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ