ኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ጦርነት ይገጥሙ ይሆን?
ማክሰኞ፣ ግንቦት 19 2017የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራን 34ኛ ዓመት የነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባለፈዉ ቅዳሜ ያስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችንና የፖለቲካ ተንታኞችን እያነጋገረ ነዉ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2018 ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ጋር ያደረጉት ሥምምነት መፍረሱን በይፋ አስታዉቀዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሚመሩትን የብልፅግና ፓርቲም «የዉጪ ኃይላት አዲስ ወኪል ወይም ተገዢ» በማለት ነቅፈዉታል።
ብልፅግና ለአዲስ ጦርነት ቴክኖሎጂና ጦር መሳሪያዎች እያከመቸ፣ «ልክ የሌለዉ ዶላርም» እያወጣ ነዉ በማለት ወቅሰዋል።አንጋፋዉ የኤርትራ መሪ የኢትዮጵያ መንግሥታትን ለ80 ዓመታት የዉጪ ኃይላት «የወኪሎች ወኪል በማለት» አጥብቀዉ ወቅሰዋቸዋል።የኤርትራ ፕሬዝደንት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር መሥርተዉት የነበረዉ ወዳጅነትና በወዳጅነቱ መሠረት ኤርትራ በትግራዩ ጦርነት መሳተፏ ላደረሰዉ ዉድመት «አንፀፀትም» ብለዋል
ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1998 ጀምሮ ፕሬዝደንት ኢሳያስ በአደባባይ ንግግር ሲያደርጉ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ወይም ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ በየጊዜዉ የሚወቅሱ፣የሚከሱና የሚወነጅሉትን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን በዘንድሮዉ ንግግራቸዉ አልጠቀሱትም።የኢሳያስ ንግግር ከህወሓት ጋር ዳግም መወዳጀታቸዉን ጠቋሚ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ደግሞ የዳግም ጦርነት ዝግጅት ምልክት እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
የፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ደጋግመዉ የዉጪ ኃይል የሚሉት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ነዉ።በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዳግም ጦርነት እንዳይጫር «ቁልፉ ያለዉ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዕጅ ነዉ» እንደ አቶ አብዱረሕማን ግምት።
የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤየሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ቃል አቀባይ ዓሊ መሐመድ ዑመር በበኩላቸዉ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ለሕዝባቸዉ ሠላምና ብልጽግና ለማምጣት ከመስራት ይልቅ «ሌሎችን በመዉቀስና በማዉገዝ» እንደኖሩበት አሁንም ደገሙት ባይ ናቸዉ።አቶ ዓሊ ኤርትራ በተለይ «በሁለቱ የአፋር አካባቢዎች ጦር እያሰፈረች ነዉ»ብለዋል።
ከፖለቲካ ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድና ከፖለቲከኛ ዓሊ መሐመድ ጋር ያደረግናቸዉን ሙሉ ቃለ መጠይቆች ከዚሕ በታች ያሉትን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን ያዳምጧቸዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ