ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ትገፋበታለች ተባለ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2017የኢትዮጵያመንግሥት ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የሀገሪቱን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማሳካት መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶች መከተሉን እንደሚገፋበት አሳወቀ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሻከር ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን የመጠቀም ዕድሏን አጥብቦታል ያሉ አንድ የኢኮኖሚ ባለሞያ ሀገሪቱ የንግድ መርከቦቿን ለመጠበቅ የባሕር ኃይል ማቋቋሚያ የባሕር በር መሻቷ ተገቢ ነው ብለዋል። የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት መሰማራቷ ለኢትዮጵያ በወታደራዊ እና ሌሎች መስኮች የመጥቀሙን ያህል ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ እና ከግብፅ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ቀድሞ የነበረውን ውጥረት አባብሷል ሲሉ ቀጣናውን አስመልክቶ ባዘጋጁት ጽሑፍ ጠቅሰዋል።
ወደብ እና የባሕር በር አልባ መሆን ያለው ተጽዕኖ
ወጣት ቶፊቅ የጅቡቲ ዜጋ ነው። በሙያው ደግሞ አሽከርካሪ ።ይህ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ኖሯል። መርካቶ፣ ጠማማ ፎቆ፣ ሜክሲኮ፣ መገናኛ እያለ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ መንደሮችን መለያዎችን እንደሚያውቃቸው ነግሮኛል። አዲስ አበባ ውስጥ ቅንጡ የሚባሉና ከ30- 50 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ውድ ተሽከርካሪዎች ጅቡቲ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን ፍራንክ በላይ እንደማያወጡም አጫውቶኛል። በእርግጥም በተሽከርካሪዎች የግብይት ሥርዓት ውስጥ ተመሳሳይ የዋጋ ልዩነት በኬንያም፣ በሶማሌላንድም መኖሩን ከዚህ በፊት ያነጋገርኳችው ሰዎች ከኢትዮጵያ አነጻጽረው ገልፀውልኛል። ይህ የወደብ አልባ ሀገራት ፈተና ምን እንደሚመስል አንድ ማሳያ ነው።
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ትናንት ሚያዚያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማስከበር ዲፕሎማሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶችን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሥራ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የባሕር በር አማራጭ የግድ ማግኘት ይኖርባታል የሚለውን አቋም ማራመድ ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። በቅርቡ ባደረጉት የፓርላማ ማብራሪያም ይህንን አጠናክረውታል። "የቀይ ባሕር ፍላጎታችን ከሶማሌ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራ፣ ከኬንያ የሚያጣላ የሚያዋጋ መሆን የለበትም"።
በዚህ ረገድ የባለሞያዎች አስተያየት
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚሉት የቀይ ባሕር አካባቢ ሁልጊዜ ከችግር የማይለይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ይህንን አቋም ማራመዷ የተገባ ነው። "ኢትዮጵያ የምትፈልገው ወደብ ብቻ አይደለም። የባሕር ኃይልም ማስቀመጫ ነው የምትፈልገው። የአፍሪካ የንግድ መርከብ በአፍሪካ ትልቁ የንግድ መርከብ ነው። እነሱን መርከቦች ለመጠበቅ ባሕር ኃይል ያስፈልጋል"።
ሚካኤል ኪኺሸን ገብሩ የተባሉ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው መንቀሳቀስ ከጀመረችበት ካለፉት ስድስት ዐመታት ወዲህ ለኢትዮጵያ መንግሥት በዲፕሎማሲያ፣ ወታደራዊ እና ሌሎች ዘርፎች ጥቅም የማስገኘቷን ያህል ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ እና ከግብፅ ጋር ባላት ግንኙነት ቀድሞ የነበረን ውጥረት አባብሷል ሲሉ ጽፈዋል።
ኤርትራ እንደ ሀገር ከቆመች 34 ዓመት ሊሞላት ሳምንታት ቀርተዋታል። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የአሰብ እና የምፅዋ ወደቦችን ካጣች እና በወደብ ኪራይ መፈተን ከጀመረች ሦስት ዐሥርት ዐመታት አለፉ ማለት ነው። ለመሆኑ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መልካም ግንኙነት ለምን የመቀልበስ አዝማሚያ ውስጥ ገባ ብለን የጠየቅናቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ ሦስት ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።
"እንደ አንዳንዶቹ በሻቢያ እና በሕወሓት መካከል ባለው ዘመን የተሻገረ የጠላትነት ስሜት መነሻነት ሕወሓትን ሙሉ በሙሉ ሳንጨርስ [ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ጋር] ወደ ስምምነት ገብተሃል የሚል ኩርፊያ ውስጥ ገብታለች የሚል ነው፤ በኤርትራ በኩል። አንደኛው ደግሞ በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ አያገባህም የሚል ገሸሽ የመደረግ ነገርን አምጥቷል"
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት "በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያለው ሁኔታ እንዲረጋጋ፣ ለሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትሥሥር እና ዕድገት ምቹ እንዲሆን፤ ውጥረቶች እንዲረግቡና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት ቁልፍ መሆኑን" ስለመመልከቱ በመግለጫው አብራርቷል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ