እስራኤል 200 ፍልስጤማውያን ሐማስ 4 ታጋቾች ለቀቁ
ቅዳሜ፣ ጥር 17 2017በጋዛ የተኩስ አቁም ሥምምነት መሠረት እስራኤል 200 ፍልስጤማውያን እስረኞችን፤ ሐማስ 4 ታጋቾችን ዛሬ ቅዳሜ ለቀቁ። እስራኤል እና ሐማስ በደረሱበት የተኩስ አቁም ሥምምነት መሠረት ሁለተኛውን ዙር የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ማጠናቀቁን ቀይ መስቀል አስታውቋል።
ከእስራኤል እስር ቤቶች ከተለቀቁ ፍልስጤማውያን መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት በቀይ መስቀል ተሽከርካሪዎች ታጅበው በአውቶቡስ በዌስት ባንክ ከምትገኘው ራማላሕ ሲደርሱ በአካባቢው የተሰበሰበ ሕዝብ በከፍተኛ ሆታ ተቀብሏቸዋል።
ሌሎች 70 ፍልስጤማውያን ከእስራኤል እስር ቤቶች ከተፈቱ በኋላ ወደ ግብጽ ተሸኝተዋል። ወደ ግብጽ የተሸኙት በእስራኤላውያን ላይ ጥቃት ፈጽመው የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው እና ወደ ጋዛ መመለስ የማይችሉ ናቸው።
ፍልስጤማውያኑ ከግብጽ በኋላ ወደ ቱርክ፣ አልጄሪያ ወይም ቱኒዝያ ሔደው መኖር እንደሚችሉ የፍልስጤም የታራሚዎች ጉዳይ ኮሚቴ ኃላፊ አሚን ሹማን መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ሐማስ በፊናው ፊታቸውን በጭምብል የታጠቁ የጦር መሣሪያዎች ያነገቡ ታጣቂዎቹን አሰልፎ አራት ሴት እስራኤላውያን ታጋቾችን ለቀይ መስቀል አስረክቧል። ከ477 ቀናት በኋላ ነጻ የወጡት ታጋቾች ወደ ሆስፒታል ተወስደው ምርመራ እንደተደረገላቸው የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
አራቱ ሴት ወታደሮች መስከረም 26 ቀን 2016 የታገቱት ከጋዛ አቅራቢያ ለቅኝት ከተመደቡበት ነው። ለ15 ወራት የተደረገውን ውጊያ በገታው የተኩስ አቁም የተለቀቁ ታጋቾች ቁጥር 7 ደርሷል።
ከስድስት ቀናት በፊት በተኩስ አቁም ሥምምነቱ መሠረት ሦስት ሴት ታጋቾች ተለቀው ነበር። አሁንም ሌሎች 87 ታጋቾች በጋዛ የሚቀሩ ሲሆን የእስራኤል ባለሥልጣናት 53ቱ በህይወት ይገኛሉ የሚል ዕምነት አላቸው። በተኩስ አቁም ሥምምነቱ መሠረት በመጀመሪያው ዙር በአጠቃላይ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሥምምነቱ መሠረት ሁለተኛው ዙር የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ሐማስ እስራኤል የጋዛን የተኩስ አቁም አተገባበር ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ወደ ሰሜን ጋዛ እንዳይመለሱ በመከልከል እያደናቀፈች ነው ሲል ከሷል። ታጣቂ ቡድኑ ጉዳዩ ለቀሪው የተኩስ አቁም አተገባበር ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
አሜሪካ “ታላቅ አጋር” ካለቻት ከእስራኤል ጋር በመተባበር ቀሪ ታጋቾችን ለማስለቀቅ መስራቷን እንደምትቀጥል የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
እሸቴ በቀለ
ልደት አበበ