ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪቃ በሕገ ወጥ የሰዎች አዛዋሪዎች የሚፈጸምባቸው በደል ከፍቷል
ረቡዕ፣ ጥር 7 2017
ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ፣ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ሰንድ የሌላቸው በሚባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት በደል መባባሱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ይናገራሉ። በነዚሁ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የታገቱ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ማስለቀቁን በቅርቡ የገለጸው የሀገሪቱ ፖሊስ፣ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ ተይዘው ማግኘቱን አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ነበር ፣የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ በደቡብ አፍሪቃዋ የንግድ ከተማ በጆሀንስበርግ ዳርቻ በሚገኝ አንድ ጠባብ ቤት ውስጥ በሰዎች አዛዋሪዎች ታግተው የነበሩ እርቃናቸውን የነበሩ 26 ኢትዮጵያውያንን ማስለቀቁን ያሳወቀው። ፖሊስ እርምጃውን የወሰደው ከአንድ ቀን በፊት ከአካባቢው ነዋሪዎች በደረሰው ጥቆማ መነሻነት ነው። ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ በአደገኛ ጉዞ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እጅግ ጨምሯል ሲሉ ለዶቼቬለ የተናገሩት በደቡብ አፍሪቃ ኩዋዙሉ ናታል ደርባን ከተማ የፍትህ ቢሮ የቋንቋ አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሰሩት አቶ ኮስሞስ ገብረ ሚካኤል በዚሁ መጠንም ለወጣት ኢትዮጵያውያን የተስፋይቱ ምድር ተደርጋ በምትታየው በደቡብ አፍሪቃ በደላሎች የሚፈጽምባቸው በደልም ከፍቷል።
በሕገ ወጥ መንገድ ደቡብ አፍሪቃ ከደረሱ በኋላ ለእገታ የሚዳረጉት አስቀድሞ ከደላሎች ጋር የተስማሙበትን ውል በጊዜው አላሟሉም የሚባሉት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ ባለፈው ጥቅምትም በጆሀንስበርግ ዳርቻ በአንድ ቤት ውስጥ ታጉረው ያገኛቸውን 80 ኢትዮጵያውያንንም አስለቅቆ ነበር። ፖሊስ እንዳለው በጠባቡ ክፍል ኢትዮጵያውያኑ የተያዙበት መንገድ ኢሰብዓዊ ከመሆኑም በላይ በቤቱ ውስጥ ምግብም ሆነ የግል ንጽህና መጠበቂያ አልነበረም። አቶ ኮስሞስ ከአስቸጋሪና ከከባድ ጉዞ በኋላ ደቡብ አፍሪቃ የደረሱት ኢትዮጵያውያን በደላሎቹ ከመታገታቸው በላይ በምግብም ይቀጣሉ።
ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የገጠማቸው አዲስ ፈተና
ባለፈው አርብ 26 ኢትዮጵያውያን ከታገቱበት ጆሀንስበርግ ዳርቻ ከሚገኝ ጠባብ ቤት ያስለቀቃቸው ፖሊስ በእገታው የጠረጠራቸውንና ሕገ ወጥ ሽጉጥ ተገኘባቸው ያላቸውን ሦስት ኢትዮጵያውያንን ማሰሩንም አስታውቋል።አቶ ኮስሞስ ይህን መራር እውነት ሲሉ ነው የገለጹት። ደርባን ፍትህ ቢሮ የቋንቋ አገልግሎት ክፍል ለኢትዮጲያውያን የትርጉም አገልግሎት የሚሰጡት አቶ ኮስሞስ በግልም በትርጉምና በሕግ አገልግሎት ዘርፍ ይሰራሉ። ደቡብ አፍሪቃ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክ መረጃ የሚያስተላልፈው የዩናይትድ ሚድያ ሀውስ ባልደረባም ናቸው። ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሰደድ የሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን ለመቀየር ብለው የሚጀምሩት ጉዞ የህይወታቸው ማጥፍያ እንዳይሆን መክረዋል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ