ኤርትራ የህወሓትን “የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ የማባባስ ፍላጎት የላትም” ኤርትራ
ዓርብ፣ መጋቢት 5 2017ኤርትራ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን "የውስጥ ሽኩቻ የማባባስ ፍላጎት የላትም" ሲሉ የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ትናንት በኤክስ መገናኛ አውታር ገልጸዋል።
ትናንት አዲስ አበባ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ "የተወሰኑ ወታደራዊ እና የፖለቲካ ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ" ያሏቸው የህወሓት አመራሮች ከኤርትራ ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ነበር። በዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ግን “ሌላ አካልን ለመጉዳት በሚል ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚደረግ ግንኙነት የለም” ሲል መልሷል። የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል "በህወሓት የፖለቲካ አንጃዎች ውስጥ የተፈጠረ" ያሉትን የውስጥ ሽኩቻ ሀገራቸው የማባባስ ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል። የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት ትናንት በኤክስ ባሰፈሩት መልዕክት ነው። አቶ የማነ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው ኹኔታ "በትግራይ ህዝብ ላይ አላስፈላጊ እና ሊወገድ የማይችል ስቃይ ያስከትላል" ሲሉ ጽፈዋል።አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ ላይ የሰጡት መግለጫ
"የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ አለ" የሚለው "ተደጋጋሚ" ሲሉ የገለፁት ክስ "ፍፁም ሀሰት ነው" ሲሉም አስተባብለዋል። ይህ ክስ የሚቀርበው "ግጭት ለመቀስቀስ ሰበብ ለመፍጠር ነው" በማለት የሀገራቸውን አቋም አስፍረዋል። "የኤርትራ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ" ሲሉ ተናግረዋል። "ኤርትራ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ለማፍረስ ምንም ፍላጎት የላትም" ሲሉ ጉዳዩ "በመሠረታዊነት የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ" መሆኑን አቶ የማነ ገልፀዋል። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ምላሽ የሰጡት ትላንት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኤርትራን ጉዳይ ካነሱ በኋላ ነው።
"ትግራይ ክልል ውስጥ የሚነሳን ግጭት ብዙ ኃይል ይገባበታል" ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ "በዚህ ውስጥ ኤርትራ አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግጭት የጀመረው "የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈፀመ በኋላ ነው" የሚል መረጃም አክለዋል። "አንጃ" ሲሉ ከጠሩት የህወሓት ቡድን አንዱ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እንዳለውም ገልፀው ነበር።
በዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ህወሓት የሰጠው ምላሽ
በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ትናንት ምሽት በምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አማኑኤል አሰፋ በኩል "ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሌላ አካልን ለመጉዳት በሚል የሚፈፀም ግንኙነት የለም" ብሏል።
"ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለጦርነት የሚጋብዝ ግንኙነት የለንም" ያሉት አቶ አማኑኤል አሰፋ ይህ በተደጋጋሚ ስለመገለፁም ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንቱ መግለጫቸው ሸሽተው አለመምጣታቸውን ገልፀው ነበር። አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር በመሆን መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላት በትግራይ ወቅታዊ ኹኔታ ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን የሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ እና በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከፌድራል መንግሥት ጋር እንደሚወያዩ በየፊናቸው አስታውቀዋል። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አብርሃም በላይ ለፋና ቴሌቪዥን ከትናንት በስቲያ በሰጡት ማብራሪያ "ከክልሉ መንግሥት በላይ የሆኑ አጀንዳዎች ከተፈጠሩ መፍትሔ በጋራ የምንፈልግበት ነው የሚሆነው" ብለዋል። በትግራይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሻከር መጀመሩ በተለያዩ አካላት መነገር ከጀመረ ቆይቷል። በቅርቡ የቀድሞው ርእሠ ብሔር ሙላቱ ተሾመ ኤርትራን በሚመለከት በአልጀዚራ ድረ ገጽ በታተመ የግል አስተያየት "የኢሳያስ አፈወርቂ መንግድሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ ነው" ብለው ነበር። አክለውም "በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ግጭት እንዳይከፈት ለማስቆም ጊዜው አሁን ነው" ብለዋል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ አቋም የመንግሥት አለመሆኑን የገለፀ ቢሆንም።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ