ኢትዮጵያና ኤርትራ በአዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች፥ የነዳጅ እጥረት
ሐሙስ፣ ሰኔ 19 2017የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት አስቸጋሪ በመሰለበት በአሁኑ ወቅት፥ በኤርትራ እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ከሰሞኑ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማድረጋቸው ተነግሯል ። ወደ ትግራይ ክልል የሚገባ ነዳጅ በከፍተኛ መጠን መቀነሱ በክልሉ የርዳታ ስርጭት እየተስተጓጐለ መሆኑ ተገልጧል ። በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችም የነዳጅ እጥረቱ ነዋሪዎችን እያማረረ መሆኑ እየተነገረ ነው ። ሁለቱም ርእሰ ጉዳዮች የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቅኝት ትኩረታችን ናቸው ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፥ ለ20 ዓመታት የዘለቀ መፋጠጥ እና መቃቃርን አስወግደው ግንኙነታቸውን ለማደስ እንደገናም ወደ መፋጠጡ ለመመለስ ብዙም አልፈጀባቸውም ። ሁለቱ አገራት ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልልን ባዳረሰው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት «ህወሓት»ን ለመውጋት በሚል በተለይ ትግራይ ክልል ውስጥ ለደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች በተጠያቂነት ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል ። እንዲያም ሁኖ ኢትዮጵያን በትግራይ ክልል በኩል ከኤርትራ ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር ግራና ቀኝ የሚኖሩት የሁለቱ አገራት ዜጎች 'የሕዝብ ለሕዝብ' የተባለ ግንኙነት መጀመራቸዉ ተነግሯል ።
«መቀጠል አለበት ደስ ይላል ። ለሰላም ሁሉም መሥራት አለበት ።» ጆን ረዳ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ አስተያየት ነው ። «እቃ እቃ ጨዋታ፥ መቸም ሕዝብ ተጣልተው ዐያውቅም ። ፖለቲካ፣ ሥልጣን፣ ጥቅም ሁሌም ችግር ይፈጥራሉ » ይላሉ ልዩ ኃይሉ በዛው በፌስቡክ ።
ሁቢ ሃያቲ ዳ ዳ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ አስተያየት፦ «ድሮም ዐዉቀው ነው፥ ሻእቢያ እና ሕወሓት መቼ ተለያዩና?» በሚል ጥያቄ ይንደረደራል ። «1992 አስመራ ልትያዝ ስትል መለስ ዜናዊ ተመለሱ ብሎ ጦሩ አስመራን እንዳይቆጣጠር አደረገ...የቤተሰብ ጠብ ነበር ጊዜው እስኪ ደረሰ ተጣላን አሉ እንጂ አንድ ናቸው፤ ያሁኑ ዕቅዳቸውም ምን እንደሆነ እናዉቃለን» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል ።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በኤርትራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ነዋሪዎች
የባህር በር እና የአሰብ የባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ ይበልጥ ያጦዘው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች ግንኙነት መሻከሩ በግልፅ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት ነው 'የሕዝብ ለሕዝብ' የተባለው ግንኙነት መደረጉ የተሰማው ። ዛላንበሳ ዉስጥ «የሠላም» የተባለ መርኃ ግብር መካሄዱም የተነገረው ባለፈዉ እሁድ (ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም) ነበር ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲነት ያገደዉ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ግንኑነቱን እንደሚደግፍ ዐሳዉቋል ። በተመሳሳይ ከዛላንበሳው ግንኙነት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎም (ሰኔ 8 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) በትግራይ ክልል ራማ በኩል በኤርትራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ሰላማዊ ግንኙነትን የሚያስጀምር የተባለ መርኃግብር ስለማድረጋቸው ዶይቸ ቬለ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምቷል ።
ዮሐንስ ገብረማርያም የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «ለፓለቲካ ድራማ የተከፈተ ነው ነገ መዘጋቱ አይቀርም ፤ የ2018 እርቅ ጦርነት ነው ይዞ የመጣው ይሄም ከዛ የተለየ አይሆንም» ብለዋል ። በኃይሉ አያሌው መስፍን የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፦ «ወያኔና ሻዕቢያ ተስማምተው ማለት ነው?» ሲሉ ይጠይቃሉ፦ ራሳቸውም መልስ ይሰጣሉ፦ «ሕዝቡን ነፃ ቢተውት ሕዝብን እንደ ካርታ መጫወቻ ማድረግ ቢበቃ!!! ሁለቱም ድርጅቶች ይፈራሉ እንጂ በሕዝብ አይወድዱም ሃቁ ይህ ነው!» ሲሉ ።
«ብልፅግና ግን ያውቀዋልን?» ይጠይቃሉ፦ አቤል የእናቱ ዓለሙ በአጭሩ ። «ከኢትዮጵያ ዕውቅና ውጪ የሆነ ግንኙነት ነው» ሲሉ መልስ ይሰጣሉ ጌታነህ ጌትዝ ጌቱ በእዛው ፌስ ቡክ ላይ ። «ሕገወጥ ነው» ሲሉም የራሳቸውን ብይን ይሰጣሉ ። ትችት ብይኑን ትተው አጭር ጥያቄ የሰነዘሩት ደግሞ ሠይፉ መንግሥቱ ናቸው ። «ይህ ጓደኝነት ግን ዘላቂ ይሆን ይሆን?» ሲሉ ።
የነዳጅ እጥረት በኢትዮጵያ
የነዳጅ እጥረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ተነግሯል ። መንግሥት ለነዳጅ ያደርግ የነበረው «ጥቅል ድጎማ» ከግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ መቋረጡም ተዘግቧል ። የነዳጅ ዋጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዓለም ዋጋ ጋር «ተመሳሳይ» መደረጉም ተገልጧል ። የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ባሰሙት ንግግር ፦ «የዓለም ዋጋ ከጨመረ ይጨምራል፤ የዓለም ዋጋ ከቀነሰ ይቀንሳል» ሲሉ ተደምጠዋል ።
መኖር ነው ተስፋዬ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ አስተያየት እንዲህ ይነበባል ። «አባቴ እንኳን ድጎማ፤ ተርፎን ወደ ውጭ ልንልክ መሆኑን አልሰማህም እንዴ???» ሞ ሥልጣን ይቀጥላሉ እንዲህ እያሉ፦ «ድጎማው ሕዝቡን ለሚበዘብዙ ለትራንስፖርት መኪና ባለንብረቶች በወር አስከ 30 ሺ እየተሰጡ ሕዝቡን አደኸዪት፤ ባለንብረቶች ከበሩበት ።» አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፦ «ድጎማ የነዳጅ ዋጋን ዝቅ አድርጎ ለተጠቃሚ መሸጥ ነበር፣ አልገባንም» በማለት ነው ።
ሥላቃዊ በመሰለ አስተያየታቸው፦ «የሁላችንም ኢኮኖሚ ከሚገባው በላይ በማደጉ… እንደውም ላለፉት 7 ዓመታት ሲደጎም የነበረው ጭምር ታሳቢ ተደርጎ መክፈል ይጠበቅብናል ። ደጉ መንግስታችን…» ያሉት ደግሞ ኤፊዬኪያ ገብረሕይወት ናቸው ።
«እንደዚህ አይነት መከራ ኢትዮጵያ አይታ ዐታውቅም»
የሩቅ ሰው በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ የመንግሥት ርምጃን ተገቢነት ዘለግ ባለው ጽሑፋቸው አብራርተዋል ። «መንግስት የወሰደው ርምጃ አስፈላጊና እሰይ ይበል ነው» ሲሉም ይጀምራሉ አስተያየታቸውን ። ምክንያት ያሉትን ይገልጣሉ፦ «ምክንያቱም ከዚህ በፊት ያለው አሠራር የዘርፉ አመራር ባለሀብቶችን እና የጥቁር ገበያ ነጋዴዎችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ። ዞሮ ዞሮ መንግስት ተጎጂ ነበር ዕናውቃለን ለዘርፉ መንግስት ምንያህል በጀት እንደሚፈስ፤ ግን ሕዝቡ በዚሁ ልክ ተጠቃሚ አይደለም» ይላሉ ። ይቀጥላሉ፦ «መኪና ከታርፊ ውጭ ይጭናል፥ ማደያ ነዳጅን ዐውቆ ይደብቃል፥ በዚህ ልክ ነጋዴው ምርት ላይ ዋጋ እንደፈለጉ ይጨምራሉ» ሲሉ ። እናም ጽሑፋቸውን እንዲህ ያጠናቅቃሉ፦ «ነገሩ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ሆኗል ግን የመንግስት ጉዳትና የታችኛው ኅብረተሰብ ጉዳት የከፋ ነበር ። የታችኛው ኅረተሰብ የእድሉ ተጠቃሚ አይደለም » በማለት ።
«እንደዚህ አይነት መከራ ኢትዮጵያ አይታ ዐታውቅም» ሲል ይነበባል የደምስ ውቡ አጭር አስተያየት ። መቼ ነው በቃ የሚለን በሚል ስም የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «የፈረደበት ሕዝብ መከራው በዛ» ብለዋል ። መንግሥቱ መህካ ማሞ በበኩላቸው፦ «ሰሚ ላይኖር ጩኸት ሆነ የእኛ ነገር» ብለዋል ።
ትግራይ ክልል ውስጥ በነዳጅ እጦት ምክንያት ከ150 በላይ የርዳታ እና የሕክምና ግብአት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለቀናት ባሉበት መቆማቸውን ክልሉ ዐሳውቋል ። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፦ ወደ ክልሉ ይገባ የነበረው የነዳጅ መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ በክልሉ የርዳታ ስርጭት ላይ አሉታዊ ተጽእእኖ መፍጠሩን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል ።
«በዛላንበሳ አይገባም እንዴ?» ይላሉ ግርማ አሰፋ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ። የሰሞኑን የኤርትራ እና የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሕዝብ ለሕዝብ የተባለ ግንኙነት ማድረጋቸውን በማጣቀስ ይመስላል አስተያየት የሰጡት ። በዓምላኩ ደሳለኝ በአጭር አስተያየታቸው፦ «እኛምጋ የለ» ብለዋል፤ ነዳጁን መሆኑ ነው ። «ይሄ ኮ ሆን ተብሎ ሲደረግ የከረመ ነው» ያሉት ደግሞ ቀለበት ሙሴ ናቸው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር